
ፊደል ቀርጻ ለዘመናት ሀገር በቀል የዕውቀት ችቦ ስታበራ የኖረችው ኢትዮጵያ በንባብ ጉዳይ ፤ አሁናዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት (ወመዘክር) ከንባብ ባህል እያፈነገጠ ያለውን ትውልድና የትምህርት ሥርዓትን ከንባብ ጋር ለማቆራኘት ሰፊ ሥራ እየሠራ ስለመሆኑ አስታውቋል።
ተቋሙ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ እና ከጢዮ ወረዳ አስተዳደር ጋር በመጣመር ከሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ “የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል በአሰላ ከተማ የንባብ ሳምንት በማካሄድ ላይ ነው።
“የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት ሰኔ 5 እና 6 በሁለቱ ቀናት በአሰላ ከተማና ጢዮ ወረዳ ለሚገኙ ለዘጠኝ የ 1ኛ ደረጃ፣ ለአራት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ለአሰላ ማረሚያ ቤት የሚውል በድምሩ 3ሺህ 545 መጻሕፍት እና የ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን 69 ሺህ 698 ብር የገንዘብ ድጋፍ አበርክቷል። ከዚህ ውስጥም 340 መጻሕፍት እና 113 ሺህ 940 ብር ለማረሚያ ቤቱ የሚውል ነው።
“ዘመድ ቤተሰቦቻችሁ እናንተን አገልግል ቋጥረው፣ ስንቅ ይዘው ይጠይቋችኋል። መጽሐፍ ይዞላችሁ የሚመጣ ግን አይኖርም። ስለዚህ እኛም ከአገልግሉ ይልቅ ለእናንተ የሚያስፈልጋችሁ የአዕምሯችሁ ምግብ እንደሆነ በመረዳት ዛሬ እንደጅምር እኚህን መጻሕፍት አበርክተንላችኋል” በማለት ለታራሚው ንግግር ያደረጉት፤ በኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት የቤተ መጻሕፍት ሃላፊ አቶ አባተ ካሳው ከላይ የተጠቀሰውን ድጋፍ አበርክተውላቸዋል።
ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ቤተ መጻሕፍትም ሆነ የመጻሕፍት አቅርቦት እንዳልነበረ የጠቀሱት የማረሚያ ቤቱ ሃላፊ ኮማንደር አበራ ገለታ ሾሌ “በሥነ ጽሁፍ የዳበሩና መጽሐፍ እስከማሳተም ድረስ ፍላጎት ያላቸው ታራሚዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ለንባብ የሚሆኑ መጻሕፍትን ለማግኘት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ግን አልነበረም። ለታራሚዎች ከቅጣት ይልቅ በንባብ ባህል ላይ ብንሠራባቸው ራሳቸውን አንጸው ለመውጣት ከዚህ የተሻለ ምንም አይኖርም።
በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ቤተ መጻሕፍት መገንባት ይኖርባቸዋል በማለት ከተለያየ ማህበረሰብና አካባቢ አንድ ላይ የተሰባሰበው ታራሚ የእስር ጊዜውን ጨርሶ የሚሄደው ወደዚሁ ልዩ ልዩ አካባቢና ማህበረሰብ እንደመሆኑ በእነርሱ ላይ መሥራት ማህበረሰባዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አስቀምጠዋል። የማረሚያ ቤቱ ሃላፊ አክለውም፤ የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት ያበረከታቸውን መጻሕፍት እንደመነሻ በማድረግ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ቤተመጻሕፍት የማደራጀት ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ማረሚያው እስካሁን ትምህርት ቤት የሌለው ሲሆን፤ በቅርቡ ሊገነባ መታቀዱንም ሃላፊው ገልጸዋል።
“ለሰው ልጆች ሁሉ እኩል የሆነው ትልቁ ሀብት ‹‹ጊዜ›› ነው። እናንተ ደግሞ እዚህ ማረሚያ ቤት ውስጥ የጊዜ ሀብታሞች ናችሁ። ይህን ሀብት ለንባብ ማዋል ከቻላችሁ ማንነታችሁን ማነጽ ብቻ ሳይሆን፤ ነገ ከዚህ ስትወጡ ሕይወታችሁን የምትቀይሩበትን ቁልፍ መያዝም ትችላላችሁ” በማለት ለታራሚዎች ምክረ ሃሳባቸውን ያጋሩት ደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ፤ ዛሬ ላይ ሆነው ስለትናንቱ ጸጸት ከማሰብና ከማሰላሰል ወጥተው በእጃቸው ያለውን ዛሬን እንዴት በንባብ ነገን መሥራት እንዳለባቸው ለታራሚው አስረድተዋል። በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች መጻሕፍትን የጻፉ ሌሎች ደራሲያንም ከታራሚው ጋር ቆይታ በማድረግ ልምድና ክህሎቶቻቸውን አካፍለዋል።
ትውልዱን በንባብ መንፈስ ለማነጽ ማረሚያ ቤቶች ከየትኛውም በላይ አመቺ ስፍራ እንደሆኑ ቢገለጽም፤ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በሀገራችን የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ምቹ የቤተ መጻሕፍት ማዕከላትና የመጻሕፍት አቅርቦት የሌሉባቸው ናቸው። ይህንኑ ችግር በመረዳት፣ የማህበረሰባችንን የንባብ ባህል ለማሳደግ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የገለጸው የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት፤ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በየወሩ የንባብ ሳምንት በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። በአሁኑ ሰዓት ከተቋሙ ጋር በጥቂቱ ትምህርት ሚኒስቴር ድጋፉን እያደረገ ሲሆን፣ በቀጣይ መንግሥታዊም ሆኑ የግል ተቋማትና ግለሰቦች ከዚህ ግዙፍ ዓላማ ጋር አብረው እንዲሠሩ ጠይቋል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም