
ከታደለችው ሁለንተናዊ ተፈጥሯዊ ፀጋ አኳያ ኢትዮጵያ ለተፈጥሮ ቅርብ መሆኗ አያጠያይቅም። ይህንን ተከትሎ ቱሪዝም እና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች ናቸው ብለን ብንናገር ማጋነን አይሆንም። ዘርፉ ደግሞ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ይመራ እንጂ፤ መንግሥታዊ ያልሆኑትን ጨምሮ ከብዙ አካላት ጋር የተሳሰረ ነው። ከነዚህ ውስጥ የአስጎብኚ ማኅበራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ለዛሬ አስጎብኚ ማኅበራት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያላቸውን ሚና እና ለዘርፉ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅዖ እንዲሁም በሚዛመዱባቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከባለሙያ ጋር እንቆያለን። ሀሳብ እና ምክር ሊያጋሩን የታላቅ ኢትዮጵያ ማኅበር መሥራች አባል እንዲሁም የፕሌጀር ኢትዮጵያ አስጎብኚ እና የጉዞ ወኪል ባለቤት አቶ ናሆም አድማሱ ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል።
እንደመግቢያ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ የአስጎብኚ ማኅበራት ሥራ እና ተልዕኮ ምንድነው? ስንል ጠይቀናቸው ምላሽ ሰጥተውናል። አቶ ናሆም፤ እንደማኅበር አምስት ስድስት የሚሆኑ ዓላማዎችን አስቀምጠው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ እነዚህም የአባላትን ጥቅም ለማስከበር ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት፤ አባላቶች በቱሪዝም ልማት ላይ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ ማድረግ፤ አባላትን በመወከል እንደአንድ ድምፅ ሆኖ ማገልገል፤ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ለአባላት ምቹ የገበያ ሁኔታን መፍጠር እና ሙያ ተኮር ሥልጠናዎችን ለአባላት ማመቻቸት ዋና ዓላማዎች እንደሆኑ አንስተውልናል።
ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ለውጥ ላይ ትገኛለች። ሆኖም ይሄ ለውጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን በተዋረድ ሁሉንም ማኅበረሰብ መንካት አለበት ይላሉ። ለውጥ ትርጉም ያለው መታየት ሲችል፤ ማኅበረሰብን ሲጠቅም፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ ሲችል ነው ሲሉ ይናገራሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ የቱሪዝም ዘርፉ በለውጥ እርምጃ ላይ እንዳለ አመላካች የሆኑ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ይገኛሉ ያሉ ሲሆን፤ ለአብነት የመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ የኮሪዶር ልማት፣ እንደአዲስ ኮንቬንሽን ዓለም አቀፍ የሁነት አዳራሾችን፣ በሜጋ ፕሮጀክት እና በገበታ ለሀገር የታቀፉ ዘርፉ ላይ እመርታ ሊያመጡ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን እንደማሳያ ያነሳሉ።
አክለውም እነዚህን ለውጥ አመላካች እንቅስ ቃሴዎች ከአስጎብኚ ማኅበራት ጋር በማዛመድ የጋራ የሆነ መድረክን በመፍጠር እያንዳንዱ ልማት ላይ የሚኖራቸውን ሚና በማጤን ለውጡን ማፋጠን እንደሚቻል ይጠቁማሉ። ይሁንና አንዳንድ ልማቶች ላይ ተሠርተው አልቀው ከተመረቁ በኋላ አስጎብኚ ድርጅቶች ወይም ማኅበራት የማያውቋቸው እንዳሉ ያመለክታሉ። አንዳንዴ ተጋብዘው የዓላማው ተቋዳሽ መሆን የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖር እንቅስቃሴው የበለጠ ይፋጠናል የሚል እምነት እንዳላቸው ያመለክታሉ፡፡
