«የማዕከለ ሰብዕ ትንሳኤ በኤረር ተራራ ድምጾች» የተሰኘ መጽሐፍ ወደ አንባብያን እጅ ከገባና የመጻሕፍቱን ገበያ ከተቀላቀለ ወራት አልፈዋል። የመጽሐፉ ነገርና መልዕክት ግን ሁሌም አዲስ ነውና ዛሬ በዚህ አምድ ልናነሳው ወደናል። ይልቁንም የመጽሐፉ ደራሲ ጤንነት ሰጠኝ በመጽሐፉ ዙሪያ ያቀበለንን ሃሳብ እናካፍላችኋለን።
መጽሐፉ በአቀራረቡና በያዘው ሃሳብ ለየት ይላል። በዚህ መጽሐፍ አንዱና አንኳር ነጥብ ማዕከለ ሰብዕ የሚለው ነው። «ማዕከለ ሰብዕ» የተባሉት እነማን ናቸው? ደራሲው ጤንነት እንዲህ አለ፤ ማዕከለ ሰብዕ የተባሉት በእውቀት ክምችት ያይደለ ነገሮችን በመገንዘብና በማስተዋል፤ ተፈጥሮን በማየትና አካባቢን በመረዳት በሃሳብ ልዕልና የደረሱ ሕዝቦች ናቸው።
ከዛም አልፎ ምስጢራዊ ከሆኑና የሰው ልጆች ሊደርሱባቸው አይቻልም ተብለው የሚታሰቡ ዓለም አቀፍ እሳቤዎች ላይ የደረሱ ሰዎች ማዕከለ ሰብእ ተብለዋል። ታድያ ይህ ከፍታ በሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ዘርፍ አይደለም። ከሁለቱም ልቀው መታየት የቻሉቱ ናቸው። ይህ ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃም ግንዛቤውና ተቀባይነቱ ያለ መሆኑን ጤንነት ያነሳል። አያይዞም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ታላቅነቷን ያገኘችው በእነዚህ ሰዎች ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳል።
ይህ መጽሐፍ ታድያ እነዚህን በሃሳብ ልዕልና ላይ የሚገኙ ሰዎችን ከዚህ ትውልድ ሰው ጋር የሚያገናኝና የሚያነጋግር ነው። ሁለቱም ወገኖች በገጸባህሪያቱ ተወክለው፤ ማዕከላዊ ስፍራ በሚባለው በኤረር ተራራ ተገኝተው ይነጋገራሉ። በንግግሩም ውስጥ ለዚህ ዘመንና ትውልድ መፍትሄ የሚሆን ሀሳብ ከማዕከለ ሰብዕ ወገን ይገኛል።
መጽሐፉን አንባብያን እንድታነቡ በመጋበዝ በውስጡ ተጠቅሶ ከሚገኘው ሃሳብ መካከል አንዱን ሃሳብ ወዲህ እናምጣው። ይህም በመጽሐፉ የተለያየ ምዕራፍ የተጠቀሰው «ሰባት አምድ» የሚለው ሃሳብ ነው። ሰባት በአገራችን እንዲሁም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት የተለየ ትኩረት የሚሰጣት ቁጥር ናት። ታድያ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደምን ገባ? የመጽሐፉ ደራሲ ጤንነት ተከታዩን መልሷል።
ሰባት አምድ የተባሉት አንድነትና ልኅቀት የሚታይባቸው፤ አንድ ማኅበረሰብም ወደ አንድነት የሚመጣባቸው የተለያዩ መንገዶች ናቸው። በዚህ መሰረት የመጀመሪያው አንድ ግለሰብ ነው። አንድ ሰው የተለያዩና ብዙ የሰውነት ክፍሎች አሉት፤ ግን አካሉ አንድ ነው። ሲሠራም አንድ ሰው ተብሎ እንጂ ብዙ የአካል ክፍሎቹ እያንዳንዳቸው አይደለም።
ከዛ ከፍ ሲል ሁለተኛው ቤተሰብ ነው። ቤተሰብ በስጋና በደም ይተሳሰራል። ታድያ አንድ ሰው «እህትህ ተመታች» ሲባል ፍጹም ይደነግጣል። ሌላ የማይዛመደውና የማያውቀው ሰው ተጎዳ ቢባል ግን ሀዘን ቢሰማውም ድንጋጤው ከዛኛው ጋር አይገናኝም።
ሦስተኛው ማኅበረሰብ ነው። ይህም ባህልን መሰረት ያደረገ የተለያዩ ቤተሰቦች ስብስብ ማለት ነው። ትስስሩን ከብሔር ጋር ብናመሳስለው፤ በዚህ ኅብረት ውስጥ ለብሔር ተቆርቋሪነት አለ። የራሱ አካል ያልሆነ፣ በስጋም ያልተዛመደው ግን በባህል ተሳስረዋልና የአንድ ማኅበረሰብ አባል በመሆን ብቻ ተቆርቋሪነትና አንድነት ይታያል።
አራተኛው አምድ በድንበር የሚከለለው አገር ነው። የአገር ነገር ሁሉንም ሰው ያሳስባል። ይህ ደግሞ ከላይ ካሉት ሦስቱ ልቆ የሚገኝ የኅብረት ቁልፍ ነው። ከዚህ ከፍ ሲል በአምስተኛ ደረጃ ሃይማኖት ይገኛል። ይህ በአካባቢም፣ በስጋና በደምም ሆነ በሌላ ቅርበት የሚመጣ አይደለም፤ በሃይማኖት አስተምኅሮ ነው። በዚህም እልፍ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ያለ አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ሲነካ እዚህ ያለው ይሰማዋል። ይህ ደግሞ ከቀደሙት እጅግ የላቀና ድንበር የተሻገረ ትስስር የሚታይበት ነው።
ስድስተኛ በመንፈስ አንድ የሆኑና ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆኑ በመጨረሻ በሃሳብ ልዕልና የደረሱት ማዕከለ ሰብዕ የሚባሉት ይገኛሉ። እነዚህም ሰው በመሆን ብቻ እና በጥበብ ዘርፍ የሚተሳሰሩት ናቸው። ታድያ ከዚህ ምን ይገኛል? የመጽሐፉ ደራሲ ጤንነት በኤረር የተሰሙት ድምጾች መልዕክት እንዲህ ነው ይለናል፡፡
«በማዕከለ ሰብእ እሳቤ ብሔር መሰረቱን መጣል ያለበት ባህል ላይ ነው ይላል። ባህል መሰረቱ ቋንቋ ላይ ብቻ አይደለምና። ዋናው የአንድ ብሔር ባህልና እምነቱ እንዲሁም አኗኗሩ ነው። አንድ ሰው መሰረቱ በባህል ላይ ቢቀመጥ ሁሉም ይጠራል። በዛ ውስጥ ትልልቅ የበሰለ ሃሳብ ስላለ። አሁን ላይ ቋንቋውን ይዞ ከላይ ከላይ የሚሮጠው ነው ችግር የሚፈጥረው።…»
በአገራችን ይህ የማዕከለ ሰብዕ ጥበብ የአክሱምና የነላሊበላ፣ የቅዱስ ያሬድና የሄኖክን ጨምሮ እጅግ ላቅ ያሉ ስልጣኔዎች አስገኝቶናል። ትልልቅ መገለጥ ላይ የደረሱ፣ ሃሳባቸው ዓለምንና አገርን ያነቀሳቀሰ፣ ዛሬም ድረስ ጥበባቸውን ይዘን የምንቀጥለው የእነዚህን ሰዎች ነው። በቁጥር ትንሽ የሆኑ፤ ነገር ግን ሀሳባቸው ትልቅ ስለሆነ ግን ትውልድ እየኖረበት ያለ።
ታድያ አሁን ላይ ምን ደረሰ ስንል፤ መጽሐፉ ትንሳኤያቸው በቅርቡ ይሆናል ይለናል። ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግን መቀዛቀዙንና ሰዎች በልዕለ ኃያል ሃሳብ መኖር መተዋቸውን ይጠቅሳል። ለዚህም ምስክሩ አሁን ላይ ባሉት እሳቤዎች ከመኖር ውጪ አዳዲስ ሃሳቦች እየፈጠረ ያለ ስለሌለ ነው። «ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አሁን ላይ በመንፈሳዊ ዘርፍ የተገኙ ጥናቶች ናቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት» ብሏል፤ ደራሲ ጤነንት። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
ሊድያ ተስፋዬ