
-ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች ነው
አዲስ አበባ፦ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የስደተኞች አያያዝ እውቅናን ከመስጠት ባለፈ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የስደት ተመላሾች አገልግሎት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የስደተኞችን አያያዝና አስተናጋጅ ማህበረሰቦችን መደገፍ ላይ ያተኮረ ከፍተኛ ደረጃ ውይይት ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በወቅቱ እንዳሉት፤ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ተቀብላ በማስተናገድ የረጅም ዓመት ታሪክ አላት። ይሄንን ታሪክ አሁንም አጠናክራ እየቀጠለች ነው። ለስደተኞች የሚደረገው ድጋፍ በወረቀት ላይ ብቻ ታቅዶ የሚቀር ሳይሆን በተጨባጭ ምድር ላይ ወርዶ እየተሠራበት የሚገኝ ነው ብለዋል።
በዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችን አሳታፊና አካታች የሆነ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት፣ የትምህርት፣ የጤና የማህበራዊ እና የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ መንግሥት በትኩረት እየሠራ እንዳለ ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
ስደተኞችን በማካተት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ነገር ግን አሁንም ስደተኞቹ የሚገኙባቸው መጠለያዎች ከከተማዎች የራቁ እና በድንበር አካባቢ የሚገኙ በመሆናቸው የመሠረተ ልማት ችግሮች አሉባቸው ብለዋል። ይሄንንም ለማሻሻል የዓለምአቀፍ ማህበረሰቡ በኢትዮጵያ በኩል የሚደረጉ ጅምሮችን ከማድነቅ ባለፈ ርዳታ እና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለስደተኞች የተሻለ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት የሚደረጉ ድጋፎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የስደተኞች ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች መኖራቸውን ገልፀው፤ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሴቶች፣ ህፃናት እና የእድሜ ባለፀጋዎች እንደሚገኙ አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስደተኞች መብትና ጥበቃን ማስከበር የሚያስችል የሕግ ማሕቀፍ በማዘጋጀትና በ10 ዓመት የልማት ግቧ ላይ በማካተት ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኑንም አብራርተዋል። በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የስደተኞች አካታች ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ ሊሆን የሚችል መሆኑንም አንስተዋል።
የስደተኞች ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብር መፍጠር ይገባል ነው ያሉት። የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ስደተኞች ለሚያገኙት አገልግሎት የፋይናንስ፣ የቴክኒክ እና ሌሎች አይነት ድጋፎችን በማድረግ ሃላፊነት መወጣትን እንዲጋሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚስተር ፊሊፖ ግራንዲ በመድረኩ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምትሰጠውን አገልግሎት አድንቀው የአካታች ፖሊሲዎቿ ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ኮሚሽነሩ ወደ ኢትዮጵያ በርካታ ጊዜዎች መምጣታቸውን ተናግረው፤ በስደተኞች አያያዝ እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በርካታ ለውጥ መምጣቱን አብራርተዋል። በማካተት ፖሊሲ ትግበራዎች ለውጥ መጥቷል ማለት ግን ምንም ችግር የለም አለማለት መሆኑንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ላሉ ሀገራት ጎረቤት በመሆኗ በርካታ ስደተኞች ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ እና ጦርነት የተፈተነች ቢሆንም በስደተኞች አያያዝ ላይ መሻሻል መኖሩን ጠቁመዋል። ስደተኞችም ከርዳታ ጠባቂነት በመውጣት የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩ መደረጉ የሚበረታታ መሆኑንም አብራርተዋል።
ስደተኞችን የማካተት ፖሊሲም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እና ድርጅቶችም ለዘርፉ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ባለድርሻ አካላትም እንዲሁ የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኞችን ተቀብሎ እየሰጠ ያለው ድጋፍና እንክብካቤ አድናቆት የሚቸረው መሆኑን ተናግረዋል።
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲን፣ የገንዘብ ሚኒስትር ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የትምህርት ሚኒስትር አማካሪ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወትን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም