ጥበባት ለሀገር ማንሰራራት

ወይዘሮ ትዕግስት ለማ ይባላሉ። የካስማ ኪነ ጥበብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሥራችና አባል ናቸው። በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀው 16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው የኢትዮጵያውያን የልብስ አሠራር የፈጠራ ውጤት የሆነውን የጥጥ መፍተል አሠራር እያሳዩ ነው።

ወይዘሮ ትዕግስት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከተክል እስከ መልበስ ድረስ ያለው የጥጥ ፈትል ሥራ ራሱን የቻለ የቀላል ኢንዱስትሪ አይነት ነው። ወደ ከባድ ኢንዱስትሪ የሚወሰደውና ‹‹ኮተን›› ተብሎ የሚመጣው ይሄው የኢትዮጵያ ነባር ሀገር በቀል ሥራ ነው።

እናቶቻችን በቱባው ሠርተው ይለብሱት የነበረ የኢንዱስትሪ መነሻ ነው። በብዙ ሀገራት የልብስ መሠረቱ ጥጥ ነው። በኢትዮጵያ ደግሞ ቀለሙን እና ዓይነቱን በመለያየት የማንነትና የባህል መገለጫም ነው። የወላይታ፣ የወሎ፣ የሐረር… እየተባለ በተለያየ የጥበብ መገለጫነት ይሠራል ብለዋል።

‹‹ካስማ ዕድሜያችን ከ40 በላይ የሆኑ እናቶችን ያገናኘን ነው›› ያሉት ወይዘሮ ትዕግስት፤ ይህን የጥጥ ፈትል ሥራ ለማወቅ የእናቶቻቸው ልምድ እንደነበራቸው ይናገራሉ። የአሁኑ ትውልድ የማያውቀው መሆኑን በትዝብት የተናገሩት ወይዘሮ ትዕግስት፤ ካስተማሯቸው ግን የአሁኖቹ ወጣቶች ፈጣን እና ቶሎ የሚገባቸው መሆኑን ይናገራሉ።

እንደ ወይዘሮ ትዕግስት አስተያየት፤ እንዲህ አይነት ወደ ኢንዱስትሪ የሚወስዱ ነባር የኢትዮጵያ ባህሎች በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካተው ሊሰጡ ይገባል። ነበር ሀገር በቀል የፈጠራ ውጤቶችን ማለማመድ ወደ ዘመናዊ አሠራር እንዲወስዳቸው ያደርጋል።

የዘርፉ ባለሙያዎችም ጥናት እንዲያደርጉበት መነሻ ይሆናል። ጥጥ መፍተልና እንዝርት ማሽከርከር ያስለመዷቸው ተማሪዎች በቀላሉ መፍተል እንደቻሉም ወይዘሮ ትዕግስት ገጠመኛቸውን ተናግረዋል።

መምህርት አለመወርቅ ጌታቸው በሙያቸው መምህር ናቸው። ካስማ የኪነ ጥበብ ማህበርን ወክለው የተገኙት መምህርት አመለወርቅ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ካስማ የኪነ ጥበብ ማህበር ሀገር በቀል የሆኑ የኢትዮጵያ የጥበብ ፈጠራዎች እንዲያንሰራሩ ሥልጠና ይሰጣል።

የስፌት አገልግል ዕቃዎች፣ ከቅል የሚዘጋጁ ሽክናዎችና የሸክላ ዋንጫዎች ይሠራሉ። ትንሽ ወደ ዘመናዊነት ሲመጣ ደግሞ የጥልፍ እና የዳንቴል ሥራዎች ይሠራሉ። የባህል የመጠጥ አይነቶችም ይዘጋጃሉ ነው ያሉት።

እንደ መምህርት አመለወርቅ አስተያየት፤ ሽክና ከምን እንደሚዘጋጅ ብዙዎች አያውቁም ነበር። ሀገር በቀል ከሆነው የቅል ምርት ሀገር በቀል በሆነ ባህላዊ መንገድ የሚዘጋጅ የጠላ መጠጫ ዕቃ መሆኑን ሲያውቁ ብዙዎቹ ወጣቶች የነበረ ባህል አይመስላቸውም ብለዋል። እንዲህ አይነት ባህላዊ የፈጠራ ሥራዎችን ማስተዋወቅ ለዘመናዊ ፈጠራ ማነሳሻ ይሆናል ሲሉ ይገልጻሉ።

ከአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ከሴቶች ማረሚያ የመጡት ወይዘሮ ፀሐይ ደበበ በ16ኛው የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ፌስቲቫል ላይ የዕጅ ሥራ የሆኑ መገልገያ ዕቃዎችን እየሸጡ ነው። ወይዘሮ ፀሐይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የተለያዩ ባህላዊ የዕጅ ሥራዎች ይሠራሉ፤ እንዲህ አይነት የባህል ፌስቲቫሎች መዘጋጀታቸው ባህልን ከማስተዋወቅ ባሻገር የፈጠራ ባለቤቶች ሥራዎቻቸውን እንዲሸጡ እና ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል። በማረሚያ ቤቱ ውስጥም ሐሙስ ቅዳሜ እና እሁድ ለታራሚ ቤተሰቦችና ጠያቂዎች እንደሚሸጥ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው(ዶ/ር) በ16ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ኪነ ጥበብ ሃሳብን ከቃላት ባለፈ ኃይል ማስተላለፍ የሚቻልበት ነው። ኪነ ጥበብ የለውጥ አራማጅ እና የለውጥ ማፅኛ ዘዴ ነው፤ ተሻጋሪ የሆነ አሰባሳቢ ሃሳብን በማስረፅ ሕዝብን ለአብሮነትና ለብልፅግና እንዲነሳ ያደርጋል ብለዋል።

‹‹ኪነ ጥበብ ሀገርን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚያስተሳስር ነው›› ያሉት ኃላፊዋ፤ ኪነ ጥበብ በየዘመኑ ያለውን የሀገር ፍቅር የሚያንፀባርቅ ነው ይላሉ።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ኪነ ጥበብ የሰው ልጅ የምናብ አስተሳሰብ እውቀት እና የፈጠራ ሥራ ውጤት የሚታይበት ነው። የሠለጠኑ ሀገራት የሥልጣኔያቸው መነሻ የምናብ አስተሳሰባቸውን እና የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በአግባቡ መጠቀም ነው። የለውጡ መንግሥትም ምናብ እና ፈጠራ ትኩረት እንዲሰጣቸው አድርጓል። በተሠሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ ምናብ እና የጥበብ ፈጠራ ያላቸው ሚና ምስክር ነው ያሉት።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ የፌስቲቫሉ መዘጋጀት ኪነ ጥበብ ለሀገር ገጽታ ያለውን ፋይዳ ያሳድጋል። የተለያዩ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህልና ፈጠራ እንዲተዋወቅ ያደርጋል። ነባር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለጀማሪዎች ልምዳቸውን የሚያሳዩበት እና አዳዲስ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ኪነ ጥበብ አሰባሳቢ ትርክት በመገንባት ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጠናከር ያደርጋል። ኪነ ጥበብ ሁለንተናዊ ብልፅግናን በማምጣት የነገዋን ኢትዮጵያ የሚሳልበት ዘርፍ ነው። ይህን የኪነ ጥበብን አቅም በማወቅም ከ53 ሺህ በላይ ከሚሆኑ የጥበብ ባለሙያዎች ጋር ውይይትና ምክክር ተደርጓል ብለዋል።

‹‹ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት›› በሚል መሪ ቃል ትናንት ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም የተጀመረው ከተማ አቀፍ ፌስቲቫል ነገ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You