እንዴት ብዬ?

ሰማይና ምድር የጨለማ ካባ በመደረብ አፍ ለአፍ ገጥመው ሲንሾካሾኩ ካፒቴን ሙሉ አሰፋ የሹፍርና ግዴታዋን ለማድረስ ከመገናኛ ወደ ለገጣፎ ሚሽን ተሳፋሪ ጭና እየተጓዘች ነው። የአልኮሉ ሽታ እየተነፈገ ምቾት ቢነሳትም የተላበሰችው ሙያ ትዕግስትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሕዝብን ለማገልገል ስትል ከተሳፋሪዎች የሚሰነዘሩ የነገር ፍላጻዎችን ችላ ሞራሏን ለማጠንከር ታገለች “ጆሮ ዳባ ልበስ” በማለት ሁሉንም እንዳመጣጡ እየሸኘች። “ይህቺ ድስት የለሽ፤ ምን ወላጅ ቢያሳድጋት ነው እንደጎረምሳ እያመሸች የምትገባው? ይብላኝ ላገባት” ይላሉ በምጸት ሳቅ ታጅበው። መኪናው እየከነፈ ነው፤ ሰዎቹም አግቧቸውን ቀጥለዋል። “ሹፌሯ ሴት ናት፤ በደህና ታደርሰናለች ብለህ ነው? ብንወርድ ይሻላል” እያሉ ሁለት ወንድ ተሳፋሪዎች ሲንሾካሾኩ ከሙሉ ጆሮ ሲንጦለጦል መጥቶ ገባ፤ እሷ ግን

“ሆድ ያስብስ የለም ወይ ሲገረፍ ክራሩ፣

ሽሙጥ አቀብሎት ነገር ሥራ ሥሩ።” በማለት ቃል ሳይወጣት አዜመችና “በሴቶች አቅም ላይ የሚታይ ማንኛውም ጥርጣሬ እንዲረታ ሥራዬ አንደበቱን ይፍታ” አለች። ከቃል በላይ ተግባር ፍቱን መድኃኒት እንዳለው በማመን። በተሳሳተ አመለካከታቸው ሴትን ልጅ ከወንድ እጅ የጣሏት፣ ችሎታዋን ሳያዩ የናቋት፣ ቀርበው ሳይረዱ የፈረዱባት እንዲሁም “ግድ የለህም እንደሰው እንሁን” ብለው የገቡት እነዚያ ተሳፋሪዎች ከሚፈልጉት ቦታ ደርሰው ሊወርዱ ሲሉ ትሕትና በተሞላ ድምጸት የሙሉ ጥሪ ሰቅዞ ይዞ አላላውስ አላቸውና “እመት” አሏት ሃፍረት እያሸማቀቃቸው። “ደረሳችሁ?” ብላ ስትጠይቃቸው “ምን ማለትሽ ነው?” አሉ ያልገባቸው በመምሰል። “ከገባችሁ ጊዜ አንስቶ ሴትነቴን ስታሙት ነበር” አለቻቸው። ፊቷን ፈገግታ ሳይለየው። እንደ ምራቅ የተፉት ነውር ሆኖ ስላሳፈራቸው ካንገታቸው በማንጎንበስ መሬት መሬት ማየት ያዙ። ወዲያው ከጉልበታቸው ዝቅ አሉና ሃፍረት ባጎላደፈው ምላሳቸው እየተንተባተቡ የምስጋና ቃል አዥጎደጎዱና እጅ ነስተዋት ወረዱ።

ወትሮውኑም ካፕቴን ሙሉ አሰፋ ይህን ሙያ ከልቧ ፈቅዳው አታውቅም። የእንጀራ ጉዳይ ሆኖ ጣለባት እንጂ። “ለነገሩ ያባቴ ምኞት ነው ለዚህ ያደረሰኝ” አለች። የኋላ ታሪኳን ከመሪው ጋር እየጠመዘዘች። ከዛሬ አርባ ስምንት ዓመታት በፊት በወርሐ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ዘጠኝ አመተ ምሕረት ከአባቷ አስር አለቃ አሰፋ ወልደ ማርያምና ከእናቷ ከወይዘሮ ፍታሌ መገናሳ ለቤቱ የመኸር ልጅ የሆነችው ካፒቴን ሙሉ አሰፋ በሀገረ አዲስ አበባ ሃያ ሁለት ማዞሪያ ነው የተወለደችው። “አዲስ ጥንዶች ለትዳር እንግዳ ይሆኑና ጎጇቸው ውል ይበዛበታል፤ በዚህ መሐል የሚገኘው የመጀመሪያ ልጅም ሙገሳውም፣ ወቀሳውም እንደክረምት ሰማይ ይፈራረቅበታል። ሕይወት ስታበግናቸው ‹‹መጣህብን›› ኑሮ ሲቀናቸው ደግሞ ‹‹መጣህልን›› በሚሉ ተለዋዋጭ ስሜቶች ይናወጣል።

እንደዚህ ሁሉ መጽሐፍ ይሁን የሙዚቃ ሥራ በኪነጥበቡ ዓለም የበኩር ትሩፋታችን በሙያ ግድፈትና ከልምድ ማነስ በሚመጣ ስህተት ጉድለቱ ያይልና ምሉዕነቱን ያራክስብናል ህላዌነቱንም ያኮስስብናል” እንዲል እውቁ ፒያኒስት ‹‹አርታተም›› ። ካፒቴን ሙሉ አሰፋም የቤቱ ኃላፊነት ጫንቃዋ ላይ የወደቀው ገና የልጅነቷ ጤዛ ሳይረግፍ ነበር። አካሏ ሳይጠና ልቦናዋ ሳይሰላ የተጋረጠባት ፈተና “ወይ ድንግርግር ተጓዝ ያለው እግር” ቢያሰኛትም እናቷ ፊደል ያልቆጠሩ የቤት እመቤት በመሆናቸው ካባቷ ሞት በኋላ የጎጇቸው ምሰሶ እንዳይዘም “ኑሮ እሹሩሩ አይብዛ ሽንቁሩ” ብላ ራሷን በቀን ሥራ ላይ አዋለች።

የዘጠኝ ወር ቤቷና ወንድሞቿ ቀምሰው ያድሩ ዘንድ የገባችበት የሻይ ቤት ሥራ ትርፉ ድካም ብቻ ቢሆንባትም “ምን ካሉት ምን ይሞቃል” ነውና ጥርሷን ነክሳ በመሥራት ላይ እንዳለች ‹‹ምትአም›› የተባለ የኮንስትራክሽን ድርጅት ማስታወቂያ ያወጣና ተወዳድራ በማለፍ ዛሬ ላለችበት የሹፍርና ሕይወት መሠረቷን ያዘችበት።

ጥንስሱም ሰምሮላት “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” እንዲሉ አበው በቀን ሥራ ውሎዋ የደገፈችውን ታናሽ ወንድሟን ዲፕሎማ በማስተማር ናሽናል ሞተር ድርጅት ውስጥ በቋሚነት ለማስቀጠር በቃች። በዚህም ቤታቸውን ለመደገፍ ተጨማሪ ጉልበት መፍጠር ቻለች። ይሁን እንጂ የወንድሟ ድጋፍ ከጥቂት ወራት በላይ መዝለል አልቻለም፤ በገጠመው የአዕምሮ ሕመም ሳቢያ ከቤት መዋል ያዘ። በባላቸው ሞት ኃዘን ያቆራመታቸው እናቷ የልጃቸው ችግር ሲደገም በማይሽር የዲስክ በሽታ ተያዙና የሙሉን አሳር አበዛው። ሙሉ ከእጅ ወደአፍ በሆነ ኑሮ ላይ ፋታ የማይሰጥ ችግር ሲጨመርባት መላ ቅጡ ጠፋት። በዚህ ምክንያት እንደሙጫ ተጣብቃበት የነበረውን ትምህርቷን ለመልቀቅ ተገደደች። ባልገመተችው ሁኔታ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ቢመጣላትም የመከራ ማዕበል ገፍቶ ከትምህርት ጎዳና አስወጣት።

ከአንደኛ እስከአስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ ቀለም የተጎነጨችበትን ምሥራቅ ጮራን ባየች ጊዜ ያቋረጠችውን ትምህርት እንደምትቀጥል ብታስብም መቼ? የሚለው ጥያቄ ግር ይላትና መልሳ ትውጠዋለች፤ “እውን መማር አቅቶኝ ነው?” በማለት ራሷን ስትጠይቅ የምትሰጠው ምክንያት ታጣና በጸጸት ሳማ ትለበለባለች።

በወታደር ቤት የሜካኒክ ሹፌር የነበሩት አባቷ “የኔን ሙያ ትይዣለሽ ልጄ” ሲሏት ወግ ባህሉና ፍርሃቱ ተብትቦ ሲያሸማቅቃት “አይሆንም” ስትል ስለፍርሃት ጦስ የነገሯትን ምክረ ሃሳብ አስታውሳ አመነዠከችው።

ሳንዱች እየሸጡ ልጃቸውን በከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስተምሩ በመንደሩ የታወቁ ነጋዴ ነበሩ። አንድ ቀን ልጃቸው ለእረፍት በመጣበት አጋጣሚ እንዲያግዛቸው ይጠይቁትና እየሠሩ ሲጨዋወቱ ለወደፊት የዓለም ኢኮኖሚ ምስቅልቅሉ እንደሚወጣ እያነሳ ፍርሃቱን ገለጠላቸው። ቀለም የቀመሰ ኮሌጅ የበጠሰ ነውና ፍርሃቱን ተቀብለው ሳያመነቱ ዋጡት። ያዘጋጁት የነበረውን የሳንዱች መጠን ከዕለት ወደለት እየቀነሱ ሲሄዱ ደንበኛ ራቃቸውና ቤቱን ዘግተውት አረፉት። ማስተዋል የጎደለው ትምህርት በፍርሃት ሸብቦ የሚገጥሙንን ፈተናዎች በጠንካራ ሞራል እንዳንጋፈጣቸው ልፍስፍስ ያደርገናል፤ ደግሞስ የተማረ ሁሉ አዋቂ ነው ያለው ማን ነው? ሙሉ ነገር ማንቀራጨቷን ቀጥላለች።

ገበሬውን “ስንዴ ዘርተሃል?” በማለት ሲጠይቁት “አይዘንብም ብዬ አልዘራሁም” ሲል ይመልስላቸዋል፤ “በቆሎስ?” ብለው ዳግመኛ ሲጠይቁት “ተባይ ይበላዋል ብዬ ፈርቼ አልዘራሁም” ይላቸዋል፤ “እና ምን ለመዝራት አስበሃል?” በማለት ሲጠይቁት “ጎመን በጤና” ብሎ እየኖረ እንደሆነ መለሰላቸው። ከነጋችን በረከት ይልቅ የዛሬ ፍርሃታችንን ደጋግመን ለልቦናችን በነገርነው ጊዜ ከሕልማችን ያሸሸናል፤ ካፒቴን ሙሉም ከገበሬውና ከሳንዱች ሻጩ ሰውዬ በባሰ የሥነልቦና ፍርሃት እንደገጠማት ከወጋችን መረዳት ችያለሁ፡፡

ከአስተማሪ ታሪኮች እንግዳዬም አንባቢዎቼም ትማሩበት ዘንድ የቻርለስ ዲክንስን ደብዛዛ የሕይወት ገጽ ገለጥኩ። ቻርለስ ዲከንስ ጥቂት የማይባሉ የዕድሜ ዘለላዎቹን በእስር ቤቱ የጨለማ ክፍል ውስጥ ስላሳለፈ የፍርድ ቀኑን ጨርሶ ሲወጣ የታገለለትን የነፃነት ብርሃን ለማየት አልደፈረም። ጣረሞት የተጫናቸው ድምፆችም ነፃ ይወጡ ዘንድ ዋጋ እንዳልከፈለ ሁሉ ዛሬ ላይ ሊሰማቸው አልፈቀደምና ከጨለማ ክፍሉ እንዲመልሱት ተማጸነ። ከፍርሃት ባርነት ያልተላቀቀ ሰው ዓለምን ይቅርና ራሱንም ቢሆን ነፃ ሊያወጣ አይችልም። ምክንያቱ ደግሞ የተስፋ መቁረጥ ክፉ መንፈስ በሃሳባችን ተሰንቅሮ ሕልማችንን እንዳንጨብጥ፣ ከጎታች ልማዳዊ እሳቤዎች እንዳናመልጥና አዳዲስ የሕይወት ገጾችን እንዳንገልጥ ወደኋላ የሚያንደረድረን አቀበት መሆን ብቻ ሳይሆን ለውድቀትም ይዳርገናልና ነው።

ተንስዑ ለጸሎት እያልኩኝ ስዞር፣

አንቺን ምን አመጣሽ ከመንበሩ ስር።

ብሎ መቀኘት ይህን ጊዜ ይመስለኛል።

ካፒቴን ሙሉ አሰፋም ጤና የራቃቸውን እናቷንና ወንድሟን “ያበጀሁት ውሃ አጣጬ እንደኔ ላይወድልኝ ይችላል” በሚል ፍርሃት ተሸብባ “እነሱን ትቼ እንዴት ብዬ አገባለሁ?” እያለች እድሜ ልኳን ወንድ ስትሸሽ ኖራለች።

የማሌዢያው ዝሆን አምስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ በረዥም ገመድ አስረው ነበርና ያላመዱት አካሉ ጎልብቶ ቅስሙ ደርጅቶ ባዩ ጊዜ ከሌሎች ዝሆኖች ጋር ይደነብ ዘንድ ከረዥሙ ገመድ ቢፈቱትም ባጠሩለት ክልል ውስጥ ፍርሃትን ነውና የገበየው ከለመደው መስመር በላይ መሻገር አልቻለም።

ካፒቴን ሙሉ አሰፋም በትዳር ዓለም ውስጥ ራስን መስጠትን ሌላውን መዘንጋት አድርጋ በመቁጠር “አዱኛሽን እዪ፤ እሱ እንኳን ቢቀር ከውጪም ቢሆን ወልደሽ አምጪ” የሚለውን የወላጆቿን ጉትጎታ ሸሽታ፣ ከዕድሏ ተጣልታ፣ ወግ ማዕረጓን ዘንግታ ልምዝምዝ ሃሳብ እያስታመመች ከሰው ርቃ በብቸኝነት ሕይወት ዳገታማውን የኑሮ አቀበት እየገፋች ትገኛለች።

አንድ ወጣት ነበር አሉ። ማግባት ፈለገና የኔ የሚላትን ሴት አምጥቶ እናቱን ሲያስተዋውቃቸው ካይዋት በኋላ እናት “አይሆንም” ይላሉ። በእንዲህ መልኩ በርካታ ሴቶችን አንዷንም ሳይወዱለት ይቀሩና ወዳጄ ለሚለው አብሮ አደጉ ሲያማክረው ራሳቸውን እናቱን የምትመስል እንዲያጭና ወስዶ እንዲያስተዋውቃቸው ይነግረዋል፤ እሱም እንዳለው አደረገና የናቱን እሽታ በተስፋ ሲጠብቅ ፈቃዳቸውን ሰጡት። ይሁን እንጂ ደስታው አፍታ አልቆየም። አባቱ በተራቸው “እናትህን የምትመስልማ ጭራሽ አታገባም” ብለው ትዳር ለመያዝ ከነበረው ጉጉት አናጠቡት።

ልጅም በምን ይሉኛል እድሜ ልኩን ሳያገባ የፍርሃቱ ጦስ ሰለባ ሆነ። “ወደተፈጥሮ እንመለስ” በማለት አብዝተው የሚጽፉትና የሚናገሩት ሳድጉሩ ስለፍርሃት ይህን ይላሉ። “ፍርሃት ማለት የሕልማችንን አበባ የሚቀጥፍ የስኬት ቡቃያችንን ገና አንገት ሳይለይ በንጭጭነቱ የሚቀረጥፍ የስሜት ትብታብ የውድቀት ምኩራብ የመንፈስ እዳ የስንፍና ጓዳ ነው።”

በዕለት ተዕለት ክዋኔያችንና በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ፍርሃት ሳንካው ካየለ በካፒቴን ሙሉ ሕይወትም ያጠላው ደመና ነፍስ ዘርቶ ሥጋ ሠርቶ

“ገንፎ በቅቤ፣

ይወዳል ወገቤ።”

ከሚለው ሀገርኛ ትውፊት ጋር በስማ በለው ቃል እያስተጋቡ ለመኖር ይገደዳሉ ማለት ነው። የጃይኒዝምን እምነት አብዝቶ የሚያንቆለጳጵሰው ሕንዳዊው መሃቪራ “የሰው ልጅ ካደረበት ፍርሃት የተነሳ ከተፈጥሮና ከስሜቱ ሸሽቶ ለአጉል እምነት ይዳረጋል” ይላል።

“መሃቪራ መሃቪራ፣

እየቆረጠ ሰጠው ላሞራ።”

እንዲል ጋሼ ስብሃት።

ጋሼ ስብሃት የመሃቪራን ሃሳብ አስታኮ ትዳርና ፍርሃት ያላቸውን መገፋፋት ወግ መዞ በእንዲህ መልኩ ይገልጠዋል። ወጣቱ የሱ በጋብቻ ለወግ ማዕረግ መብቃት የወላጆቹን ፍቅር የሚያጎድልበት መስሎ ስለተሰማው ፈቃዱን ተጭኖ ስለነሱ ለመኖር ስሜቱንና ፍላጎቱን አሸነፈ፤ ካፒቴን ሙሉም “ያለኔ ማንም የላቸውም” በሚል ስጋት እንስፍስፍ አንጀቷን ቀይዳ ስለቤተሰቦቿ ስትል እድሜዋን ገበረች። እንዲህ አይነቱ መንፈሳዊ ጽናት እሷነቷን ገንብቶ ከዓላማዋ ፈቅ ባያደርጋትም ዓለሟን ለሻቱ ወላጆቿ ግን የልቦና ቁስል እንደሆነ እናቷ በእንባ ዶፍ እየታጠቡ አዋዩኝ።

ቀናት ተመሳቅለው ጊዜ እየሾረ፣

ትናንት እስከዛሬ እንዲህም ተኖረ።

ነገስ?

በሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You