በሮም አደባባይ የታየው የኢትዮጵያ ጀግንነት

የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ታሪክ በሀገራቸው ብቻ የተወሰነ አይደለም። በጠላት አገር አደባባይ እንደ አንበሳ ሞገሳቸውን የሚያሳዩ ናቸው። ከ87 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 7 ቀን 1930 ዓ.ም ኢትዮጵያዊው ጀግና ዘርዓይ ደረስ በጣሊያን ሮም አደባባይ የጣሊያንን ሕዝብ አፍ ያስያዘ የጀግንነት ገድል ፈጽሟል። በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የዚህ ጀግና ታሪክ እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት የታሪክ ክስተቶችን እናስታውስ።

ከ97 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 7 ቀን 1920 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ጁን 14 ቀን 1928) ዓለም አቀፉ አብዮተኛ፣ አርጀንቲናዊው የማርክሲስት አቀንቃኝ፣ የነፃነት ታጋይ፣ ሐኪም፣ ደራሲ፣ መምህር፣ ዲፕሎማት፣ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያ እና የጦር መሪ … ኧርኔስቶ ‹‹ቼ›› ጉቬራ ተወለደ። ይህ ዘርፈ ብዙ ባለሙያ በዋናነት በማርክሲስት አብዮተኛነቱ ይታወቃል። ለሌሎች ዓለም አቀፍ አብዮቶችም አርዓያ ተደርጓል። በኢትዮጵያም በተለምዶ ‹‹ያ ትውልድ›› እየተባለ የሚጠራው የ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ

ፋኖ ተሰማራ

ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆቺ ሚኒ

እንደ ቼ ጉቬራ

የሚል መሪ ቃል ነበረው። ይህ መፈክር ዛሬ ድረስ ያንን ትውልድ ለማስታወስ ጥቅም ላይ ሲውል ይሰማል።

ከ43 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 6 ቀን 1974 ዓ.ም ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተወለደ።

በዚሁ ወደ ሌላኛው ጀግና ዝርዝር ታሪክ እንሂድ።

በተድላ ዘዮሐንስ ዘውዴ የተጻፈው ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ-ከወልወል እስከ ጎንደር (ግንቦት 1927-ኅዳር 1934)›› መጽሐፍ እና ሌሎች ሰነዶችን ዋቢ አድርገን በዛሬው የሳምንቱ በታሪክ ዓምዳችን ይህን ክስተት እንዘክራለን።

ዘርዓይ ደረስ የተወለደው በ1908 ዓ.ም ኤርትራ ውስጥ አዲ ሓይስ በተባለ ስፍራ ነው። ያደገው ደግሞ እዚያው ኤርትራ ውስጥ ሓዘጋ በተባለ ቦታ ነው። ርዕሰ ደብር እቁበ እንድርያስ (በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ትምህርት የተማሩና ያስተማሩ) በተባሉ የሃይማኖት አባት አማካኝነት የቤተ ክህነት ትምህርት ተምሯል።

ከቤተ ክህነት ትምህርት በኋላ ዘርዓይ አሥመራ ከተማ ውስጥ በሚገኝና በሣልሳዊ ኢማኑኤል ስም በተሰየመ ትምህርት ቤት ገብቶ ዘመናዊ ትምህርት ተምሯል። ከዚያም መምህር ሆኖ ማስተማር ጀመረ። ይሁን እንጂ ዘርዓይ ለተማሪዎቹ ስለኢትዮጵያ ደጋግሞ መናገሩና መከራከሩ ለጣሊያኖቹ ምቾት የሚሰጥ ስላልነበር ከሥራው ተባረረ። እርሱ ግን ‹‹ገብረሚካዜላውያን›› የሚባል ማኅበር አቋቁሞ ኢትዮጵያ በጠላት እጅ ስለወደቀች ሁሉም ሰው በጸሎትም በመንፈስም ከኢትዮጵያውያን ጎን እንዲቆም መቀስቀስ ጀመረ። የኢትዮጰያን መወረር ተቃውሞ በጋዜጣ ላይ ገለፀ።

ከአንድ የኤርትራ ገዢ ዘንድ ቀርቦ ሲጠየቅ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጣሊያንኛና ዓረብኛ መናገር እንደሚችልና ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛና አገውኛ የሚያስጠናው ቢያገኝ መማር እንደሚፈልግም ተናገረ። ሀገረ ገዢውም እንዲህ ዓይነቱን ሰው አሥመራ ውስጥ ከማስቀመጥ ወደ ኢጣሊያ መላክ የተሻለ እንደሆነ በማመኑ፤ ዘርዓይ በመስከረም 1929 ዓ.ም ወደ ሮም ተላከ። በዚያም አንድ የቅኝ ግዛት ሀገር ዜጋ ሊያገኘው የሚገባው ከፍተኛ ደረጃ ተሰጥቶት የአስተርጓሚነት ሥራውን ጀመረ። ይሁን እንጂ ያ ሁሉ ሥጋዊ ምቾቱ ለኢትዮጵያ ነፃነት ከመታገል ሊያግደው አልቻለም።

ሰኔ 7 ቀን 1930 ዓ.ም የኢጣሊያ መንግሥት በዶጋሊ ጦርነት ለሞቱት ጣሊያናውያን የተሰናዳ የመታሰቢያ መርሐ ግብር በሮም ከተማ በአንድ የመንግሥት አደባባይ ላይ አዘጋጅቶ ነበር።

ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም የራስ አሉላ (አባ ነጋ) ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው የመጡትን ጣሊያኖችን ዶጋሊ በተባለ ቦታ ላይ ገጥሞ የጣሊያን ጦር አሰቃቂ ሽንፈት ገጥሞታል። ጣሊያን ለዚህ ክስተት ነበር መታሰቢያ ያዘጋጀች።

ዘርዓይ በዕለቱ ፒያሳ ዲ ፒአሞንቲ በተባለው አደባባይ እንዲገኝ የተደረገው የኢትዮጵያን የጦርና ሌሎች ዕቃዎች ይዞ ለማላገጫነት እንዲቆም ነበር። ዘርዓይ ከያዛቸው እቃዎች መካከል አንዱ ራስ አሉላ ዶጋሊ ላይ ጀብዱ የሠሩበትና በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፎ የተወሰደው ጎራዴ ነበር። ዘርዓይም እቃዎቹን ይዞ እንዲሄድ ከመታዘዙ በቀር ለመሳለቂያነት መቆም እንዳለበት አልተነገረውም ነበር።

ዘርዓይ ፒያሳ ዲ ፒአሞንቲ አደባባይ ሲደርስ እንግዳ ነገር ተመለከተ። ቀደም ሲል አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተተክሎ የነበረው የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ሮም አደባባይ ላይ ተተክሎ አየው። ከሐውልቱ ላይ ሁለት ግልገሎች የምታጠባ የተኩላ ምስል ተቀምጦበታል። በአንበሳው መስቀል ላይ ደግሞ የኢጣሊያ ባንዲራ ተሰቅሏል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መሬት ላይ ተጥሏል። በዙሪያው ተጽፈው ከሚታዩና የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ክብር ከሚነኩ መፈክሮች መካከል አንዱ ‹‹ … የይሁዳ አንበሳን ልጆችሽ እንደፍየል ጭራውን ጠምዝዘው አምጥተው ከእግርሽ ስር ያሰግዱታል …›› የሚል ነበር። በአደባባዩ የተሰበሰበው ሕዝብም እየሳቀና እየጮኸ አንበሳው ላይ ምራቁን በመትፋት ያፌዝና ይሳለቅ ነበር።

