አረንጓዴ ዐሻራችን ለልምላሜያችን

ኢትዮጵያን ለማወደስ ከሚዜሙ እና ተደጋግመውም ከሚደመጡ የዜማ ስንኞች መካከል “ውቢቱ ኢትዮጵያ”፣ “ለምለሚቱ ሀገሬ”፣… የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ውብ ተፈጥሮ፣ ጥብቅ የደን ሀብትና ከፍ ያለ የአረንጓዴ ልባስ ባለቤት ስለመሆኗ እንዲናገሩ ተደርገው የተሰደሩበትን እውነትና ሁነት ይገልጻል።

ይሁን እንጂ ታሪክ እና ኑረት ለየቅል ሆነው፤ የኢትዮጵያ ውበትና ልምላሜ ተነጣጥለው መኖር ከጀመሩ ብዙ አስርት ዓመታት አልፈዋል። ምክንያቱም፣ ያኔ ኢትዮጵያ ውብና ለምለም በምትባልበት ወቅት፤ የደን ሽፋኗ ከ40 በመቶ የላቀ ነበር። ጋራ ሸንተረሯ በአበቦች የፈካ፤ የወንዞቿ ፏፏቴ ድምጾች፣ የአዕዋፍቱም ዝማሬዎች ድንቅ ተመስጦን የሚፈጥሩ ነበሩ።

ዛሬ ግን ይሄ ታሪክ እንጂ እውነት አይደለም። እንዴት ቢሉ፤ ለምሳሌ፣ ከአምስት ዓመት በፊት በነበረው መረጃ መሠረት፣ ጥብቅ ደኖቿ ተጨፍጭፈው ከ40 በመቶ ይልቅ የነበረው የደን ሽፋኗ ወደ ሦስት በመቶ አሽቆልቁሎ ነበር። በዚህም የውሃ ሀብቶቿ እየደረቁ፣ አዕዋፋቱም ማረፊያ እያጡ፣ በፋፋቴዎችና በአእዋፍ ዝማሬዎች ክሱት ሆነው የሚገለጡ ውበቶቿም ደብዝዘው ኖረዋል።

ከእዚህ አለፍ ሲልም ኢትዮጵያ ዓለማችንን በብዙ መልኩ በእጅጉ እያስጨነቃት የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ገፈት ቀማሽ ወደ መሆን ተሸጋገረች። የክብር ልብስና ካባ የሆናት የደን ሀብቷ ሲገፈፍ እርቃኗን በመቅረቷ፤ በአንድ በኩል ጎርፍ አፈሯን ይጠርገው፤ በአንድ በኩል ድርቅ አሳሯን ያበላት ያዘ። ዜጎቿን ለረሃብና መፈናቀል፤ የእንስሳት ሀብቷን ለእልቂት፤ የተፈጥሮ ሀብቶቿንም ለመመናመን ዳረገባት። በጥቅሉም ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ሰደድ እሳትና ሌሎችም ክስተቶች የዜጎቿን ሕይወትን ፈታኝ አድርገውባት ቆይተዋል።

የችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሄድን የተመለከቱ መንግሥታትም ለችግሩ መንስኤ ሰው ነውና፤ መፍትሄውም ከራሱ ከሰው ሊመነጭ ስለሚገባው የመፍትሄው አካል ወደመሆን ገቡ። በዚህ በኩል ታዲያ ሁሉም እንደየችግሩ አይነት የመፍትሄውንም አይነት መንደፍ ጀመረ። ለምሳሌ፣ በካይ ጋዝ ወደ ከባቢ የሚለቅቁ ሀገራት፤ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠናቸውን መቀነስ፤ የደን መመናመንን የፈጠሩ ሀገራትም እንዲሁ ደኖችን መልሰው እንዲያገግሙ ወደ ማድረግ ተሸጋገሩ።

እነዚህ ተግባራት ታዲያ በሚፈለገው ልክ ተጉዘው የሚፈለገውን ውጤት አምጥተዋል ማለት ባይቻልም፤ እንደየአተገባበር ቁርጠኝነታቸው ግን በየሀገራቱ የታዩ ጅምር ለውጦች አሉ። በዚህ በኩል፣ ወደ ከባቢ የሚለቀቅ በካይ ጋዝን ከመቀነስ አኳያ የታየው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይልቁንም ሲጨምር እንጂ ሲቀንስም አልታየም።

