በአንድ አገር የሚካሄድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነው የሚባለው የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ቀንና ድህረ ምርጫ ያሉ ሂደቶች ነፃ፣ ፍትሐዊና ተወዳዳሪ ባህሪያትን የተላበሰ ሲሆን ብቻ ነው። የማንኛውም ሀገር የመንግሥት ሥልጣን ሊመነጭ የሚገባውም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ በአብላጫ ድምፅ የሕዝብ ፈቃድ ማግኘት ሲቻልም ነው።
ዴሞክራሲ በሰፈነበት አገር ምርጫ ከጦር መሣሪያ በላይ ይፈራል። ይከበራልም። ምክንያቱም ሕዝብ በድምጹ የሚፈልገው ፓርቲ ሲመርጥ የማይፈልገው ደግሞ ድምጹን የሚነሳበት በመሆኑ ነው፡፡ ማንኛውም ምርጫ የሕዝብን ፍላጎት መጠየቂያ ነፃ የሆነ የዴሞክራሲ መንገድ እንጂ የመርሀ ግብር ማሟያ አይደለም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ለአገርና ለሕዝብ የቆመ፣ ነፃና ሕጋዊ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት ያለውና በምርጫ መሸነፍና ማሸነፍ እንዳለ የሚገነዘብ መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲ መኖርን ይጠይቃል። ይህ ካልሆነ ግን ምርጫ ፌዝ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ አገራዊ ምርጫ ታካሂዳለች። ከ1987 ወዲህም እስካሁን ለአምስት ጊዜያት አገራዊ ምርጫ አካሂዳለች። ቀጣዩና ስድስተኛው ምርጫ ደግሞ በቀጣዩ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን ምርጫ ለማስተናገድም ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል። ይህን ምርጫም ካለፉት በተሻለ ፍትሃዊ፣ ተአማኒና ገለልተኛ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ መንግሥትም ይህን ለማስፈፀም ዝግጁ ከመሆንም በላይ ቆራጥ አቋም ይዟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም መንግሥት ሁሉም የሚያምንበትና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ ለማካሄድ ብሎም ተዓማኒ የሆነ የምርጫ ተቋም እንዲኖር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል። የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩል ሜዳ ላይ እንዲወዳደሩና ምርጫውን ተዓማኒ ማድረግ የሚያስችል ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ለማቋቋም ወሳኝ እርምጃን ተራምደዋል።
ብዙ ጊዜ ስለ ምርጫ ስናነሳ ቶሎ የሚታየን የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ የመሆን ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም ፓርቲና የአገሪቱን ሕዝብ በሚያስማማ መልኩ የቦርዱን የበላይ አመራር እንዲሆኑ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ሰሞኑን ሾሟል፡፡ እኝህ ሰውም ገለልተኛ፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ በተግባርም ዋጋ የከፈሉ ናቸው፡፡ ይህም የሚቀጥለው ምርጫ ከዚህ ቀደምት ምርጫዎች በተለየ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም ቀደም ሲል የነበረውን ጥርጣሬ በእጅጉ የሚቀርፍና የነበረንን የምርጫ ባህል ከመሰረቱ የሚቀይር መሆኑም ታምኖበታል።
ይህ ከሆነ ታዲያ ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ገዢውን ጨምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በጋራም ሆነ በተናጠል የየበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው እርግጥ ነው።
እንደ እኔ እምነት መጪውን ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከሁሉ ቀድሞ ከወዲሁ ማሸነፍና መሸነፍን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁነት ያስፈልጋል። ነፃ ምርጫ ተደርጎ ማንም ቢያሸንፍ ውጤትን የመቀበል ዝግጁነት የግድ ይላል። መጀመሪያ ፓርቲዎች አገርና ሕዝብ መምራት እንችላለን ከማለታቸው በፊት ማንኛውንም ውጤት የመቀበልና ለሕዝብ ድምጽ ውጤት ተገቢውን ክብር የሚሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ የምርጫ ዴሞክራሲያዊ ባህልን መልመድም ግድ ይላቸዋል።
የጥፋትና የበቀል አካሄድ ለአገር ቀርቶ ለግለሰብ እንኳን ፋይዳ የለውም፡፡ ስለዚህ የአገር ጉዳይን አንግቦ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ አሁን ባለንበት ዘመን ሊከተለው የሚገባው ሰላማዊ የትግል ስልት ብቻ ሊሆን እንደሚችል መካሪ የሚሻው አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ሂደቱ ጥሩ ቢሆንም የኋላ ኋላ «ድምጽ ተጭበ ርብሯል» በሚል በተፈጠረው እሰጣ አገባ ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት መንስኤ ሆኗል፡፡
በመሆኑም ቀጣዩንም ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሥልጣን ሊይዙ የሚችሉት የሕዝቡን አመኔታ ሲያገኙ ብቻ መሆኑንም መረዳት ይኖርባቸዋል። አንድ ፓርቲ ሥልጣን የሚያዘው በማጭበርበርና በጉልበት ሳይሆን አብላጫውን የሕዝብ ድምጽ ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡
በመሆኑም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ሰላምና እኩልነት እንዲሰፍን ማድረግ ይገባል፡፡ በተለይ በተናጠል፣ በግንባር፣ በቅንጅትና በውህደት ገዢውን ፓርቲ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጊዜያዊና ስሜት ኮርኳሪ ድርጊቶች መራቅ አለባቸው፡፡ አገርም በስሜት እንደማትመራ ጠንቅቀው ማወቅ ይኖርባቸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚፈጥሩትን ትርጉም የለሽ የፖለቲካ ሽኩቻ ሊያስወገዱም ይገባል። ቀጣዩ ምርጫ ሲታሰብ ፓርቲዎቹም ከነቀፌታና የትናንቱን እያነሱ ከመውቀስ ተላቀው ወደ ፊት የሚያሻግሩ ሃሳቦች ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በግልጽ በማስቀመጥ የሕዝብን ኑሮ የሚለውጡ አጀንዳዎች ላይ ቢጠመዱ ለእነሱም የተሻለ ይሆናል፡፡ ሕዝቡ በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል የሚል አስተሳሰብ እንዲኖረው ማድረግም ቀጣይ የፓርቲዎች ዋነኛ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
አንድ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር መጪው ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት በተሻለ ዴሞክራሲያዊ ባህልን መሠረት ጥሎ የሚያልፍ መሆን እንዳለበት ነው። ይህ ደግሞ ፓርቲዎች አለን የሚሉትን ልዩነቶች በግልጽ በማስቀመጥ፣ ልዩነታቸውን አክብረው በጋራ አጀንዳ ተባብረው በመስራትና እርስ በራሳቸው ተጠላልፈው ላለመውደቅ በሚያደርጉት ጥረት ይወሰናል። በርእዮተ ዓለም ከሚለያዩት ፓርቲዎች ጋር ያላቸው አመለ ካከትና አተያይም መልካም መሆን አለበት። በተለይ መላውን ሕዝብ በዚህ አቅጣጫ እንዲጓዝ ለማስቻል የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ሊሸከሙት የሚገባው አገራዊ ኃላፊነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡
ከዚህ በፊት በተካሄዱ ምርጫዎች ፓርቲዎች ከሚነቀፉባቸው ጉዳዮች አንዱ የአባላቱ የሥነ ምግባር ችግር ነው። በመሆኑም ቀጣዩም ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ አባላቶ ቻቸውን ሥነ ምግባር የተላበሱ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
«ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ» እንዳይሆን ምርጫው ሲደርስ ይራዘምልን አሊያም ምርጫው ልክ አይደለም የሚሉ አቤቱታዎችና ቅሬታዎችን ከወዲሁ ለማስወገድ የሚያስችሉ ሥራዎችን መስራት አለባቸው፡፡በተለይ ከውጭ የገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቦርዱን እውቅና አግኝተው መንቀሳቀስ አለባቸው ። ፓርቲዎች ምርጫውን በብቃት ለማከናወን የፋይናንስ አቅማቸውን ማጠናከር ሁነኛ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ ለዚህ እውን መሆን መስራት እንዳለባቸውም ሊዘነጋ አይገባም።
በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ጣምራ ዜግነት ስለማይፈቀድ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው የፖለቲካ መሪዎች በሀገሪቱ ምርጫ ለመወዳደር የሌላ ሀገር ዜግነታቸውን መተው አለባቸው፡፡
በምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚፎካከሩት ከገዢው ፓርቲ ጋር ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሳቸውም ጭምር ነው፡፡ በአንድ ሀገር ብዙ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበዙ ቁጥር የሚያገኙትም ድምጽ በዚያው ልክ ይከፋፈላል። ነገር ግን የዚህ ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር ፓርቲዎች ያላቸውን ልዩነት አቻችለው በመዋሃድ የተወሰኑ ጠንካራ ፓርቲዎች ሆነው መውጣት ይኖርባቸዋል።
ከምርጫ ሕጉና አስፈጻሚዎች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡እነዚህ ሕጎች፣ ደንብና መመሪያዎች ዙሪያ ላይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የማሻሻል ሥራዎች ከወዲሁ በፍጥነት መስራት ያስፈልጋል፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ ካልሆኑ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ መሆን አይችልም። ይህ መሆኑም ከማዕከል እስከ ምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢያ የሚመደቡት አስፈፃሚዎች ገለልተኛ ለማድረግ በተለይም የሚመለመሉበትና የሚሾሙበት አካሄድና መስፈርት መፈተሽ ይገባል።
ለአንድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መሆን የመገናኛ ብዙኃን ሚናም እጅጉን የላቀ ነው። ከዚህ ቀደም የነበሩ የታሪክ ሁነቶች እንደሚታወሰው በምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን ሚዛናዊነትና ገለልተኝነት ፈተና ላይ ወድቋል። የግል መገናኛ ብዙኃን መንግሥትና የምርጫውን አፈፃፀም ሂደት በመኮነን ሲጠመዱ፤ በአንፃሩ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉት መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የመንግሥት ደጋፊና አቀንቃኝ በመሆን የገለልተኝነትና የሚዛናዊነት ችግር ተንፀባርቆባቸዋል፡፡
በመሆኑም ታሪካዊውን ምርጫ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም መገናኛ ብዙኃን ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ውይይት፣ ሰላማዊ ሠልፍ ሆነ ወቅታዊ መግለጫዎች በምስል፣ በድምፅና በቃላት ብዛት ተመጣጣኝ የሆነ ዕድል በመስጠት ገለልተኝነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል።
መገናኛ ብዙኃን ካለፉት ተሞክሮዎች በመነሳት ያለፉ ስህተቶችን ሳይደግሙ ለሙያቸውና ለህሊናቸው ታማኝ በመሆን ሚዛናዊነቱን የጠበቀ መረጃን ለሕዝብ ማድረስ አለባቸው፡፡
በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እጅግ የተራራቁ ሃሳቦችን የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን ለማቀራረብ እርስበርስ የሚወያዩበት፣ የሚጣመሩበትና ሐሳባቸውን ለሕዝቡ የሚያቀርቡበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል።
ምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃን እና ተመሳሳይ ተቋማት ይህን ምርጫ ለማስተናገድ የሚችል ቁመና እንዲላበሱ ማድረግም በመንግሥት በኩል የሚጠበቅ ሥራ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ እንዳሉት «ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ተአማኒና ሕጋዊ የሆነ ምርጫ ማካሄድ ከቻልን ማንም አሸነፈ ማን፣ የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ናት፡፡» ስለዚህ በአጠቃላይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተገነባባት፣ ፍትህ የነገሰባት፣ እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከአለፉት ምርጫዎች በተገቢው ተምረን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይኖርብናል። ይህን ስናደርግም በኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ ማድረግ እንችላለን፡፡
ታምራት ተስፋዬ