ዘርዓይ ደረስ ሁኔታውን በመገረምና በመናደድ ስሜት ሲመለከት ማርሻል ማሪዮ ኢሶን የተባለ የዘበኞች አለቃ ወደ ዘርዓይ ቀርቦ ድርጊቱን መመልከት እንደማይችል ነገረው። በተጨማሪም ማርሻል ኢሶን የዘርዓይን መናደድ ስለተመለከተ ዘርዓይን ከአካባቢው ሊያባርረው ሞከረ። ዘርዓይ ‹‹እናንተ የምታዩትን እኔ የማላይበት ምን ምክንያት አለ?!›› ብሎ ጠየቀው። የዘበኞቹ አለቃም የዘርዓይን ጥያቄ እንደድፍረት በመቁጠር ‹‹ … ከእንግዲህ አንበሳ የለም! ለተኩላዋ ልትሰግድና ልታመልካት ይገባሃል!›› አለው። ዘርዓይ ግን ‹‹አይደረግም!›› አለ። ክርክሩ ከረረ። ማርሻል ኢሶን ‹‹… ከእንግዲህ በኋላ አንበሳው የተኩላዋ አሽከር መሆኑን ልነግርህ እወዳለሁ … ያውም ንጽሕናውን ያሻሽል እንደሆነ …›› አለ። ዘርዓይ በእልህ ተከራከረ። አንበሳው ጣሊያኖችን ከአንድም ሁለት ጊዜ ሰባብሮ ድራሻቸውን እንዳጠፋቸው አስረዳው። የዘበኞቹ አለቃ ‹‹… ከአንበሳው ጀርባ ላይ ወጥታችሁ አሳዩት ቁርጡን ይወቀው!›› የሚል ትዕዛዝ ለወታደሮቹ ሰጠ። ሕዝቡ ጭምር አንበሳው ላይ ለመውጣት ተተረማመሰ።

ዘርዓይ ደረስ ሥራውን የጀመረው በዚህ ሰዓት ነበር። በያዘው ጎራዴ ጣሊያኖችን መጨፍጨፍ ጀመረ። ‹‹… ከእንግዲህ በኋላ አንበሳው የተኩላዋ አሽከር መሆኑን ማመን አለብህ … ተኩላዋን ልታመልካት ይገባሃል…›› ብሎ ያፌዘበትን ማርሻል ኢሶንን ለአንበሳው እንዲሰግድ አድርጎ እጅና እግሩን ክፉኛ አቆሰለው። የሌሎችንም ሬሳ በአንበሳው ስር ጎተተው። ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ እንኳ ለመሸሽ አልፈለገም።

ሮም ተሸበረች። ‹‹ኢትዮጵያ ሰብራ ገብታ የኢጣሊያን ሕዝብ ጨፈጨፈችው … ታጥቀህ ራስህን ተከላከል …›› ተብሎ ታወጀ።

ሁሉም በያለበት ተኩስ ከፈተ። በዘርዓይ ጎራዴና በአደባባዩ ላይ በነበረው ትርምስ ምክንያት ከሞተው ሰው በተጨማሪ ‹‹… ታጥቀህ ራስህን ተከላከል …›› ተብሎ በታወጀው አዋጅ ምክንያት ብዙ ሰው እርስ በርሱ ተጋደለ። የኢጣሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ድርጊቱ ውርደት ስለሆነባቸውና ነገሩን በምስጢር ስለያዙት ስንት ሰው እንደሞተ በውል አይታወቅም። አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች በዕለቱ በጥቂቱ የአምስት ሰዎች አስከሬን ከአደባባዩ ላይ መነሳቱን ሲጽፉ ሌሎች ደግሞ ቁጥሩን እስከ 18 ያደርሱታል። በትርምሱ ምክንያት ብዙ ሰዎች መቁሰላቸው የታሪክ ጸሐፊዎቹን አስማምቷል።

ዘርዓይ ጣሊያኖች ላይ እርምጃ መውሰድ የጀመረው ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ነበር። ሽብሩ ግን እስከ 10 ሰዓት ተኩል ድረስ ቀጥሎ ነበር። ከቀኑ 10 ሰዓት ተኩል አካባቢ ሀገሪቱ ሰላም መሆኗንና ሽብሩ የተፈጠረው አንድ የአዕምሮ በሽተኛ ሕመሙ ተነስቶበት እንደሆነ የሚገልፅ አዋጅ ተነገረ። የአወጁ ቃል ይህ ብቻ አልነበረም። ‹‹… ወደ ፒያሳ ሄዳችሁ እጁን ያዙ!›› የሚል ትዕዛዝም ነበረው። በዚህ ትዕዛዝ ምክንያት የከተማው ሕዝብ እንደገና ወደ አደባባዩ ወጣ።

ዘርዓይ ደረስ ሰውነቱ እንደነብር ተቆጣ። በተኩላዋ ሐውልት ላይ ቆሞ በመናገር ሕዝቡን ዝም አሰኘው። ‹‹ … በየቤታችሁ እየዞርኩ ብዙ ሰው አርድ ነበር። ግን እኔን አስሮ የያዘኝና እዚህ ሲያኮራምተኝ የዋለው የአንበሳው ፍቅር ነው። ደግሞም አሟሟቴ ከአንበሳው ስር እንዲሆንልኝ ፈልጌ ነው። ወንድ ይምጣና ይማርከኝ …›› ብሎ ተናገረ። ከተኩላዋ ላይ ወርዶ አንበሳውን እየዳሰሰ ቆመ።

አውቶማቲክ መሣሪያ የያዙ ወታደሮች በሞተር ሳይክል፣ ከሁለት አቅጣጫ በመምጣት ዘርዓይን ተኩሰው መቱት። ጎራዴውን መዘዘና እንደገና ወደ ሕዝቡ ገሰገሰ። ከተማዋ በተኩሱና በሽሽቱ ምክንያት እንደገና ተረበሸች። ዘርዓይ ቢወድቅም ሊቀርበው የደፈረ ሰው አልነበረም። ጎራዴውን ይዞ ከወደቀበት ተነሳ። መሬት ላይ ወድቆ የነበረውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማንሳት በደሙ ለውሶ አንበሳው ላይ ሰቀለው። ተኩላዋ ላይ የነበረውን የኢጣሊያ ባንዲራ የተሰበሰበው ሕዝብ እያየው አወረደው፤ ቀዳዶ ከመሬት ጣለውና ረገጠው። አንበሳውን እየሳመ ያነጋግረው ነበር። ዘርዓይ ይህ ሁሉ ሲያደርግ ሊያስቆመው የሞከረ ሰው አልነበረም። አሁን ግን ወታደሮቹ ደግመው ተኮሱበት። ዘርዓይም ወደቀ ግን አልሞተም ነበር።

ዘርዓይ ይህን ሁሉ ሠርቶ፤ በስድስት ጥይት ተመትቶ መትረፉ ጣሊያኖችን አበሳጫቸው፤ አስደነገጣቸውም። በወቅቱ በሮም ከተማ ውስጥ ከነበሩት ሐኪም ቤቶች ሁሉ የተሻለ ወደሚባለው የሕክምና ተቋም (ቀዳማዊ ኡምቤርቶ ፖሊክሊኒክ) አስገቡትና ሕክምና ተደርጎለት አገገመ። ሐምሌ 15 ቀን 1930 ዓ.ም ቤኒቶ ሙሶሊኒ በዘርዓይ ጥቃት የቆሰሉትን ለመጠየቅ ሐኪም ቤት ሲደርስ ማርሻል ማሪዮ ኢሶን ሞቶ እየተገነዘ ነበር። ለኢሶን ያመጣለትን ኒሻን አስቀምጦ በከፍተኛ ቁጣ ዘርዓይ ወደተኛበት ክፍል ገባ። አገግሞ ስላገኘው የበለጠ ተናደደ። ‹‹… አንተ ነህ ሮምን የደፈርካት?›› ብሎ ጠየቀው። ሙሶሊኒም ዘርዓይ በሚገባ ታክሞ እንዲድን ለሐኪሞቹ አደራውን ሰጠ። ዘርዓይን በሞት መቅጣት የኢጣሊያን ስም በማይረባ ነገር በመላው ዓለም መበተን መሆኑን ገልፆ፤ በዳነ ጊዜ በቃልም በጽሑፍም ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ የአዕምሮ ሕመምተኛ መሆኑን የሚገልፅ ማስረጃ እንዲዘጋጅና ዘርዓይም ሕመምተኛ መሆኑን እንዲያምን እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጠ።

