የትናንት በስቲያዋ የወረሃ መጋቢት መባቻ ለኢትዮጵያውያን ጥቁር ቀን ሆና አልፋለች። ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው በበረራ ቁጥር ኢት 302 ቦይንግ 737- 800 ማክስ በሀገሩ ሰማይ ስር ተከስክሷል። በአደጋው የ35 አገራት ዜጎች የሆኑ 157 መንገደኞችና የበረራ ሠራተኞች ህይወታቸው አልፏል።
ክስተቱ የኢትዮጵያውንን ልብም ሰብሯል። አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ከቢሸፍቱ በስተምሥራቅ በግምት ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቱሉፈራ ጉምብቹ ወረዳ ቀጫ ዲራ ቀበሌ ነው። በቦታው ተገኝተን እንደተመለከትነው አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ከተራራ ስር በሚገኝ ሜዳማ ቦታ ላይ ነው።
የተከሰከሰበት ቦታ ወደ ውስጥ ሰምጧል። አካባቢው ክፉኛ ተቆፍሯል፡፡ በጉድጓዱ ዙሪያ ትናንሽ የአይሮፕላኑ ቁርጥራጭ አካል ይታያል። የውሃ ማያዣ ኮዳዎች ተቆራርጠው ይታያሉ። የአውሮፕላኑ አካል ከመቆራረጡና ከመድቀቁ የተነሳ በዚያ ቦታ ግዙፍ አውሮፕላን ተከስክሷል ብሎ ለማመንም ያስቸግራል።
አውሮፕላኑ ሲከሰከስ የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ስለሁነቱ የሚናገሩት በጥልቅ የሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ነው። የአካባቢው ነዋሪ አቶ መልካ ገለቱ አውሮፕላኑ ቁልቁል ሲምዘገዘግ መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለከብቶች ገለባ ሰጥተው ወደ ቤት ገባ እንዳሉ ባለቤታቸው የሰጧቸውን አቦል ቡና ገና ፉት ሳይሉ ከባድ ድምፅ መስማታቸውን የሚናገሩት አቶ መልካ፣ ቡናውን ቁጭ አድርገው ቱር ብለው ሲወጡ በተፈጠረው የአውሮፕላን ድምፅ ከብቶቻቸውና በጎቻቸው ደንብረው ማሰሪያቸውን በመበጠስ ከግቢ መፈርጠጣቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በሁኔታው ተደናግጠውቀና ሲሉ አውሮፕላኑ እሳት እየታየበትና እየጨስ በቤታቸው ላይ ያልፋል።
ከፍተኛ ንፋስና ድምፅ ይሰማ ስለነበረ የተወሰኑት የአካባቢው ሰዎች ወደቁ፤ ሌሎች ደግሞ ብርክ ይዟቸው በድንጋጤ ደርቀው ቆመው ቀሩ። ቤቶቹና አካባቢውም በጭስ ታፈኑ። በመጨረሻም አውሮፕላኑ ከቤታቸው ጎን በእርሻ ቦታ ተከስክሶ ብትንትኑ ወጣ። ሌላኛው የዓይን እማኝ አቶ ጉተማ ንጉሡ፤ ከአንድ ባልደረባቸው ጋር በመሆን አክስታቸውን ለመጠየቅ በጉዞ ላይ ነበሩ፡፡ አውሮፕላኑ ሲከሰከስም በዓይናቸው ዓይተዋል። ‹‹አውሮፕላኑ ሊከሰከስ ሲል ከፍተኛ ድምፅ አሰምቷል፤ጭስም ታይቷል። ወዲያውም በአፍጢሙ ተከሰከሰ። ከፍተኛ ፍንዳታ አሰማ።
በጭስና በአቧራም ታፈንን።›› የሚሉት አቶ ጉተማ፣ ጭሱና አቧራው ወደ ተከሰከሰበት አካባቢ አላስጠጋ እንዳላቸውም ይናገራሉ። ለተወሰነ ጊዜ ራቅ ብለው በቅርብ ርቀት ሆነው ሲመለከቱ መቆየተቻውን ጠቅሰው፣ጭሱ እንደጠፋም ወደ ተከሰከበት ቦታ መቅረባቸውን ያብራራሉ።
ከዚያም የአካባቢው ነዋሪዎች መሰባሰባቸውን ይገልጻሉ:፡ የአካባቢው ሚሊሺያ አቶ ግርማ ተሊላ አውሮፕላኑ ሲከሰከስ በአካባቢው ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል ይላሉ። ወደተከሰከሰበት ቦታ ለመጠጋትም የሚፈነዳ ነገር ይኖራል በማለት ለመጠጋት ፈርተው እንደነበር ገልጸው፣አቧራውና ጭሱ ሲጠፋ በመጀመሪያ በቦታው የደረሱት እሳቸው እንደነበሩም ነው የሚናገሩት። አቶ ግርማ አካባቢው ላይ እንደ ደረሱ የተመለከቱት አውሮፕላኑ ያረፈበት ቦታ ላይ ትልቅ ጉድጓድ መፈጠሩን ነው።
በጉድጓዱ ዙሪያም ደም፣ የተቆራረጠ የተለያዩ የሰው አካላት ፤ ትናንሽ የአውሮፕላን ቁርጥራጮችን ተመለክተዋል። ከዚህ ውጪ በቦታው በህይወት ያለ ሰው አላገኙም፡፡ አካባቢውን ከበው ሲመለከቱ የወረዳው ፖሊሶች ደርሰው መጠበቅ መጀመራቸውን እነ አቶ ግርማ ጠቅሰው፣ወዲያውም አምቡላንሶች በአካባቢው ቢደርሱም የሚወስዱት እንዳላገኙ የተናገሩት በጥልቅ የሃዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ነው። ትረፊ ያላት የግሪካዊው መንገደኛ አንቶኒስ ማቭሮፖሎስ ነፍስ ግን የአደጋው ልዩ ክስተት ሆናለች፡፡
ግሪካዊው ሁለት ደቂቃ በመዘግየቱ ከአደጋው ተርፏል፤ መንገደኛው “ሁለት ደቂቃ በመዘግየቴ ምክንያት አውሮፕላኑ ስላመለጠኝ ከሞት ተርፌያለሁ” ሲል በፌስ ቡክ አካውንቱ ገልጿል። ትኬቱን እና የዕለቱን ሁኔታ በፌስቡክ አካውንቱ ላይ አያይዞ የገለጸው ግሪካዊው ተጓዥ፤ ሁለት ደቂቃ ብቻ በመዘግየቱ ‹‹ለምን ለመግባት እከለከላለሁ›› በሚል ከአየር መንገዱ ሠራተኞች ጋር ጭቅጭቅ ፈጥሮ እንደነበረም አስታውሷል:: አደጋው ሲነገረው ግን በዕድለኛነቱ ተገርሞ መመለሱን አስታውቋል። ግሪካዊው ‹‹ባላረፍድ ኖሮ 158ኛው ሟች እሆን ነበር›› ሲልም ነው ዕድለኛነቱን የገለጸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