ለቱሪዝም ዕድገት እየተደረጉ ያሉ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች አስጎብኚ ማኅበራትን ያሳተፉ መሆናቸው የጋራ ኃይል ከመፍጠር አኳያ የላቀ ሚና አለው ሲሉ የሚናገሩት አቶ ናሆም፤ አስጎብኚ ማኅበራት መነሻው ቱሪዝም መድረሻው እንዲሁ የሀገር የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደሆኑ አስታውሰዋል። በዘርፉ የተሰማሩ እና የሠለጠኑ ባለሙያዎች ያሉበት እንደመሆኑ ባለሙያዎች የሚሰጧቸው ግብዓቶች ደግሞ ለዘርፉ ወሳኝነት እንዳለው አመላክተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ፖሊሲ ሲቀርጽ ባለድርሻ አካላትን አሳትፎ፣ ሌሎች አካላትንም መድረክ ላይ እንዲገኙ በማድረግ መሆኑን አንስተው፤ ይሄ ዓይነቱ አሠራር በዘርፉ ላይ የጋራ ዓላማ ለማበጀት ጥሩ እንደሆነ አመላክተዋል። ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ሥራዎች ሲታሰቡ አብሮ መሥራት፣ አብሮ ግብዓት መሰብሰብ፣ አብሮ ማሰብ እና አብሮ ማከናወን አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው፤ ቀጣይ እንቅስቃሴዎችም በዚህ መንገድ ቢቀጥሉ የተሻለ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
እንደእሳቸው ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በማዘጋጀት እና በመታደም የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ወሳኝ ለውጦችን እያደረገች ትገኛለች። የጉብኝት ፓኬጆችን በማዘጋጀት የኹነት እንግዶችን ለቱሪዝም ዘርፉ በመጠቀም እንዲሁም ሀገር ከማስተዋወቅ አኳያ ጥሩ ነገር አለ። ይሁንና ይህ በቂ እንዳልሆነ ካለው ግዙፍ እና ሰፊ የሥነ ምሕዳር ፀጋ አኳያ ያልተሠሩ ሥራዎች መዘንጋት የለባቸውም።
‹‹ስብሰባ እንዳለ ልናውቅ እንችላለን። ሆኖም ተሳታፊዎች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ የትኛውን የሀገራችንን የቱሪዝም ስፍራ እንደጎበኙ እና እንደሚጎበኙ የማይታወቅበት ሁኔታ አለ፡፡›› የሚሉት አቶ ናሆም፤ እየተሠሩ ያሉ መልካም ሥራዎች እንዳሉ ሆነው የኹነት እንግዶችን ተቀብሎ በምን ያክል ጊዜ ውስጥ የትኞቹን ስፍራዎች ማስጎብኘት ይሻላል ከሚለው ጋር ተያይዞ ክፍተት እንዳለ አንስተዋል።
ፓኬጆች ቢኖሩም ፓኬጆቹ እንዴት መሸጥ እንደሚገባ፤ ተሰብሳቢዎቹ እንዴት ሊያገኟቸው እንደሚችሉ፤ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ መስተካከል ያለባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ አንስተዋል። እስከሚመጡ ጠብቆ ‹‹ይሄ ይሄ አለን›› ማለቱ ያን ያክል አዋጪ እንደማይሆን አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደው ስብሰባም ሆነ ጉብኝት በአንድ ጊዜ ማድረግ ነው።
ይሁንና የተሻለው አካሄድ ስብሰባ ከመደረጉ ቀደም ብሎ ታዳሚዎች ጊዜያቸውን ለሚፈልጉት የመስሕብ ስፍራ እንዲጠቀሙ የቅድመ ዝግጅት ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። አክለውም እንግዶች ስለሀገሪቱ የቱሪዝም መስሕቦች ቀድመው ቢያውቁ ባላቸው ውስን ጊዜ ውስጥ የትኞቹን ቦታዎች ማየት እንዳለባቸው መወሰን እንዲችሉ ዕድል የሚሰጥ ነው። ከዚህ አኳያ ያሉ ክፍተቶች መስተካከል ቢችሉ ጥሩ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ እንዲህ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ከመጠቀም የሚጀምር ነው ያሉት አቶ ናሆም፤ ሁነት ሲዘጋጅ የሚመጡ የውጭ ሀገር እንግዶች ቱሪዝሙ ላይ ፈሰስ የሚያደርጉት ገንዘብ አለ። አብረዋቸው የሚመጡ ጋዜጠኞች ይኖራሉ። ይህ ኢትዮጵያን ለዓለም ከማስተዋወቅ አኳያ የተሻለ ዕድል ስለሚኖረው እዚህ ላይ ጠንካራ ሥራዎች ሊሠሩ ግድ እንደሚል አንስተዋል፡፡
ኮንፍረስ ተሳታፊዎች በቱሪስት ቪዛ እንደሚመጡ አስታውሰው፤ እነዚህ እንግዶች በኢትዮጵያ መስሕብ ተማርከው፣ ጊዜያቸውን ገንዘባቸው አውጥተው ቦታዎችን እንዲጎበኙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት የቅንጅት ሥራዎች ሊዳብሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
