በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የታሪክና የዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብዱ መሃመድ አሊ ትውልዳቸውና ዕድገታቸው ደሴ ሲሆን ከአማራና ትግራይ ወላጆች እንደተገኙ ይናገራሉ፡፡ ሁለቱንህዝቦች እንዲህ ሲሉም ገልጸዋቸዋል፤ ‹‹አንድ ትግራዋይ ለእኔ ፊቱን ያዞረ አማራ ነው፡፡ አንድ አማራ ደግሞ ፊቱን ያዞረ ትግራዋይ ነው፡ ፡
ምክንያቱም ሁለቱ ህዝቦች በደም፣ በቋንቋ፣ በእምነት በመልከዓ ምድርና በስነ ልቦና እጅግ የተቀራረቡ፤ በሁለት ስያሜዎች የሚጠሩ አንድ ህዝቦች ናቸው፡፡›› እንደ ዶክተር አብዱ ሁሉ ስለሁለቱ ህዝቦች የዘመናት የባህልና የታሪክ ተጋምዶ በማሳያነት የሚጠቀሱ ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድም የአማራና የትግራይ ክልል ሀገር ሽማግሌዎች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት እንዳብራሩት የዘመናት አብሮነት ያላቸው ህዝቦች በሚኖሩባቸው በሁለቱ ክልሎች መካከል የሚታዩ እሰጣገባዎችናውጥረቶች የህዝቡን አብሮነትና አንድነት የሚገ ልጹ አይደሉም፡፡ ‹‹ሁለቱ ህዝቦች የአንድ እናት ልጆች ናቸው፤ በስጋና በአጥንት የተሳሰሩ ናቸው፡፡
ትስስራቸው ደግሞ በመልካም ጊዜ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በችግር ጊዜ ጭምር ያልተቋረጠና ሊቋረጥምየማይችል ነው» የሚሉት በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ራያ አላማጣ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የሀገር ሽማግሌ አቶ አረፋይነ ታረቀ ናቸው፡፡ አቶ አረፋይነ እንደሚሉት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው ቁርኝት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በጋብቻ የተሳሰሩና ዛሬም በጋብቻ እየተሳሰሩ ያሉ ከመሆናቸውም በላይ የደስታና የችግር ጊዜያቸውን በጋራ ያሳለፉ ናቸው፡፡ የተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት ሁለቱ ህዝቦች በጋራ አሳልፈዋል፡፡ በ1980ዎቹ አካባቢ በነበረው ድርቅ ምክንያት ወደ አማራ አካባቢ ሄደው የችግር ጊዜያቸውን አሳልፈው መመለሳቸው ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡
በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የሀገር ሽማግሌ አቶ መኳንንት ደሳለኝ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ህዝቦቹ የሚያመሳስላቸው በርካታ ነገሮች ያሏቸው ናቸው፡፡ ከቋንቋ ልዩነት ውጪ ምንም የሚያለያያቸው ነገር የለም፡፡ እጅግ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ አኗኗራቸው እንኳን ሲታይ ተሰባጥረው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን እንደሀገር ለማቆየት መላው ኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት መክፈላቸውን የሚያስታውሱት አቶ መኳንንት፤ በተለይም የአማራና ትግራይ ህዝብ የበዓድ ሀገራት ወራሪዎች በሚመጡበት ወቅት በጋራ ሆነው አሳፍረው በመመለስ ለብዙ ዘመናት የቆየ ታሪክ አላቸው፡፡
እንደ አቶ መኳንንት ማብራሪያ፤ሁለቱ ህዝቦች በአንድ ገበያ በመገበያየት አንዱ የሌላው ከሌላው ይሸምታል፡፡ በተለይም ደባርቅ፣ ዳባትና ሽሬ አካባቢዎች ነዋሪዎች እጅግ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ትስስር ነው የነበረው፡፡ አሁን ግን ንግዱ ተቋርጧል፡፡ ይህ ለሁለቱም ህዝቦች ጥሩ አይደለም፡፡ ይህ የንግድ ግንኙነት መቋረጥም አልነበረበትም ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡ የንግድ ትስስሮቹ መቀጠል አለባቸው ይላሉ፡፡ አቶ አረፋይነ እንደሚናገሩት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማይረቡ ምክንያቶች በሁለቱ ክልል አመራሮች መካከል የሚታየው እሰጣገባ ለዘመናት የቆየውን አብሮነት የሚገልጽ አይደለም፡፡ ሁለቱን ክልሎች የሚመሩ አካላት የህዝቡን የዘመናት አንድነት ወደ ጎን ትተው በማይረቡ ጉዳዮች ሲነታረኩ ማየትም አሳፋሪ ነው፡፡
በሁለቱ ክልል አመራሮች መካከል የሚታዩ ፍትጊያዎች ለሁለቱ ህዝቦች ምንም ፋይዳ የላቸውም፡፡ ‹‹ሁለቱም ህዝቦች የሚፈልጉት ሰላም፣ ልማት፣ የአስተዳደር ወሰኖች ሳያግዳቸው አንዱ ከሌላው አካባቢ ሄዶ መገበያየት ነው›› የሚሉት አቶ አረፋይነ፣ ፖለቲከኞች በፈጠሩት ስህተትና መቃቃር ህዝቡ ሰላሙንና አንድነቱን ማጣት ስለሌለበት የሁለቱ ክልል ፖለቲከኞች ፖለቲካቸውን ከህዝቡ ጋር ሳያገናኙ እዚያው ሊጨርሱት ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ አቶ አረፋይነ ማብራሪያ፤ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች መሥራት ያለባቸውን ሥራዎች አለመሥራታቸው በክልሎቹ መካከል አሁን ለሚታዩ ችግሮች መንስኤ ነው፡፡ ሁለቱ ተገናኝተው ህዝቡ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መፍትሔ እየሰጡ ቢሄዱ፤ አሁን የሚታየው ችግር አይፈጠርም ነበር፡፡
አሁንም ቢሆን ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሥራት ችግሩ እንዲፈታ መሥራት አለባቸው፡፡ ‹‹የትግራይና አማራ አባቶቹና አያቶች አብሮነትን፣ ጠላትን በጋራ መመከትን፣ መከባበርን፤ አብሮ መብላትና አብሮ መጠጣት፤ በችግር ጊዜ አንዱ ሌላኛው ጋር ተጠግቶ ማሳለፍን ነው ያስተማሩን›› የሚሉት አቶ አረፋይነ ፣የአሁኑ ወጣቶች አባቶቻቸውና አያቶቻቸው ያቆዩዋቸውን እሴቶች ከሚጎዱ ነገሮች መቆጠብ አለባቸው፡፡ የአያቶችን ታሪክ ወደ ጎን በመተው ሁለቱን ህዝቦች የሚያራርቁ ነገሮችን ከመፈጸም ሊቆጠብ ይገባል፡፡ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳ ቁጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አቶ መኳንንት እንደሚያብራሩት በአ ሁኑ ወቅት በሁለቱ ክልሎች መካከል ያሉ መወነጃጀሎችና መግለጫዎች የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች የዘመናት አብሮነት ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም፡፡
ስለሁለቱ ህዝቦች የሚነገረውና የሚሰማው በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረውን ግንኙነት አይገልጽም፡፡ የሚነሱ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል የነበሩ ግንኙነቶች እንዳይቀጥል የሚደረጉ ጥረቶች መቆም አለባቸው፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት ህዝቡን ማዕከል ያደረገ ጥረት መደረግ አለበት የሚሉት አቶ መኳንንት፤ ህዝብን ሳያሳትፉ አመራሮች ብቻ ተነጋግረው ችግርን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ያለውን ችግር አይፈታም ይላሉ፡፡ ሁለቱ ክልሎች ችግሮች በመግለጫ ይፈቱ ይመስል መግለጫ በማውጣት ከመጠመድ ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ይገባቸዋል፡፡ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት፤ ከፌዴራል መንግሥት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከመላው ህዝቡ ጋር በመሆን፤ ችግሩን እስኪፈታ ህዝቡ ግን ግንኙነቱን መቀጠል አለበት፡፡ ፖለቲከኞች የህዝብን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ችግሮችን እየፈቱ መሄድ አለባቸው ሲሉም ይመክራሉ፡፡ የታሪክና የዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪው ዶክተር አብዱ መሃመድ እንደሚሉት ሁለቱ ህዝቦች የሚያቀራርባቸው በርካታ ነገሮች ያላቸው አንድ አካል፤ አንድ አምሳል ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በልሂቃን መካከል ያለው አለመግባባት የችግሩ መንስኤ ሆኗል፡፡
ሁለቱ ክልሎች በሚሰጡት መግለጫዎች ሁለቱንም ክልሎች የሚያስተዳድሩ አካላት የቡድን ውጥረት ውስጥ መሆናቸውን አመላካች ናቸው የሚሉት ዶክተር አብዱ፣ መግለጫዎቹ ሌላ ውጥረት ከመፍጠር ውጪ ለክልሎቹ ህዝቦች መቀራረብ ምንም የማይፈይዱ ናቸው ይላሉ፡ ፡ በሁለቱ ህዝቦችና ክልሎች መካከል ያለውን ልዩነት እያሰፉ እንዳይሄድ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም በጋራ መሥራት አለበት፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ልዩነቶችን እያጦዙ መሄድ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ነው›› የሚሉት ዶክተር አብዱ፤ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ፍጥጫ ውስጥ በመቆየት አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ልዩነቶቻቸውን በይደር ቢያስቀምጡ ይመረጣል ይላሉ፡፡ በይደር የሚቀመጡ ጉዳዮችን በቀጣይ ከሚደረገው ምርጫ በኋላ በዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ተቋማት አማካይነት እልባት እንዲያገኙ ቢደረግ የተሻለ ነው ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በመላኩ ኤሮሴ