ያልዘሩትን ማጨድ!

ወልዶ እንጂ ሰርቆ መሳም፣ ካልዘሩበት ማሳ መልቀም ኪነታዊ ስርቆት ነው። የለበሱት የጥበብ ሸማ ቢመሳሰል፣ ኪስህ ኪሴ ተብሎ አይገባም። ምክንያቱም አዋጅ ቁጥር 410/96 የሚለው ይሁንኑ ነው። ‹አትስረቅ፣ አትገደል፣ አታመንዝር፣ የባልንጀራህን አትመኝ…› የአሥርቱ ትእዛዛት ቃለ አንቀጾች ቢሆኑም፤ 410/96’ን የሚተላለፍ ሁሉ በተዘዋዋሪ የሚፈጽመው እኚህኑ ነው።

በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ስር ያሉ ማንኛቸውንም ህግ የጣሰ፣ ያልዘራውን ለማጨድ ማልዶ ለስርቆት እንደሚወጣ ሌባ ነው። ያውም የሚሰርቀው ቁስ ሳይሆን አዕምሮን ነው። የአንዱን የፈጠራ ሥራ በሰረቀበት ቅጽበት የባለቤቱን ሕይወትና ጥበብ እንዲሁም የራሱንም ጥበብ ይገድላል። ከምኞት ሁሉ የከፋው ምኞት የባልንጀራን መመኘት ነው። ያዩትን የሰሙትን ነገር ወድጄዋለሁ ተብሎ ያለፈቃድ መጥለፍ ምንዝርና ነው።

ባለቤትነቱ የሌላ ሰው ከሆነ ሥራ ላይ እየዘገኑና እየቆራረጡ ወይም አስመስሎ እንደ አዲስ ፈጠራ ማቅረብ፤ በትዳር ላይ ትዳር ደርቦ እንደማማገጥ ነው። በድብቅ አዳቅለው የሚያመጡት የጥበብም ፍሬም እንዲሁ ነው። ለአንድ የፈጠራ ሥራ እንደ አስፈላጊነቱ እቁባቶች ይኖሩት ይሆናል፤ ፈጽሞ ግን ውሽማ አይሻም። የራሱ እንዳልሆነ ልቡ እያወቀ፣ ሥራው የኔ ነው ብሎ ሲመጣ፣ በሐሰት ለራሱ መመስከሩም ነው። ከሰው ጥበብ ሰርቆ፣ በሰው ጥበብ ደምቆ ለመታየት መሞከር በሕግጋቱ ውስጥ የአዕምሮ ውስልትናም ጭምር ነው።

ይሁንና…እንደ እኛ ሀገር የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ፤ ይህ ሁሉ ምን ያህል እውነት ነው? ብለን ከጠየቅን፣ እጅግ ግነት የበዛባቸው ዐረፍተ ነገሮች እንደሚሆኑ አያጠራጥሩም። ምክንያቱስ? ስንል ደግሞ፤ የመጀመሪያው ነገር ሀገራችን የዓለም አቀፉን የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ስምምነት ባለመፈረሟ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፤ በአዕምሯዊ ንብረቶች ባለቤትነት በራሷ ለራሷ የቀረጸችውን የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ፣ ሕጉን ከመፈጸምና ከማስፈጸም ረገድ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሳያስገኝ ቆይቷል። ከወዲህኛው ሰሞን ግን አንድ መልካም ነገር ብቅ ያለ ይመስላል።

ጥበብ ባሳለፍናቸው ሳምንታት ውስጥ ከሰማቻቸው አበይት ብሥራቶች መካከል አንደኛው ይህን የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን የሚመለከት ነው። ለዘመናት ከጉያችን ስር የበቀለ አረም ሆኖ፣ የጥበብ ኢንዱስትሪውንና የኪነት ሰዎቻችንን ደም ሲመጥና ሲመዘምዝ የኖረ ነገር እንደመሆኑ፣ ሰሞነኛውን ሁነት እንደመልካም ብሥራት ያስቆጥረዋል። መልካሙ አጋጣሚም፣ የሦስትዮሽ ጥምረት የተካሄደበት ነው።