አስጎብኚ ማኅበሩ ከባህል እና ቱሪዝም እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጋር ያላቸው የአብሮ መሥራት ቅንጅት ምን እንደሚመስል ጠይቀናቸው፤ አስጎብኚ ማኅበሩ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠራ አብራርተዋል። ከሥራዎቹ መካከል ወሳኝ ከሚባሉት ከገቢዎች ሚኒስትር ጋር የሚሠሩ መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሏት ሀገር ናት። ከዚህ አኳያ ዘርፉን ለማስተዋወቅ፣ የቱሪስት ቁጥሩን ከመጨመር ጋር እንግዶች ላይ የተጣለውን የአስራ አምስት በመቶ ታክስ ላይ እየተነጋገሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ሌሎች ሀገራት ከጥቅሉ ላይ ሳይሆን ከሚያገኙት ትርፍ ላይ ታክስ እንደሚቆርጡ በማመላከት፤ ያን በማድረጋቸው በዘርፉ ላይ እመርታ ከማሳየት ባለፈ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል። ይህ አሠራር ኢትዮጵያ ሲመጣ ውድ መዳረሻ ያላት ሀገር ያደርጋታል። የታክስ ሥርዓቱን ማስተካከል ሀገሪቷን ተወዳዳሪ ከማድረግ፤ ብዙ ጎብኚዎችን ከመሳብ፤ መስሕቦችን ከማስተዋወቅ፤ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ከማድረግ አኳያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ያለው የጎብኚዎች ፍላጎት ከሰርቪስ ጥራት እኩል ዋጋ ማግኘትም ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን አንስተዋል። የሀገሪቱ የተፈጥሮ ፀጋ የቱንም ያህል ቢተዋወቅ፣ የቱንም ያህል አስደናቂ ቅርስ ቢኖር፤ ዋጋቸው ላይ ለጎብኚዎች አስቻይ ሁኔታ ካልተፈጠረ ተጠቃሚነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እንደሆነ አንስተዋል። በአፍሪካ ደረጃ ግብፅ፣ ኬኒያ እና ታንዛኒያ በቱሪዝም ዘርፉ እየተጠቀሙ ያሉ ሀገራት ናቸው። ተመጣጣኝ ያልሆነ ዋጋ፤ ዕድሎችን ለነዚህ ሀገራት አሳልፎ መስጠት ያስከትላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እነኚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከገቢዎች እና ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ልክ መሄድ እንዳልቻሉ ይናገራሉ። ዘርፉ የኤክስፖርት ዘርፍ በመሆኑ የታክስ ምጣኔው ዜሮ መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተው፤ የገቢዎችም ሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር የሚረዱት ኤክስፖርት ከሀገር ወጥተው ወደውጭ የሚላኩ ነገሮችን ብቻ ነው። ይሁንና የቱሪዝም ዘርፍ ልዩ የሚያደርገው የውጪ ምንዛሪ ማምጣቱ እንዳለ ሆኖ፤ ወደ ሀገር የሚገባ እንጂ ወደ ውጭ የሚሄድ ምንም የለም። ነገር ግን በአረዳድ ክፍተት አገልግሎቱ የውጭ ምንዛሪ ቢያስገኝም፤ አገልግሎቱ በሀገር ውስጥ ስለተሰጠ እና ሀገር ውስጥ ክፍያው ስለተፈፀመ ከጥቅሉ ላይ የአስራ አምስት በመቶ ታክስ ይቆረጥበታል የሚል መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ ላይ እንደዋነኛ የሚነሳው የዘርፉን ሁኔታ፣ የዘርፉን ባሕሪ መረዳት ነው። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ የሚሠራ ሥራ ብዙም አዋጭነት አይኖረውም። እየታየ ያለው የቱሪዝም መነቃቃት ባልተገባ የታክስ አረዳድ እንዳይገታ ሁኔታዎችን መመልከት ተገቢ እንደሆነ አቶ ናሆም ገልጸዋል። ይህም እንደሀገር መገኘት ያለበት የውጭ ምንዛሪ እንዳይገኝ ከማድረጉም በላይ፤ ለጎረቤት ሀገራት ምቹ ዕድሎችንም የፈጠረ እንደሆነ አንስተዋል። ለአስርተ ዓመታት ያህል ክርክር ሲደረግበት የቆየ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም እልባት እንዳላገኘ አንስተዋል፡፡
ሀገሪቱ በቱሪዝሙ ላይ ትልቅ አቅም አላት ያሉት አቶ ናሆም፤ እየታየ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ የቅርብ ዓመታት የለውጥ ዐሻራ መሆኑን ጠቁመው፤ ወደፊት የበለጡ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጅት እያደረገች እንደሆነ ገልጸዋል። የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ማስተዋወቋ፣ የኢጋድ አባል ሀገራት ጋር የአስር አመት ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ማስተር ፕላን አዘጋጅ አካል ሆና መመረጧ፤ የተቀበለችው አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፍ አደራዎች ያላትን እምቅ አቅም የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
አያይዘውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቱሪዝም ልማት ላይ ሻምፒዮን ሆነው መመረጣቸው፤ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ከማሳየቱም በላይ ቱሪዝም ለሀገር ወሳኝ የኢኮኖሚ አውታር አድርጎ ለመጠቀም የሚደረግ ፍላጎት ማሳያ ነው ብለዋል። ይሄን ዕድል በትብብር፣ በትስስር፣ በውስጥ አቅም አበልፅጎ መጓዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ሌላው አቶ ናሆም እንደችግር ያነሱት የመስፈርት ጉዳይን ነው። አንድ በሙያው ላይ ረጅም ጊዜ የቆየ ሰው ኢንቨስትመንት ፍቃድ ለማውጣት እንደማይችል ጠቅሰው፤ ብቃት ተብሎ የሚቀርበው መኪና ይዞ መገኘት እንደሆነ አንስተዋል። ሙያ እንጂ መኪና የብቃት ማረጋገጫ ሊሆን አይገባም የሚል እምነት እንዳላቸውም አመላክተዋል፡፡
በትክክለኛው መንገድ ከታየ ሰው በሙያው ተመዝኖ፣ ፍቃድ አውጥቶ፣ ለሀገር ብዙ ነገሮችን ማምጣት ይችላል። ቤተሰቡን ይጠቅማል። ማኅበረሰቡን ያገለግላል። ነገር ግን በአንዳንድ አሠራሮች ብዙ ባለሙያዎች ዘርፉን በነፃነት መቀላቀል ባለመቻላቸው፤ ሙያው ኖሯቸው ፍቃድ ማግኘት ባለመቻላቸው በተለያየ ሁኔታ በራሳቸው የሚሠሩ እንዳሉ አመላክተዋል።
ለረጅም ጊዜ ይፀድቃል እየተባለ ያልፀደቀ የተዘጋጀ ሰነድ መኖሩን አስታውሰው፤ በተጨማሪ በአዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ላይ ሙያን መሠረት ያደረገ መስፈርት እንደሚወጣ መጠቀሱን ገልጸዋል። የዚህ ፖሊሲ መፅደቅ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ አንስተው፤ ለባለሙያዎች ዕድል የሚሰጠው አዋጅ በቶሎ ፀድቆ ዘርፉ ላይ የበለጠ እንዲሠራ እና ለውጥ እንዲመጣ እንደሚፈልጉ አመላክተዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያ የሚፈልግ ዘርፍ ነው። ለጋራ ለውጥ የጋራ አሠራር አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፤ ለዘርፉ እድገት የባለሙያዎች ወደፊት መምጣት ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል። በአንድ ዘርፍ ላይ ቁርጠኝነት ከባለሙያ ጋር ሲቀናጅ ትርጉም ይኖረዋል ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
እንደአጠቃላይ አሁን ባለው ሁኔታ ዘርፉ ራሱን ከመግለጥ፣ ለልማት ከማዋል፣ ማኅበረሰቡን ከማንቃት አኳያ የተሻለ ሥራ እየተሠራበት መሆኑን አንስተው፤ በተለይ ሀገሪቱ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ችግሮችን በመቅረፍ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል። አያይዘውም ቱሪዝም እና ሰላም የማይነጣጠሉ በመሆናቸው፤ ሰላም ላይ ቢሠራ ለዘርፉ የበለጠ ዕድል ከፋች ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ አስገንዝበዋል፡፡
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም