አዲስ አበባ፡- የአራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ። እስከአሁን ባለው ሂደት በህዝብና ቤት ቆጠራው ዙሪያ ህዝቡን ለማስገንዘብ የተሠራው የቅስቀሳ ሥራ የተፋዘዘ እንደሆነም ተመልክቷል።
የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ከሦስት ሳምንታት በኋላ ለሚጀመረው የህዝብና ቤት ቆጠራ ቀደም ሲል ከተደረጉ ሦስት ቆጠራዎች በተሻለ መልኩ ዝግጅትተደርጓል።
የቆጠራ ካርታና መጠይቆች ተዘጋጅተዋል። ቴክኖሎጂ የመምረጥ፣ የመሞከርና የመላመድ ሥራዎች ተከናውነዋል። ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የመሰረተ ልማት ላልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የሚያገለግሉ 126ሺህ የሐይል ቋት (ፓወር ባንክ )፣ 25 ሺህ ሶላር ፓናል ግዥም ተከናውኗል። ለቆጠራው አገልግሎት ከሚውሉት 180 ሺ ታብሌቶች (የእጅ ኮምፒውተሮች) ውስጥ በ160 ሺህ ታብሌቶች ላይ ዲጂታል ካርታና መጠይቆችን የመጫን ሥራ ተሠርቶ ታብሌቶቹ ወደ ክልሎች እየተሰራጩ ይገኛሉ።
ቀሪዎቹ በዚህ ሳምንት ውስጥ ተጭነው የሚሰራጩ ይሆናል። 37ሺህ መቆጣጠሪያ ቦታዎችም ተለይተዋል። ‹‹ክልሎችም ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀውናል›› ያሉት አቶ ሳፊ፣ ስነ ምግባር፣ ለሥራው ቁርጠኛና በቂ ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎችንና ተቆጠጣሪዎችን መልምሎ ዝግጁ ማድረግ አንደኛው ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
ክልሎች ለቆጠራ ሥራው የመለመሏቸው ከስምንት ሺ በላይ የመጀመሪያ ድግሪ ያላቸው ባለሙያዎችም ከየካቲት 26 ቀን ጀምሮ እስከ መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የአሰልጣኞች ስልጠና በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ ባለሙያዎቹ ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ በቆጠራው የሚሳተፉ 180ሺ ባለሙያዎችን የሚያሰለጥኑ ይሆናል ብለዋል።
ጥራት ያለው መረጃ ለመሰብሰብም በማዕከል ሆኖ በቴክኖሎጂ በመታገዝ መቆጣጠር የሚቻልበት ስርዓት መዘረጋቱን አመልክተው፣ ለሦስት መረጃ ሰብሳቢ ሠራተኞች አንድ ተቆጣጠሪ የተመደበ መሆኑንና ድንገተኛ ተቆጣጣሪዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። ‹‹ቴክኖሎጂው ቢዘጋጅ፣ የሰው ሐይሉ ቢመለመል ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጥ ካልተቀሰቀሰ የህዝብና ቤት ቆጠራው ውጤታማ አይሆንም›› የሚሉት አቶ ሳፊ፣ እስከአሁን ባለው ሂደት በስነ ህዝብና ቤት ቆጠራው ዙሪያ ህዝቡን ለማስገንዘብ የተሠራው የቅስቀሳ ሥራ የተፋዘዘ በመሆኑ በቀጣይ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የህዝብና ቤት ቆጠራ ለፖለቲካ፣ ለማህበራዊና ለኢኮኖሚ ጥቅም ስላለው ቆጠራን የሚያደናቅፍ አካል እንደማይኖር ገልጸው አገር ወደ ፊት እንድትቀጥልና ዜጎች መሰረታዊ የሆኑ መብታቸው እንዲከበርላቸው ለማድረግ መረጃው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። የቆጠራው አስፈላጊነት በአብነት ሲያስረዱም ዜጎችን ንጹህ ውሃ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ መንገድና መሰል መሰረተ ልማቶችን በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል። እንደ አቶ ሳፊ አገላለፅ የጸጥታ ጉዳይን በተመለከተ ክልሎች ለቆጠራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለባቸው። በተለያዩ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች እስከ ቆጠራው ቀን ድረስ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ መሥራት አለባቸው።
ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ካልተመለሱ ግን ባሉበት ቦታ ሆነው ሊቆጠሩ ይችላሉ እንጂ በአገሪቱ ውስጥ የማይቆጠሩ አካባቢዎች የሉም። በህዝብና ቤት ቆጠራው ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል። የቆጠራው የመረጃ ጥራት ጥያቄ ሊያስነሳ የሚችለው ሁሉም ሰው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሳይወጣ ሲቀር መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ለቆጠራው የተመለመሉ ሰዎች ለህሊናቸው፣ ለአገራቸውና ለህዝባቸው ታማኝ ሆነው መረጃ መሰብሰብ አለባቸው። መንግሥት በበኩሉ ጥራት ያለው መረጃ ለመሰብሰብ ቆጠራው በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ አድርጓል›› ብለዋል።
አቶ ሳፊ እንዳሉት፣ ቆጠራው በተቻለ መጠን በ10 ቀናት እንዲጠናቅ ዕቅድ ተይዟል። በገጠር ከመጋቢት 29 ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ሲሆን በከተሞች ደግሞ ከሚያዝያ 11 ቀን እስከ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚጠናቀቅ ይሆናል። የገጠሩን ሕዝብና ቤት የቆጠሩ ባለሙያዎች ሀብትን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር በከተሞችም እንዲቆጥሩ መፈለጉንም ታውቋል።
የህዝብና ቤት ቆጠራ በየ10 ዓመቱ የሚካሄድ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የጸጥታ ችግር በማጋጠሙ ሳቢያ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሊራዘም መቻሉ ማወቅ ተችሏል። ከሁለት ዓመት በፊት ለ4ኛው ህዝብና ቤት ቆጠራ ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት ቢሆንም ይህ ገንዘብ በአሁኑ ጊዜ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ በጀት በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚጸድቅ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011
በጌትነት ምህረቴ