ፕሮፌሰር ፋውስቶ ኮንስታንቲኒ የተባለው ሐኪም የሙሶሊኒን ትዕዛዝ ለማስፈፀም ላይ ታች አለ። ለብዙ ቀናት አግባብቶ አንድ ወረቀት እንዲፈርም አቀረበለት። ደብዳቤው ስለተደረገለት ሕክምና አመስግኖ ‹‹ በ500 ወታደሮች አደባባይ ላይ በድንገት ታምሜ በሰዎች ሕይወት ላይ ስላደረስኩት በደል ይቅርታ እጠይቃለሁ። በስድስት ጥይቶች የተመታው ሰውነቴና አንጎሌም ድኖ በቅርብ ቀን ለመውጣት ሐኪሙ ተስፋ ሰጥቶኛል …›› የሚሉ ሀሳቦችን ያካተተ ነበር። ዘርዓይ ደብዳቤውን ከሐኪሙ ነጥቆ በመቀዳደድ ፊቱ ላይ በተነበት። ቀደም ሲል ስለዚሁ ጉዳይ በተደረገ ክርክር ላይ ዘርዓይ ‹‹… በእናንተ አፍ እውነት የሚነገረው መቼ ይሆን?›› ብሎ በድፍረት የጠየቀው ፕሮፈሰር ኮንስታንቲኒ የሐፍረት ማቅ ለብሶ ወጣ፤ ድጋሚ ወደ ዘርዓይ አልተመለሰም።

ፕሮፌሰር ኮንስታንቲኒ በድጋሚ እርሱ በአካል ወደ ዘርዓይ ባይመለስም ጥረቱን ግን አላቋረጠም ነበር። ሁለት ኢትዮጵያውያንን (አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ደጃዝማችና አንድ መነኩሴ) ላከበት። ሁለቱ ሰዎች የዘርዓይን አቋም ለማስለወጥ ብዙ ደከሙ። የኢጣሊያን መንግሥት ኃያልነትና የእርሱን ወጣትነት እያገናዘቡ ብዙ አባበሉት። እርሱ ግን ሀሳቡን መለወጥ አልፈለገም። ወደ ደጃዝማቹም ዞሮ ‹‹… እንደርስዎ ያለ ሰው የማንም ጭነት ማጓጓዣ መሆን አልነበረበትም›› አላቸው። በተጨማሪም ‹‹ ለእነርሱ ክብርና ለእነርሱ ወረራና መስፋፋት ከቶ የእናንተ አጠንጣኝነት ምንድን ነው? ሲል ጠየቃቸው። ደጃዝማቹ ግን መልስ አልነበራቸውም። ዘርዓይ ቀጥሎም ‹‹እንስሶች እንኳ ጌታቸውን ይወዳሉ። እናንተ ግን ቅሌታችሁን ተሸክማችሁ ትዞራላችሁ!›› ብሏቸው ወደ መነኩሴው ዞረ።

‹‹የእግዚአብሔር እንደራሴ መስለው በጥቁር ጨርቅ ትምነሸነሻላችሁ። የሰውን የእኩልነት ኑሮ ለማጥፋት ከላይ ተልካችሁ የመጣችሁ መቅሰፍቶች ናችሁ! ቅስናዎን ይተውት! ተራ መሐይም መስለው እንደሌሎች ባንዳዎች ቢያገለግሉ ይሻላል፤ ከአጠገቤ ውጡ!›› ብሎ አባረራቸው። ዘርዓይ አቋሙን እንደማይቀይር ስለታወቀ በድጋሚ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አልቀረበለትም።

አንድ ጊዜ መደበኛ ፍርድ ቤት ሌላ ጊዜ የጦር ፍርድ ቤት ሲያመላልሱት ቆይተው ታሰረ፤ በዚያው በእስር ቤት እያለ በ1937 ዓ.ም ሕይወቱ አለፈ። አስክሬኑም ወደ ኤርትራ መጥቶ በሐዘጋ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል።

እነሆ ይህን ጀግና ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You