“የኳሱ ጌታ!”

“1975 ዓ.ም ለሙሉጌታ ከበደ ጥሩ ዓመት ነበር። በዚያኑ ዓመት ለብሄራዊ ቡድን ተመረጠ። የደሴ ከተማ ነዋሪም በሙሉጌታ መመረጥ ተደሰተ። በዚያን ዓመት ፔፕሲ የኢትዮጵያ ቻምፒዮናነትን ክብር ተቀዳጀ። የወሎ ምርጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ትቅደም ዋንጫን አነሳ። የማሸነፊያዎቹን ግብ ያስቆጠረውና ለድሉ ማማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ ሙሉጌታ ነበር። የሀገር ጥሪ ስለመጣለት ለአዲስ አበባው ጉዞ የሽኝት ግብዣ ቤተሰቦቹ አዘጋጁለት። ጓደኞቹና አድናቂዎቹ እንዲሁም የእናቱ እድርተኞች በተገኙበት ሞቅ ባለ ሁኔታ ተደገሰ። ምርቃቱም ተዥጎደጎደ…” በማለት የኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ነጋሪው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) በአንድ ወቅት ‹ሰውየው› በሚል ባስነበበው መጣጥፍ የኳሱ ጌታ ታላቅ ተጫዋች የሆነበትን ጉዞ ሲተርክ።

ሙሉጌታ ለታላቅ ሀገራዊ ጥሪ መንደሩን ቢሰናበት እናቱ እንዲለያቸው እንዳልፈለጉ የሚነግረን ሊብሮ ታላቁ ተጫዋች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የገጠመውን ፈገግ የሚያደርግ ገጠመኝ ብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ያስታውሱታል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን “አሸብር፣ ወለዬው፣ ተንኮሉ” በሚል ቅፅል ስሞቹ ያውቁታል። ከመንግሥቱ ወርቁ በኋላ የተፈጠረ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ንጉሥ አድርገው የሚመለከቱትም ጥቂት አይደሉም። በርካቶችም “እስካሁን ምትክ ያልተገኘለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ንጉሥ” እንደሆነ ይከራከራሉ። “የኳሱ ጌታ” ያሰኘውን ድንቅና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባለተሰጥኦ ተጫዋች መሆኑ ግን ሁሉንም ያስማማል።

ከምንጊዜም የኢትዮጵያ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሙሉጌታ ከበደ በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ዓመት ከመጫወቱ በተጨማሪ ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለደሴ ፔፕሲ እና ለወሎ ምርጥ የተጫወተ ሲሆን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሴካፋ ዋንጫን፣ በክለብ እና በግልም በርካታ ሽልማቶችን ማሸነፍ የቻለ ድንቅ ተጫዋች ነበር።

ለአስራ ሦስት ዓመታት አቋሙ ሳይዋዥቅ በወጥ ብቃቱ፣ በድንቅ ችሎታው እንዲሁም በረቂቅ ጥበቡና በተንኮሉ ጭምር ደጋፊዎቹን ብቻ ሣይሆን የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች እንዲሁም እግር ኳስን የሚወዱትን ሁሉ ሲያስቦርቅ፣ ሲያስጨፍር በደስታ ሲያስለቅስ እንደነበር በዘመኑ የነበሩ ሁሉ ይመሰክሩለታል።

በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ በድንቅ ችሎታው የማይነቃነቅ ሀውልት ለመትከል የበቃውና ሁሉም በአንድ ድምፅ “ተተኪ ያልተገኘት የኳሱ ጌታ ነው” በማለት የሚያወድሱት ሙሉጌታ ከበደ፣ በወጥ አቋሙ ለአስራ ሦስት ዓመታት በአንድ ክለብ የፈረሰኞቹን ማልያ ለብሶ በመጫወት ስሙን በወርቅ ቀለም ያፃፈ ተነግረው የማያልቁ አስገራሚ ታሪኮች ያለው ተጫዋችም ነው፡፡

የሙሉጌታን ድንቅ የኳስ ጥበብ “ቃላቶች የመግለፅ አቅም እንኳን የላቸውም፤ እሱ የእግር ኳስ አምላክ ያለ ስስት ለኢትዮጵያ የሰጣት ምትሀተኛ ተጫዋች ነው” በማለት በርካቶች ዛሬም ድረስ ያወድሱታል።

ሙሉጌታ የተወለደው በ1959 ዓ.ም መሆኑን በሕይወቱ ዙሪያ የተፃፉ ድርሳናት ያስረዳሉ። የትውልድ ቦታው ደግሞ ደሴ ከተማ ሆጤ ሠፈር ነው። ደሴ ከፍተኛ 2፣ ወሎ ፔፕሲ እና ኒያላ የተጫወተባቸው ክለቦች ክለቦች ቢሆኑም ብዙ ታሪኮችን መሥራት የቻለው ከ1977 እስከ 1989 በተጫወተበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው።

በ1973 ዓ.ም ከወሎ ምርጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተሰፋ ቡድን የተመረጠው ሙሉጌታ፣ ሦስት ጊዜ ኮከብ ጎል አግቢና ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው። የኮከብ ግብ አግቢነት ክብር የተቀዳጀው በ1977፣ 1978 እና 1986 ሲሆን፣ የኮከብ ተጫዋችነት ክብር ያገኘው በ1978፣ 1980 እና 1982 ነበር።

በነዚህ ድንቅና ስኬታማ ዓመታት ሰባት ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮናን ዋንጫ፣ ስድስት ጊዜ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ፣ አንድ ጊዜ የጥሎ ማለፍ ዋንጫና አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ትቅደም ዋንጫ አሸናፊ በመሆን በስኬትና በዋንጫ የተንቆጠቆጠ የተጫዋችነት ዘመን አሳልፏል። የኳሱ ጌታ የተጫዋችነት ዘመኑን ከደመደመ በኋላም ወደ አሠልጣኝነት ሕይወት ጎራ ብሎ ነበር። ተጫውቶ ባሳለፈበት ኒያላ የኢንስራክተር አብርሃም መብራቱ ረዳት አሠልጣኝ ሆኖ ሠርቷል። የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ዋና አሠልጣኝ ሆኖም አገልግሏል።

ከባለቤቱ ወይዘሮ ዘይቱና አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጅ ያፈራው ታላቁ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋች ሙሉጌታ ከበደ፣ ባደረበት ህመም ባለፈው ሰኔ 04-2017 ዓ.ም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ የህልፈተ ሕይወቱ ዜና ተሰምቷል። ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 05-2017 ዓ.ም የማይረሱ ታሪኮች በሠራበት የአዲስ አበባ ስታዲየም የክብር አስክሬን አሸኛኘት ተደርጎለታል። በእለቱ የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን ጨምሮ የስፖርት ቤተሰቡ፣ ጓደኞቹ፣ አድናቂዎቹና ቤተሰቡ የተገኙ ሲሆን ሥርዓተ ቀብሩ በኮልፌ የሙስሊም መካነ መቃብር ተፈፅሟል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You