የተመናመኑ ደኖችን እንዲያገግሙ የማድረጉም ተግባርም ሆነ፤ ጥብቅ ደኖች ባሉበት ተጠብቀው እንዲቆዩ የማድረግ ሂደቱም ተግዳሮት የራቀው አልነበረም። ምክንያቱም፣ በአንድ በኩል የደን ሀብትን ጥቅም ላይ የማዋሉ ልምምድ እየጨመረ መምጣት የነበሩ ደኖች ባሉበት እንዳይቀጥሉ እያደረገ ይገኛል። በሌላም በኩል የሰደድ እሳትና ሌሎችም ክስተቶች ለደን መመናመኑ አለመገታት ምክንያት እየሆኑ ይገኛል።

ከእዚህ ባሻገር፣ የጠፉ ደኖችን መልሶ በመተካት ወይም ደኖች እንዲያግገሙና ወደነበሩበት እንዲመለሱ የማድረግ ሂደቱ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑ ይነሳል። በዚህ ረገድ የሚነሳው ሀገራት ችግኞችን በመትከልና ደኖችን በማልማት ሂደት ላይ የፋይናንስ ጉዳይ ትልቅ እንቅፋት ሆኗቸው የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ተስኗቸው መታየታቸው ነው።

ኢትዮጵያም በዚህ በኩል ቀደም ብላ በተፋሰስ ልማት እና በሌሎችም መርሃ ግብሮች ሥራውን የጀመረች እና ጅምር ውጤቶች የታዩ ቢሆንም፤ አንድም የተቀናጀና የተደራጀ አሠራር ባለመፈጠሩ፤ ሁለተኛም ከፋይናንስ አቅም ጋር በተያያዘ፤ አለፍ ሲልም የሕዝቡን የባለቤትነት ስሜት መፍጠርና ማሳደግ ባለመቻሉ ምክንያቶች ውጤቱን ማዝለቅ፣ ሥራውንም ከዳር ማድረስ ሳይቻል ቀርቷል።

እንደ ሀገር ለበርካታ ችግሮቻችን መፍትሄን ይዞ ከመጣው ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ግን፤ እንደሌሎች ሀገራዊ ችግሮቻችን ሁሉ ለአካባቢ ጥበቃ ሥራው ችግርም የ “አረንጓዴ ዐሻራ”ን መፍትሄ ይዞ የመጣ ነበር። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥራውን በጀማሪነትም፣ በመሪነትም ባለቤት ሆነው የያዙት እንደመሆኑ፤ እንደ ሀገር የችግሩ ስር እንዲነቀል፤ እንደ ዓለምም ለዘርፉ ፈተና የመፍትሄ ጡብ ያስቀመጠ ውጤት ማምጣት ተችሏል።

ይሄ ተግባር በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ታግዞ በ2011 ላይ በአዳማ ገልማ አባ ገዳ ጊቢ ውስጥ አንድ ብሎ የችግኝ ተከላው ሲጀምር፤ በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ አስቀምጦ ነበር። በመጀመሪያው ዓመት መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግላቸው አንድ ሺህ ችግኞችን እንደሚተክሉ ቃል በመግባት፤ በመርሃ ግብሩ አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል አቅጣጫ በማስቀመጥ ሕዝቡን የማነሳሳት ሥራን ሠሩ።

ይሄም ብቻ ሳይበቃ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ልዩ መርሃ ግብርን ይፋ በማድረግ፤ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀንበር (በአንድ ቀን) 354 ሚሊዮን ያህል ችግኞችን በመትከል፤ በዓመቱ ማጠቃለያም በእቅድ ከተቀመጠው አራት ቢሊዮን ችግኞች በላይ በመትከል ለመርሃ ግብሩ የተቀመጠው ግብ መሳካት አይቀሬነትን ማየት የተቻለበት ተግባር ተገለጠ።

በኮቪድ እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ተሆኖ በ2012 የተተገበረው በሁለተኛው ዙር መርሃ ግብርም፤ እንደ መጀመሪያው ሁሉ ሚሊዮኖች ተሳትፈውበት፣ ሪከርድ የሆነ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ተከናውኖበት በጥቅሉም በእቅድ ከተቀመጠው አምስት ቢሊዮን ችግኞች በላይ በመትከል ነበር የተጠናቀቀው፡፡

ሦስተኛው ዓመት መርሃ ግብርም፣ በተመሳሳይ የዜጎች ተሳትፎና ተግባር ታግዞ በእቅድ ከተቀመጠው ስድስት ቢሊዮን ችግኞች በላይ በመትከል በስኬት አለፈ። የዚህኛው ዓመት መርሃ ግብር ለየት የሚያደርገው ግን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ድንበር ተሻጋሪ የሆነን ሥራ የሠራችበት፤ በጎረቤት ሀገራት ሄዶ ችግኝ መትከል የተቻለበትም መሆኑ ነበር። በጥቅሉም በሦስቱ ዓመት ተግባራት 18 ቢሊዮን ያህል ችግኞችን መትከል ተችሎ ነበር።

ሰባት ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ የተያዘበት አራተኛው ዓመት መርሃ ግብርም፤ በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ከእቅዱ በላይ ችግኞች ተተክለውበት፣ ለአራት ዓመቱ የተቀመጠውን ግብ ከማሳካት ባለፈ፤ በአራቱ ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞች እንዲተከሉ አስቻለ።

በመሆኑም በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ በተሠራው ሥራ፣ የእቅድ ዓመቱ የተጠናቀቀው 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ነበር የተጠናቀቀው። በአራት ዓመታት ተቀንብቦ የቀረበው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም በዚህ መልኩ ከእቅድ በላይ ተፈጽሞበት፤ ኢትዮጵያንም የአረንጓዴ ሸማ ልብሷን መጠን አሳድጎ ነበር ለሁለተኛው ምዕራፍ ተራውን ያስረከበው።

የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም፣ በአራት ዓመታት ውስጥ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል፤ በድምሩ በስምንት ዓመቱ 50 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ግብ በማስቀመጥ ነበር በ2015 ላይ ጉዞው የተጀመረው።

በዚህ መሠረትም ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ የመጀመሪያው ዓመት በስኬት የተጓዝንበት ሲሆን፤ በ2016 ዓ.ም ለስድስተኛ ጊዜ በተከናወነው ሥራ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ615 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል የተቻለበትን ተግባር መፈጸም ተችሏል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የተተከሉ 25 ቢሊዮን ችግኞች ጨምሮ በሁለተኛው ምዕራፍ ማጠቃለያ ዓመት ላይ 50 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ውጥንን በማሳካት ሂደት፤ እስካሁን ከ40 ቢሊዮን የተሻገረ ችግኝ መትከል ተችሏል። ይሄ ደግሞ እቅዱን ከማሳካት በላይ የሚያራምድ ሲሆን፤ የሕዝቡ ተሳትፎና የባለቤትነት መንፈስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ፤ እንዲሁም ሥራውን ከዘመቻ ሥራነት ወደ እለት ተዕለት የሥራ ልምምድ ማሸጋገሩ ለዚህ ተጠባቂ ውጤት አይቀሬነት ማረጋገጫ ይሆናል።

ይሄው ተግባር በዘንድሮው ክረምትም የሚቀጥል ሲሆን፤ ለዓመቱ የተቀመጠውን እቅድ ከማሳካትም ሆነ የአራት ዓመቱን ግብ ከማሳካት አኳያ ታቅዶ እየተከናወነ ይገኛል። ሂደቱም ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ ውጤታማ ስለመሆኑም ባለድርሻዎች ከወዲሁ እየገለጹ ሲሆን፤ እንደቀድሞው ሁሉ ዘንድሮም ሥራው በውጤትና ስኬት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

በእዚህ መልኩ ሥራው በስኬት ታጅቦ ለመዝለቁ ዋናው ምክንያት ደግሞ፤ አንድም ሥራው ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው በመደረጉ እና ሕዝቡም የባለቤትነት ስሜትን በመላበሱ ምክንያት ነው። ይሄ ደግሞ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። ከ20 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ማሳተፍ እና በአንድ ጀምበርም ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ያስቻለን ሰፊ የንቅናቄ ሥራ ተሠርቶ ነው። ከዚህም በላይ ሕዝቡ ችግኞችን በመትከሉ እና ተንከባክቦ ለውጤት በማብቃቱ የሚያገኘውን ጥቅም ከወሬ ባለፈ በተግባር እንዲያየው፤ እንዲያጣጥመውም በመደረጉ ነው።

ምክንያቱም፣ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ መቶ ሺዎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፤ ሚሊዮኖችም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ካላቸው ችግኞች የሚገኘውን ውጤት እንዲያጣጥሙ ሆነዋል። እንደ ሕዝብም፣ እንደ ሀገርም ከችግኞቹ ከፍ ያለ ፋይዳን ማግኘት ተችሏል። ይሄ የሆነውም የሚተከሉ ችግኞች የደን ሽፋንን ብቻ እንዲያሳድጉ ታስቦ የተተከሉ አይደሉም። ይልቁንም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው እንደ ቡና፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ አፕል፣… የመሳሰሉትም ጭምር ናቸው።

እነዚህ ችግኞች ደግሞ ዛሬ ላይ ሀገራዊ የፍራፍሬ ፍላጎትን ከማሟላት አልፈው፤ ለኤክስፖርት ዘርፉ አቅም፣ ለኢንዱስትሪዎችም ግብዓት እየሆኑ መጥተዋል። እናም ሕዝቡ ከችግኝ ተከላ የሚያገኘው ጥቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ባለቤት ሆኖ እየተሳተፈበት ይገኛል። ለዚህም ነው ከሃያ እና ሰላሳ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊም፣ ባለቤት ሆኖ መዝለቁ።

ሌላኛው የውጤታማነቱ ጉዳይ፣ መርሃ ግብሩ በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ እየተመራ መሆኑ ነው። ሥራው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ፣ ሚኒስትሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ሌሎችን በየደረጃው በባለቤትነት ይዘው የሚመሩትም፤ የሚሳተፉበትም ነው። በዚህ መልኩ መመራቱ ሕዝቡም በልበ ሙሉነት እንዲሳተፍ እና ሂደቱ ውጤታም እንዲሆን አግዟል።

ከእዚህ ጋር የሚታየው አንኳር የውጤታማነቱ ጉዳይ ደግሞ፤ የፋይናንስ ምንጭ ጉዳይ ነው። ብዙዎች ጀምረው ከዳር ያልደረሱበት፤ ኢትዮጵያ ግን ጀምራ በውጤት እንድትጓዝ ካደረጓት ጉዳዮች አንዱም ይሄው የፋይናንስ ምንጭ ጉዳይ ነው።

እንደ ሀገር ለመርሃ ግብሩ መሳካት ከፍ ያለ መሻት ብቻ ሳይሆን፤ ከልብ የሆነ መነሳሳት ተይዞ በቁርጠኝነት እየተተገበረ ይገኛል። በዚህ መልኩ ለሚደረግ ትግበራ እንቅፋት የሚሆነውን የፋይናንስ ችግር ከመፍታት አኳያም፤ ሥራውን ሕዝባዊ የማድረግ ነበር። እናም መላው ኢትዮጵያውያን ያለ ክፍያ እንዲሳተፉበት እና የራሳቸው ሥራ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

በመሆኑም፣ መርሃ ግብሩ የየትኛውንም መንግሥትና ተቋም እጅ ማየት ሳያስፈልግ፤ ከመንግሥት ካዝናም በጀት መመደብ የግድ ሳይል፤ ሕዝባዊ መሠረት በማስያዝ እና በሕዝብ ተሳትፎ ብቻ ብዙ ቢሊዮን ብር ይጠይቅ የነበረውን ሥራ፤ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በበጎ ፈቃድ እንዲሳተፍ በማድረግ ብቻ ውጤታማ ማድረግ ተችሏል። ምክንያቱም፣ ጉዞው ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ፤ እንደ ዜማውም ለምለሚቷ ምድር የማድረግ ነው።

ይሄ ሲሆን መልክዓ ምድሮ ያጌጣል፣ ይዋባል። ይሄ ሲሆን ምንጮች ይጎለብታሉ፤ ወንዞች በሙላታቸው ልክ ይለካሉ፤ አዕዋፋት ማረፊያም ምግብም አግኝተው በየሸንተረሩ ይዘምራሉ፤ ሥነ ምህዳሩም ተስተካክሎ ዜጎች ለኑሮ ምቹ ከባቢን ይጎናጸፋሉ። በመሆኑም አረንጓዴ ዐሻራችን፣ ለልምላሜና እድገታችን፤ ለልማትና ብልጽግናችን፤ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የመኖር ምክንያታችን መሆኑን ላፍታም ሳንዘነጋ፣ የቀደመ ተሳትፏችንን በዚህ ዓመትም ልናጠናክር ይገባል።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዐምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በማሙሻ ከአቡርሻ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You