በሀገራችን “አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን” የሚሰኝ ጠባቂ ተቋም መኖሩ የሚታወቅ ነውና አንደኛው ይሄው ነው። ሁለተኛው፤ በኢትዮጵያ የጥበባት እንቅስቃሴ ውስጥ ግዙፍ ዐሻራውን ማኖር የጀመረው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ነው። ሕገ ወጡን ተዛማጅነት ለመከላከልና ለመገሰጽ ራሱን በባለቤትነት ያቀረበው ሌላኛው ደግሞ፣ “መልቲ ቾይስ አፍሪካ” የተሰኘው ሠናይ ኩባንያ ነው። በጋራ ለመሥራትና በጋራ ለመከላከል፣ የአዕምሯዊ ንብረቶችን ባለቤትነት በመጠበቅና መብቶችን በማስጠበቅ፣ የጥበብ ኢንዱስትሪዎችንና የፈጠራ ጠቢባኑን ሥራዎች በማስከበር፣ ጥበብን ለማልማትና ለማለምለም የሦስትዮሽ የውል ስምምነት ተፈራርመዋል። በወረቀት ላይ የሰፈረ የፊርማ አጀብ ብቻ ሆኖ እስካልቀረ ድረስ፣ ብሥራታዊ ለውጥ ማምጣት የማይቻልበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

‹ተዛማጅ የቅጂ መብቶች› ወይንም ‹የአዕምሯዊ ፈጠራ ሥራዎች ባለቤትነት› ሲባል ግን እንዴት ይሆን የምንረዳው? መብቱን ለመጠብቅና ለማስጠበቅ ገና መሆናችን ብቻ ሳይሆን፤ የስያሜው ትርጉምና ምንነትም በቅጡ ያልገባን ሆኖ ይስተዋላል። በየትኛውም የኪነት ዘርፍ ውስጥ፣ በማንኛውም ዓይነት መንገድ ከዚህ ቀደም ከነበረ ሥራ ጋር አመሳስሎ መሥራት፣ ቆርጦ መቀጠል፣ ከመሃል ሃሳብ መስረቅ፣ ያለ ፈቃድ ማባዛት፣ በሕገ ወጥ መንገድ ማሰራጨት፣ የፈጠራ ባለቤቱን ዕውቅና መግፈፍ እና መሰል ተግባራት ሁሉ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥሰት ነው።

“ቅጂ” ሲባል አንድም ‹ምስልና ድምጽ መቅዳት› እንደምንለው፣ ሁለትም “ኮፒ” ማድረግ ነው። ከፈተና አዳራሽ ውስጥ ከማዶ ጠረጴዛ አንገት ሰቅሎ የጎበዙን መልስ መቅዳት፣ የሰውን ወስዶ ከዋናው ላይ በካርቦን ኮፒ ሠርቶ ማውጣት ስርቆት ነው። ከሰው ባህር በታንከርም ቀዳን በጭልፋ፣ ስርቆት ያው ስርቆት ነው። “ተዛማጅ” ሲል ከቅጂው ጋር የሚካተቱ መሰል ተግባራትን ለመግለጽ ነው። በሁለተኛው ትርጓሜው፤ በሁለት ሥራዎች መካከል ሊኖር የሚገባን ርቀትና መዛመድ የሚችሉበት መጠንን ያመለክታል። ሦስተኛው ፍቺ ስርጭትን አመልካች ነው። የቃላቱ ብዝሃ ትርጓሜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአዋጅ ቁጥር 410/96 ከተደነገጉ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ጋር የሚሄዱ ናቸው።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን ስምምነት ብትፈርም መልካም ይሆን ነበር? ወይንስ አለመፈረሟ በጀን? ይህን ውል ለመፈረም ምን አስፈራት? ጉዳዩን ለሁለት ከፍለን ልንመለከተው እንችላለን። በመጀመሪያ ልንለው የምንችለውና ከፊት የተቀመጠው አንድ እውነት፤ ሀገራችን ውሉን መፈረሟ ለፈጠራ ባለቤቶች ትልቅ እፎይታን የሚሰጥና በሥራዎቻቸው የሚገባቸውን ለመጠቀም ይችሉ ነበር። ነገር ግን፤ ከበስተጀርባ ያለው ነገር ለብዙኃኑ ሰቀቀን ነው። ጉዳዩ በኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የፈጠራ ባለቤትነትን የሚመለከት ነው። ኢትዮጵያ የዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነት አባል ሆነች ማለት፤ ገና በማደግ ላይ ላለች ሀገር ተራራውን እየቆፈሩ ሜዳ እንደማድረግ ነው። የኋላ ኋላ ጥሩ ነገር ቢኖረውም፣ አሁናዊ ሁኔታውን ለመቋቋም አዳጋች ነው።

በጣም ቀለል ካለው ነገር ስንጀምር፣ የእጅ ስልካችንን ከፍተን ወደ ‘Google play store` በመግባት፣ ኢንተርኔትን በመጠቀም ብቻ የምንፈልገውን መተግበሪያ እንጭናለን። ሀገራችን የዓለም አቀፉ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች አባል ብትሆን ኖሮ ግን ይህን ለማድረግ አይቻለንም። የፈጠራውን ባለቤት መብት መጠበቅ ስለሚኖርብን ግብይት መፈጸም ይኖርብናል። ይህ ማለት እንግዲህ የምንፈልገውን መተግበሪያ በስልካችን ለመጫን የተተመነለትን የዋጋ መጠን መክፈል ይኖርብናል ማለት ነው። ‘Apple store` በሀገራችን ውስጥ አገልግሎት የማይሰጥበት ምክንያትም በዚሁ ነው። በእጅ ስልኮቻችንና በኮምፒተሮቻችን ውስጥ የሚሠሩ እያንዳንዱ ሶፍትዌሮችና መተግበሪያቸው አገልግሎት የሚሰጡን ግዢ በመፈጸም ብቻ ነው። ስለዚህ በመተግበሪያዎቹ ውስጥ የሚገኙትን የጥበብ ሥራዎች ለማግኘት ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር ክፍያ እንጠይቃለን። ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ድራማ…የቱንም ለማውረድ ኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን፣ ለሥራዎቹ መክፈል ይኖርብናል። ልክ ለ`DSTV’ እንደምንከፍለው ሁሉ በኮምፒተሮቻችንና በስልኮቻችን ለሚገኙ ተጨማሪ አገልግሎቶች፣ በሁለት መንገድ ክፍያ ወይም ‘Subscription` እንፈጽማለን። ወርሃዊ አሊያም ሳምንታዊ፣ ወይንም ደግሞ በሰዓቱ ላስፈለገን አገልግሎት ስንከፍል ብቻ ይሆናል።

እንዲህ ባለመልኩ የምንጓዝ ቢሆን ኖሮ ለሥራዎቹ ባለቤቶች የሚያስገኘው የተትረፈረፈ በረከት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ማወቁ ሳይታለም የሚፈታ ነው። ነገር ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ስንቱ ነው ከፍሎ ሙዚቃና ፊልም የሚያወርድ? ቢፈልግስ የመክፈል አቅም ያለው ምን ያህሉ ነው? የኪነ ጥበብ ሥራዎቻችን ሁሉ ከሕዝቡ ተገንጥለው መኳረፋቸው ነበር። ይሁንና የሀገራችን የፈጠራ ባለቤቶች መጎዳት ስለሌለባቸው፣ ኢትዮጵያ በራሷ መንገድ ከምታደርገው የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ጎን ለጎን፣ ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀሙ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

ለምሳሌ፤ ከሙዚቃ ሥራዎች አንጻር እንደ “ሰዋ ሰው”ያሉ መተግበሪያዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። ሙዚቀኞቹም ሳያመነቱ ሥራዎቻቸውን ወደዚያው ማሸሹን ቀጥለዋል። ከዚህ መተግበሪያ ላይ የምንፈልጋቸውን ሙዚቃዎች ልናወርድ የምንችለው፣ ከላይ ያነሳናቸውን ዓይነት ክፍያዎችን ስንፈጽም ብቻ ነው።

ከዓመታት በፊት “The Ecomomist” የተሰኘው ተቋም ገጹ ላይ ያሰፈረው አንድ መረጃ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆነናል። ጉዳዩ አዲስ አበባ ላይ የተገኘ አንድ በርገር ቤትን የሚመለከት ነው። ተቋሙ እንዳወጣው መረጃም፤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሲንሸራሸሩ የነበሩ ቱሪስቶች ድንገት በርገር ቤቱን ይመለከታሉ። የበርገር ቤቱን ስም ሲያነቡ ግን መደሰት ብቻ ሳይሆን በጣም ተገረሙ። ያስገረማቸው ነገር፤ ፈጣንና ተወዳጅ ምግቦችን በማቅረብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው ድርጅት፣ አፍሪካ ውስጥ ቅርንጫፍ በመክፈቱ ነበር። በተዘዋወሩባቸው ዓለማት ሁሉ የዚህ በርገር ቤት የዘወትር ታማኝ ደንበኞች በመሆናቸው ለማለፍ አልቻሉም። እናም በመገኘቱ እየተገረሙ፣ ስላገኙትም እየተደሰቱ ወደ ቤቱ ገብተው፣ ከዚህ ቀደም ምርጫቸው የነበረውን የበርገር ዓይነት ያዛሉ። ያዘዙት ደርሶም ከጠረጴዛው ላይ ቁጭ ቁጭ አለ።

ቱሪስቶቹ የሚወዱትን አግኝተው ገና ከመቅመሳቸው ግን፣ ጣዕሙ ያ የሚያውቁት በርገር አይደለም። በአውሮፓና አሜሪካ በልተው በደስታ እያመሠገኑ ሲወጡ ቆይተው፣ በአዲስ አበባው ቅርንጫፍ ቅር ተሰኝተው ወጡ። በኋላ ሀገራቸው ሲመለሱ ወደ ድርጅቱ ይሄዱና “ምነው እንዲህ ጉድ የሠራችሁን? ኢትዮጵያ ውስጥ የከፈታችሁት በርገር ቤት የእናንተን ስም የሚመጥን አይደለም” በማለት አቤቱታ ያቀርባሉ። በነገሩ ግራ የተጋባው የድርጅቱ ባለቤትም “ኧረ በጭራሽ! እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ሱቅ የለኝም። ማነው በስሜ እየነገደ ያለው?” ድርጅቱም በሁኔታው ተደናግጦና ተናዶ ክስ ለመመሥረት ወደ ዓለም አቀፉ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ገሰገሰ። ነገር ግን፤ ኢትዮጵያ ይህን ውል ፈርማ አባል አልሆነችም ነበርና የአዲስ አበባው በርገር ቤትም፣ ከሚሊዮን የካሳ ገንዘብ መቀጮና ከመዘጋት ዳነ።

እንግዲህ ስምምነቱን ኢትዮጵያ ፈርማ ቢሆን ኖሮ እነማን ከተጠያቂነት እንደምንድን ቤቱ ይቁጠረው ። ለበርገር ቤቱ ብቻ ሳይሆን፣ ለኪነ ጥበብ እና ለሌሎችም ማሳያና መማሪያ ነው። ይህን ስንመለከትም ሀገራችን ስምምነቱን አለመፈረሟ፤ እሰይ አበጀች! እንኳንም አልፈረመች ያስብላል። ነገር ግን፤ ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዳር ይዘን ብንቆይ እስከ ማዕበሉ ነው። ምክንያቱም ዓለም ግስጋሴዋ ወደዚያው ነውና። ሁሌም በዚሁ እንቀጥላለን ብለን ማሰብ የለብንም። ብቻችንን አፈንግጠን፣ ከዓለም ተነጥለን፣ ከዓለም አቀፋዊነት ተገልለን ልንኖር አይቻለንም።

አሁንም ባለንበት የሚከተለን ጥያቄ ግን፤ አዋጅ ቁጥር 410/96 ምን ያህል ሥራውን እየሠራ ነው? አዋጁ ከጸደቀ 21 ዓመታት ቢያልፉም፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ዕድሜውን ያሳለፈው በእንቅልፍ ነው። በቅርቡ የተመሠረተው የሦስትዮሽ ጥምረት በሚገባ ለመቀስቀስ እንደሚሠራ የሁሉም ተስፋ ነው። አዲሱ ጥምረት የመጀመሪያ ሥራው መሆን ያለበት ግንዛቤ ማስጨበጡ ላይ ነው። ምክንያቱም አብዛኛው የኪነት ባለሙያም ሆነ ጥበብ አፍቃሪው ማህበረሰብ፤ እስከዛሬ የቆየውን አዋጅ በቅጡ ያውቀዋል ለማለት አያስደፍርም። እንደ አብነት በሙዚቃ ዘርፍ ውስጥ ያለውን ብንመለከት፣ ብድግ! ተብሎ በዘፈቀደ ያሻንን ማድረግ የተለመደ ነው። አሁን በረደ እንጂ፣ በአንድ ሰሞን “ከቨር” የሚባል ወረርሺኝ ተንሰራፍቶ ነበር።

ድምጽ ያላቸው ወጣቶች ሁሉ እየተነሱ፣ ከሩቅም ከቅርብም ዘመን ላይ የተሠሩ ሙዚቃዎችን ዳግም ስቱዲዮ አስገብተው ሲሠሯቸው ነበር። መሥራቱ ባልከፋ፤ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ፈቃድ ያልተጠየቀባቸው ናቸው። የከፋው ነገር ደግሞ፤ በ 5 እና 6 ስድስት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት አራት ሙዚቃዎች ከመታጨቃቸውም ግጥሞቹ ሳይቀሩ ይደበላለቁበታል። የተለያዩ ድምጻውያንን በምት የሚመሳሰሉ ሥራዎች፣ እንደ አንድ ወጥ ሙዚቃ አድርጎ ለመሥራት ሲባል ግጥምና ዜማዎቹ፣ ከነበረውን አንጻር ተወላግደውና ተንሻፈው የተደመጡት አሉ።

በዋናው ሥራ ውስጥ ገና ከመግቢያው የምናውቃቸውን ሙዚቃዎች ተደባልቀው ስንሰማቸው “ኧረ ይህን ሙዚቃ አውቀዋለሁ ልብል? የማን ነበር…የማን? ምን የሚለው?” እያልን ራሳችንን የጠየቅንባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። በዚህን ያህል ደረጃ የምንዳፈረው በሁሉም የኪነት ሥራዎች ውስጥ ነው። እናም መጀመሪያ ላይ ልናጠፋው የሚገባው ጠላታችን አለማወቃችንን ነው።

በከፍተኛ ሁኔታ በሀገራችን የተለመደና ነውር የሌለበት ጽድቅ ተደርጎ የሚቆጠር ነገር ቢኖር የሃሳብ ስርቆት ነው። ከዚህም ከዚያም እየቆነጠሩና እየቆራረጡ ገጣጥሞ መሥራት ነውር ነው። ውስጥ ውስጡን ደግሞ አስገዳጅ ሁኔታዎችም አሉበት። በቅድመ ሁኔታዎች፣ በገንዘብና በሌላም የውዴታ ግዴታ በማቅረብ፣ በተለይ በየስርቻው ያሉ የጀማሪያንን ሥራዎች በመቀበል እንደራሳቸው የሚያቀርቡ፣ ከበፊቱ ይሻል እንጂ አሁንም ደፍሮ የሉም ለማለት የሚችል የለም። አንዳንድ ድፍረቶች ግን እጅጉን አስገራሚም ጭምር ናቸው።

መጽሐፍን ያህል ነገር፤ ደራሲው በሕይወት እያለ፣ ከዚህ ቀደም ለንባብ የበቃውን መጽሐፍ በድብቅ እያሳተሙ ሲሸጡ የተደረሰበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። ለአብነት የገጣሚ ኤፍሬም ስዩም “ተዋነይ” አንደኛው ነው። ሌላ አንዱ ደግሞ፤ ብልጣ ብልጥነት ይሁን አላዋቂነት…የዶክተር ዳኛቸው አሰፋ አድናቂና የሃሳቦቹ ምርኮኛ ነኝ በማለት፤ የዳኛቸውን ትንታኔዎች ሰብስቦ “የዳኛቸው ሃሳቦች” የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ያሳትማል። የዚህ ሰው ድርጊት፤ ስለ ቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ያለን ዕውቀትና ግንዛቤ ገና ‹ሀ ሁ› የሚያስፈልገው እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ይህን ማድረግ የሚችልበት ዕድል ቢኖረውም፤ ትልቁ ጥፋቱ ከባለቤቱ ወይንም ከሕጋዊ ወራሹ ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት አለማወቁ ወይንም አለመፈለጉ ነው። እኚህ ሁለት ምሳሌዎችም ፍርድ ሸንጎ ላይ ቆመው፣ በአዋጅ ቁጥር 410/96 የተበየነባቸው ናቸው። በትርጉም መጻሕፍት ምክንያት የፍርድ ቤት መዝገብ የሞሉትን ጉዳዮች ግን ‹ተከድኖ ይብሰል› ማለት ይሻላል።

በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ሕግ መሠረት መጠበቅ ያለብን የራሳችንን ብቻ አይደለም። ትልቅ ክፍተትና ስርቆት ከሚታዩብን ነገሮች ውስጥ፤ የውጭ ሀገራት ሥራዎችን እያመጣን ለመከለስ ባለን ድፍረትም የምንታማ አይደለንም። ‹ቀባ ቀባ› የምትል አንዲት ፈሊጥ አለች። በተለይ በፊልም ማጀቢያዎቻችን፣ በተለይ ደግሞ በአንዳንድ ሙዚቃዎቻችን…የበርገሩን ዓይነት ጉዶችን ነው የተሸከምነው። የቱንም ያህል ቀባ! ቀባ! ቢያደርጉት የሰው ነገር የሰው ነውና ፈጦ በአደባባይ መውጣቱ አይቀርም። እንግዲህ መብት ጥበቃ ከተባለ፤ ለአዲሱ የሦስትዮሽ ጥምረት እኚህን መሰል የጓዳ ንቅዘቶችም ትልቅ የቤት ሥራ ናቸው።

የሚሰረቁትን ብቻም ሳይሆን የሚሰርቁትንም የፈጠራ ችሎታ የሚቀብረውን ይህን ሕገ ወጥ የሆነ ተዛማጅነት በቃ ሊል ይገባዋል። የሚሰርቀውን ጠብቆ ከመቅጣት በላይ፣ በማስተማርና ግንዛቤ በማስጨበጡ ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሠራ የተሻለ ለውጥ ለማስገኘት ይችላል። የሦስትዮሽ ትብብሩንም አድማሱን በማስፋትና ከስር ሌሎች ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸውን በማስከተል፣ ሰንሰለታማ ቅንጅት ፈጥሮ እስከታች ማውረድ ያስፈልጋል። የፈጠራ ባለቤቶችን መብት መጠበቅና ተጠቃሚነታቸውን መጨመር ይጠበቅባቸዋል። “በልጅ አመሃኝቶ ይበላል አንጉቶ…በጨው ደንደስ በርበሬ ትወደስ” እንደሚሉ ዓይነት አጨዳዎች ከእንግዲህ መገታት ይኖርባቸዋል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You