የግብርና ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ጉልህ ሚና ተጫውቷል

አዲስአበባ፡- የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ እና ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ ፖሊሲዎችን ለማውጣት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ጉልህ ሚና መጫወቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆልቲካልቸር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን 13ኛው የግብርና ልማት አጋርነት ፎረም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ በግብርና ዘርፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ውይይቶች ዘመኑን የሚዋጁ ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት ግብዓት ሆነዋል።

የገጠር ልማት ፖሊሲ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑ መከለስ ባስፈለገበት ወቅት ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሃሳቦቻቸው በፖሊሲ የተደገፈ መሆኑን ለማረጋገጥ ያለመ ውይይት መደረጉን በማንሳት፤ ይህም ዘመኑን የዋጀ ፖሊሲ እንዲወጣ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉ አስረድተዋል።

የኮንትራት እርሻ አዋጅ እና እሱን የሚደግፉ መመሪያዎች ከእዚህ በፊት እንዳልነበር አስታውሰው፤ ብዙ ጊዜ ባለድርሻ አካላት ጥያቄ ሲያነሱ የነበረበት ሁኔታ ነበር ብለዋል። ይህን መሠረት በማድረግም ለመጀመሪያ ጊዜ የኮንትራት እርሻ አዋጅ ተዘጋጅቶ እንዲጸድቅ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

የባለብዙ ተዋናይ የኤክስቴንሽን አገልግሎት እና አስተዳደር አዋጅ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ እና የብራዚልን ልምድ ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ ባካተተ መልኩ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን አስረድተዋል።

የባለድርሻ አካላትን ሃሳብ መሠረት በማድረግም ከፖሊሲዎች ጋር የሚጣጣም ስትራቴጂ እቅድ የመንደፍ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል። ነገር ግን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ብቻ መዘጋጀቱ ብቻ ግብ ስላልሆነ፤ ስትራቴጂዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ እቅዶችም እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሰው ኃይል እስከ አየር ንብረት በርካታ የግብርና ሀብት ያላት መሆኗን ጠቁመው፤ እነዚህን በአግባቡ ተጠቅሞ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደ ቁልፍ ሥራ መወሰዱን ገልጸዋል። ይህን ለማሳካት ከምርምር ጀምሮ እስከ ታችኛው እሴት ሰንሰለት የሚሳተፉ አካላት ድርሻቸው ከፍተኛ ነው ሲሉ አመላክተዋል።

ከኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ግብርና እንደሆነ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ዘርፉ በሚፈለገው ልክ አለማደጉን ተናግረዋል። ይህን ለማሳደግ በሚሠራው ሥራ በተመሳሳይ መልኩ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር እርሻና ሆርቲካልቸር ኤክስቴንሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የኔነሽ ኤጉ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ 13ኛው ፎረም የተለያዩ የግብርና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተናጠል የሚሠሩ ሥራዎችን በቅንጅት መሥራት በሚያስችል መንገድ ውይይት የተደረገበት ነው።

መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተናጠል በሚሠሩበት ጊዜ የሀብት ብክነት፣ የጉልበት ድግግሞሽ እና የተለያየ መልዕክት ለአርሶ አደሩ የሚተላለፍ በመሆኑ አርሶ አደሩን ግራ የማጋባት ነገር እንዳለ ጠቅሰው፤ ነገር ግን በቅንጅት መሥራት ይህን ችግር ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ፎረሙ ከተቋቋመ በኋላ የተለያዩ ፖሊሲዎች እንዲከለሱ፤ አዳዲስ ፖሊሲዎች እንዲወጡ እና የተቋማት መዋቅር እንዲለወጥ ስለመደረጉ፤ እንዲሁም የአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት፣ የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር ፍላጎት ስለመጨመሩ ሥራ አስፈጻሚዋ ወይዘሮ የኔነሽ ገልጸዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You