
-የመምህራን ትውልድን የማፍራት ተልዕኮ በደመወዝ የሚተመን አይደለም
አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ክፍል በይፋ ተከፍቷል። የመምህራን ትውልድን የማፍራት ሀገራዊ ተልዕኮ ዋጋው በደመወዝ የሚተመን እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ይህ ድንቅ ክንውን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢትዮጵያ ምላሽ፣ ግብርና፣ የውሃ ኃይል እና ኢነርጂ፣ ኤሮኖቲክስ እና አቪየሽን ላይ ያተኮሩ አምስት የአውደ ርዕይ ምድቦችን የያዘ መሆኑም ተገልጿል።
ይህም ሀገራችን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ እንደሆነም ነው የተጠቆመው።
በተጨማሪም በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የህዋ ቅርጽ ሉላዊ የትዕይንት አዳራሽም በዚሁ አውደርዕይ ይፋ ሆኗል። በ1 ሺህ ሜትር ስኩዌር ሜትር እና 36 ሜትር ዲያሜትር ይዞ ያረፈው አዳራሽ ዘመኑን በዋጀ የ4k ዲጂታል ምስል (ጥራት) ማሳያ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ነውም ተብሏል።
ምስለ-ህዋው ከፍተኛ ጥራት ያለው እጅግ አስደማሚ ምስሎችን በማቅረብ የህዋውን ዓለም እጅግ አቅርቦ የሚያሳይም ነው። እውቀት ለማሰስ፣ ለመማር እና ለመነሳሳት ምቹ የሆነው የሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል።
ኢትዮጵያውያን በሙዚየሙ ተገኝተው የኢትዮጵያን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መፃዒ ተስፋ እንዲመለከቱም ተጋብዘዋል።
በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ መምህራን ጋር ባደረጉት ውይይት፤ መምህራን ትውልድን የማፍራት ሀገራዊ ተልዕኮ ይዘው የሚሠሩት ሥራና ድካማቸው በደመወዝ የሚተመን ዋጋ እንደሌለው ጠቁመዋል።
ለመምህራን ብቻ በልዩ ሁኔታ የደመወዝ ጭማሪ ብናደርግ ችግሩ አይፈታም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመምህራን ችግር በደመወዝ ጭማሪ ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን መገንዝብ ተገቢ ነው። የመምህራንን ጥያቄዎች የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ በፖሊሲ ማሕቀፍ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
በእውነትና እውቀት የተገነባ ትውልድ ለመፍጠር የመምህራን ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሥራቸው ለሀገር መሥራትና መድከም የሚያመዝንብት ነው። ያም ሆኖ መምህራን የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በሂደትና በየደረጃው ለመፍታት ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ብለዋል።
ለመምህራን ትልቅ አክብሮት አለን፤ ያላቸውን ሀገራዊ አበርክቶም በውል እንረዳለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ለዚህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመምህራን በይፋ እውቅና መስጠታቸውን አስታውሰዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የተረከብነው ሀገር እዳ፣ ድህነት፣ ችግር ያለበት እና አንድነቱ የላላ ነው፤ ይሄን ደጋግመን ብናወራ ለውጥ የለውም፤ ከዚህ ለመውጣትና ለልጆቻችን የተሻለች ኢትዮጵያን ማስረከብ የሚያስችል ራዕይና ትጋት ያስፈልጋል።
መምህራን እንደ ሀገር ያለውን ችግር እና እድል መረዳት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፤ ለልጆቻችን የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ የበኩላቸውን ሚና ሊያበረክቱ እንደሚገባ አብራርተዋል።
ያለንበት ዘመን ውሸትና ጩኸት የነገሰበት ነው፤ ውሸትና ጩኸት ደግሞ የተሠራን ያፈርሳሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የድህረ እውነት ዓላማ ከዕለት ጉርስ ተሻግሮ ማሰብ የሚችል ትውልድ መፍጠር መሆኑን አስረድተዋል።
በድህረ እውነት ዘመን መምህራን እውነትና እውቀትን ለመፈለግ አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ አንስተው፤ የድህረ እውነት ዘመን መዳረሻ ዓላማ እና ግብ የሌለው ከዕለት ጉርስ ያለፈ ነገር ማየት የማይችል ትውልድ መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።
መምህራን በዚህ የድህረ እውነት ዘመን እውነት እና እውቀት አሸንፈው እንዲወጡ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
መምህራን የትናንት ታሪክን በማወቅ፣ ዛሬ በመረዳትና ነገን በመገንዘብ የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ በማስረከብ በኩልም ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አንስተው፤ ኢትዮጵያ ከችግር፣ ከድህነት፣ ከመከፋፈል እና ከልመና ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ገበታውን እንዴት እናስፋው የሚለውን በማሰብ ምርታማነትን ለማሳደግ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ተቋማትን በማዘመን የመምህራንን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሠራ አመልክተዋል።
የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ፣ የጋራ ትርክት ግንባታ፣ ምርታማነት፣ የገጠር ኮሪዶር እና የትምህርት ጥራት ላይ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው፤ ችግሮችን ለመፍታት የተቀመጡ ማሕቀፎችም ወደ ግብ የሚያደርሱ በመሆናቸው ለስኬቱ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የመምህራን ሚና ተማሪዎችን በማስተማር ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ ጠቁመው፤ ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን፣ ምርትና ምርማነትን ለማሳደግና የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ከግብ ለማድረስም አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥት ለሰላም በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የሰላም ሚኒስቴርን ከማቋቋም ጀምሮ ችግሮችን ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰላማዊ መንገድን ምርጫቸው ላደረጉ ሁሉ በሩ ሁልጊዜ ክፍት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የመምህራን ውይይት መምህራን በየደረጃው ሲያካሂዱት የነበረው ውይይት ማጠቃለያ መሆኑ ተመላክቷል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም