ምርጫ ዜጎች የዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ከሚተገብሩባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጥበትና ለዚህም ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርግበት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሂደት አካልም ነው፡፡ ሂደቱ የሚከናወነውም ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ በፈጠረው እኩል መድረክ ተወዳድረው አማራጫቸውን ለሕዝቡ በማቅረብ የመንግሥት ሥልጣን ውክልና የሚያገኙበት መንገድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱና ዋነኛው ነው የሚባለው።
ይህንን እውነታ በመረዳትም ጭምር ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በሀገሪቱ ስለተጀመረው የዴሞክራሲ ለውጥ እና በሚቀጥለው ዓመት ይደረጋል ተብሎ ስለሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ ውይይት ያካሄዱት። በቀጣይ የሚከናወኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ምን መልክ ይኑረው የሚለውና ምርጫውን ነፃና ፍትሃዊ ለማድረግ ሊወሰዱ የሚገባቸው አስፈላጊ ለውጦችም የትናንቱ ውይይት አጀንዳዎች ነበሩ፡፡
በተለይ ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮችን መለየት፣ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ውይይቶች ያጋጠሙ ችግሮችን መፍትሄ ማስቀመጥ የሚሉት ጉዳዮችም በስፋት ተመክሮባቸዋል።
ቀጣዩን ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ የሁሉም ወገን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ሆኖ መውጣቱ ለአገራችን ይበል የሚያስብል ጉዳይ ነው። ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ቀዳሚው ሥራ የመንግሥት ቢሆንም በምርጫው የሚፎካከሩ ፓርቲዎች የየራሳቸው የቤት ሥራ አለባቸው። ከምርጫው ሂደት ጀምሮ እስከ ድህረ ምርጫው ድረስ ሊፈጠሩ የሚችሉ ውዝግቦችን በሰከነ መንገድ መፍታት የሁሉም ኃላፊነት ነው። ይህንን ወደ ምርጫ ሳይገባ አስቀድሞ መግባባት ያስፈልጋል። የመጨረሻው ውጤት ድልም ሆነ ሽንፈት በፀጋ የሚቀበሉ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህንኑ ለማረጋገጥም ከወዲሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ሕግ፣ በምርጫ ቦርድ ስያሜ እና የምርጫ ቦርድ የመስራት አቅም ላይ ውይይት አድርገው ስምምነትና መተማመን ላይ መድረስ አለባቸው፡፡
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት እውን ከሆነበት ወቅት ጀምሮ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እየተካሄደ ይገኛል። ከዓመት ዓመት የተዳዳሪ ፓርቲዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ውበትም ስጋትም ነው ተብሎ ይታመናል። ውበትነቱ ማንም ሰው በፈለገው መልኩ ተደራጅቶ ፓርቲ ሆኖ መወዳደር መቻሉ የአገሪቷን ዴሞክራሲያዊነት ማንጸባረቁ ነው። ስጋቱ ደግሞ ሁሉም ፓርቲ ሊያሸንፍ ያለመቻሉን እውነታ ተከትሎ የሚፈጠሩ ቀውሶች ናቸው። ለዚህ ደግሞ የሚበጀው ተበታትነው ያሉ ፓርቲዎች እንደ የፓርቲዎቻቸው ፕሮግራምና ዓላማ ውህደት በመፍጠር ቁጥራቸውን መቀነስ ሲችሉም ጭምር ነው። ስለሆነም ከምርጫው በፊት ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ አንድ ነገር ሊያበጁ ወቅቱ የግድ ይላል።
በተያዘው መርሀ ግብረ መሠረት በመጪው ዓመት የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥት ከወዲሁ መንገዱን የሚጠርጉ ሥራዎችና ውሳኔዎችን እያሳለፈ ይገኛል። ለምርጫ ቦርድ አዲስ ሰብሳቢ በሕዝብ ተወካዮች በማቅረብ አሹሟል፡፡ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ እና ፍትሐዊ ለማድረግ ሊወሰዱ በሚገባቸው አስፈላጊ ለውጦች ዙሪያ ላይ ትናንት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ይህም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ ስለሆነ መንግሥትን በብዙ መልኩ ያስመሰግነዋል።
ይህ እርምጃ አንድ መልካም ነገር ሆኖ፤ ምርጫ ቦርድም ሆነ መንግሥት ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ በውይይቱ የተነሱ ፍሬጉዳዮች ተቀምረው በአግባቡ ምላሽ ሊሰጣቸውም ይገባል። ዛሬ ፓርቲዎች ስጋት ብለው ያነሷቸው ነጥቦች ምላሽ ካላገኙና በምላሹ ዙሪያ መግባባት ካልተቻለ ነገ በምርጫውና የምርጫውን ውጤት በመቀበል እና አለመቀበል ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩ አይቀርም። ስለሆነም የመንግሥት ጆሮ ሰሚ የሆነውን ያህል እጆቹም ለመፍትሄ የፈጠኑና የማይሰንፉ መሆን አለባቸው። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በሁሉም ነጥብ ላይ እኛ ብቻ ነን ትክክል ከሚል ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ አካሄድ ከወዲሁ መለያየት አለባቸው።