ኢራን አጸፋዊ ነው ባለችው ምላሽ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል አስወንጨፈች

ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች ቢያንስ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። የእስራኤል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት እንዳስታወቀው 21 ሰዎች ቆስለዋል ብሏል። ኢራን በእስራኤል ለተፈፀመባት የአየር ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ነው ያለችውን የሚሳኤል ጥቃት በእስራኤል ከተሞች ላይ ፈፅማለች፡፡

የኢራን መንግሥት ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው፤ ኢራን “እውነተኛ ቃል ኪዳን 3” የሚል ስያሜ የሰጠችውን የበቀል ርምጃ መጀመሯ ታውቋል። የኢራንን ሚሳኤሎች ለማክሸፍ እስራኤል አይረን ዶም ፀረ ሚሳኤሎችን መተኮሷም ነው የተገለፀው፡፡ ኢራን በፈፀመችው ጥቃት ቴል አቪቭ በሚገኘው የእስራኤል መከላከያ መሥሪያ ቤት አቅራቢያ የእሳት አደጋ መከሰቱ ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም ሰባት በሚሆኑ በማእከላዊ እስራኤል በሚገኙ ቦታዎች ሚሳኤሎች መውደቃቸው ተገልጿል።

እስራኤል የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን አጸፋዊ ሚሳኤሎችን ያስወነጨፈችበት የሁለቱ ሀገራት ፍጥጫ ቀጥሏል ። እስራኤል በድጋሚ አርብ ምሽት በፈጸመችው ጥቃት በርካታ ኢላማዎች መምታቷን አስታውቃለች። በቴህራን የመኖሪያ ህንጻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 20 ህጻናትን ጨምሮ 60 ሰዎች መሞታቸውን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ዘግቧል።

በኢራን አጸፋዊ የሚሳኤል ጥቃቶች ሶስት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል። አሜሪካ ወደ ግጭቱ እንድትገባ ከተደረገች ሁኔታዎች በበለጠ ሊያገረሹ ይችላሉ ተብሏል። ኢራን ሚሳኤሎችን የምታስወነጭፍ ከሆነ መዲናዋ “ቴህራን ትቃጠላለች” ሲሉ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ አስጠንቅዋል። የእስራኤል መከላከያ ኃይል ዘጠኝ የኢራን የኒውክሌር ሳይንቲስቶችን እና ባለሙያዎችን ገድያለሁ ብሏል። ጦሩ ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ በፈጸመው ተከታታይ ጥቃት የገደላቸው የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ስድስት ናቸው ብሎ ነበር።

ኢራን በእስራኤል ላይ እየወሰደች ያለችውን አጸፋዊ ርምጃ ለማስቆም አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም እስራኤልን የሚያግዙ ከሆነ በቀጣናው የሚገኙ የጦር ሰፈሮቻቸውን ኢላማ እንደምታደርግ ማስጠንቀቋን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ዘግቧል።

“አሜሪካ ስለ ጥቃቱ ቀድሞ ቢነገራትም በነዚህ ጥቃቶች ላይ ወታደራዊ ተሳትፎ አልነበራትም” ሲሉ የሀገሪቱ የዓለም አቀፍ ድርጅት ጉዳዮች ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማኮይ ፒት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል። “ዋነኛው ቅድሚያ የምንሰጠው በቀጣናው ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ዜጎች፣ ሠራተኞች እና ኃይሎችን ጥበቃ ነው።” ብለዋል፡፡

ኢራን በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ ዜጎች፣ የጦር ሰፈሮችን ወይም መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ካደረገች “የሚከተላት መዘዝ አስከፊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የአሜሪካ አቋም ኢራን ስምምነት ማድረግ አለባት የሚል እንደሆኑ ገልጸው ሀገራቸው “ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ” ትሻለች ።“የኢራን አመራሮች በዚህ ወቅት መደራደራቸው ብልህነት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 78 ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 320 ኢራናውያን መቁሰላቸውን ያስታወቀችው ኢራን አብዛኞቹ ሰላማውያን ዜጎች ናቸው ብላለች። እስራኤል የፈጸመችውን ጥቃቶች “አረመኔያዊ” እንዲሁም “ወንጀል” ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን ተወካይ ሰኢድ ራቫኒ ተናግረዋል።

የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ ኢራን ባቀረበችው ጥያቄ በኒውዮርክ ለተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ድርጅት ነው ተወካዩ ይህንን የተናገሩት። ሰኢድ ራቫኒ የእስራኤል ጥቃት በኒውክሌር ተቋማት፣ በሲቪል መሠረተ ልማቶች እና የመኖሪያ አካባቢዎች ያነጣጠሩ ናቸው ብለዋል።

ተወካዩ አክለውም “ሆን ተብሎ የተፈጸመ ስልታዊ” ግድያ ሲሉ ጥቃቱን ጠርተው “አስደንጋጭ የተሰላ የጠብ አጫሪነት ማሳያ” ነው ብለውታል። “አሜሪካ ለነዚህ ወንጀሎች ርዳታ እና እገዛ በማድረጓ ተባባሪ ናት” ሲሉ ወቅሰዋል። “እስራኤል የአሜሪካን መሣሪያ በመጠቀም በፈጸመችው ጥቃት ሕዝባችን ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አንዘነጋም” ብለዋል። የጸጥታው ምክር ቤት የእስራኤልን ድርጊት እንዲያወግዝ እና ተጠያቂ እንዲያደርጋትም ጠይቀዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You