ረቂቅ ንዝረ ዜማውያን

ኩሎ ጥበብ ኩሎ

ስሜት እሷን ተከትሎ

በአረም ባጋም ተንደባሎ

ይመለሳል ሚስጥር አዝሎ።

ድንበር አልባ ንዝር ምጥቀት

በአንድ አፍታ ህቡ ውስጠት

ኩለው በምናብ ቢያኳኩሏት

ረቂቅ ደቂቅ ሙዚቃ ናት።

ያልናት ስንኝ ገሀድ ገልጣ መጠን ምስሉን ባትገልጠውም፤ ቃሉ ግን የሚላት “ረቂቅ” ነው። ምክንያቱም ይህቺ ሙዚቃ ረቂቅ ናት። ረቂቅነት ጥበብ፣ ረቂቅነት ሙዚቃ። በሙዚቃ ውስጥ ደግሞ ስሜት እንጂ ቃላት ገልጠው የማይችሏቸው ደቂቅ ረቂቃን አሉና። እንደ ረቂቅ ሙዚቃ በህዋሳት የሚሠሩ ሌላ ዓይነት ስሜቶች አሉ ለማለት እንኳ አያስደፍርም።

በቴክኖሎጂና በዘመናዊ ዕውቀት ምን ቢረቁ፤ በሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ በሰው ልጅ አዕምሮና ምናብ ውስጥ የሚደረገውን ጥበባዊ መራቀቅ ሊደርስ አይችልም። አካላዊ ሥጋ የቱንም ያህል ለዓይን ገዝፎ ቢታይ፤ ከዓይን በተሰወረች ቅንጣት ነብስ ይሸነፋል። ህቡ በሆነ መንፈስ ስር ይወድቃል።

የእነዚህ ቅንጣቶች መርቀቅ ነው የሰውን ልጅ ሁለንተና፣ የውስጥ ማንነቱን የሚሠሩት። አዕምሮ በሃሳብ፣ ምናብም ስሜትን ተከትሎ እየተራቀቀ ሲሄድ ደግሞ አንደኛው መንገድ ላይ ሰው ከራሱ ጋር ይገናኛል። ከራሱ ጋር ሰላምታ ተሰጣጥቶ፣ ለራሱ ሰላምን ይፈጥራል። ከራሱ ጋር እያወጋ፣ ከራሱ ጋር ይጫወታል። ብቻውን ሆኖ እንደ ብዙ፣ ብዙ ያያል። ይሰማል። ያውቃል። ይረዳል። ያላስተዋላቸውን እያስተዋለ፣ እውነትን ይፈልጋል። ጥበብን ይገልጣል። ቅኔን ይቀኛል። ሚስጥራትን ይፈታል። እኚህ ሁሉም ከአንዲት ረቂቅ ቅንጣት፣ ረቂቅ ንዝረት ውስጥ ልናገኛቸው የምንችላቸው ናቸው።

የሙዚቃን ደጅ በረገጥንበት ቅጽበት፣ ስለ ሙዚቃ እያነሳን ባወጋንበትና በተነተንበት አንደበት፤ ስለ ረቂቅ ሙዚቃዎች የምናወራ ስንቶች ነን? ከመስማት አልፈን ስለ ዕድገታቸው የምንጨነቅስ እነማን ነን? በዚህ ውስጥ ሲኳትኑ የነበሩና ላሉትስ ምን ያህል ቦታ ሰጥተናቸው ይሆን?

እኚህ “ረቂቅ ሙዚቃዎች” እያልን የምንጠራቸው የጥበብ ፍሬዎች ግን፤ ጣፋጭ የስሜት ጭማቂዎች ናቸው። ሲጠጡ የሚያረኩ፣ አንጀትን ብቻ ሳይሆን ልብንም የሚያርሱ፣ የሚያረሰርሱ ናቸው። ሙዚቃ በራሱ ረቂቅ መንፈስ ያለው የስሜት ገመድ ቢሆንም፤ በረቂቅ ሙዚቃዎች ውስጥ ደግሞ ጠንከር ያለ ሁለንተናዊ ርቀት ነው። አለሳልሶ በጆሮ እየገባ፣ ውስጥን አፍሶ በልብ ይጠነክራል። መርቀቅና መራቀቅ የበዛበት ነውና። እኚህ ሙዚቃዎች፤ ዜማ እንጂ ግጥም የላቸውም። ዜማቸው ግን የሚቀዳው፣ ከስሜትና ከመንፈስ ለነብስ ነውና ነብሲያን አቅፎ የማበርታት፣ የማጽናናት፣ የማስደሰትና እፎይ! የማሰኘት አቅም ብቻ ሳይሆን ረቂቅ ጥበብ አላቸው። ምክንያቱም ልክ እንደስማቸውም ረቂቅ ናቸውና። ግጥም አልባው ውስጣዊ ዜማቸው መንፈስን ይሸክፋል።

ረቂቅ ሙዚቃ ሲባል እንዴት ይሆን የምንረዳው? ከስሜት ጋር እንደሚጋመደው ትዝታ? ለስለስ አድርገው ያንጎራጎሩት ዜማ? ልሳን አልባ የሙዚቃ መሣሪያዎች ዝማሬ (instrumental)? ወይንስ…? እነዚህ ሁሉ ለረቂቅ ሙዚቃ የቅርብ ቢሆኑም፤ ግን በረቂቅ ሙዚቃ የሚመደቡ አይደሉም። ብዙውን ጊዜ ከእነዚህ ጋር የምናምታታው ቀላል አይደለንምና ከወዲህ ልብ ልንለው ይገባል።

በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ልሳን አልባ ሙዚቃዎች ሁሉ ረቂቅ ሙዚቃ አይደሉም። ከእነዚህ መካከልም፤ ምናልባት በባለሙያው ዘንድ ካልሆነ በስተቀር “instrumental” እና “classical” የሚሉትን ሁለት ቃላት መለየት ብቻ ሳይሆን ልዩነት እንዳላቸውም የማናውቅ ብዙዎች ነን። በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበሩትን ልሳን አልባ ሙዚቃዎችን ሁሉ በተለምዶ ‘ክላሲካል’ እያልን የምንጠራቸው ቢሆንም ልዩነት አላቸው።

በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ የሚሠሩ(instrumental) ሙዚቃዎች፤ በየትኛውም ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያ ከሚገኝ ድምጽ ሊሠራ ይችላል። ረቂቅ ሙዚቃ ግን የግዴታ እንደ ሕግ የተደነገገ ባይሆንም የራሱ የሆኑ መሣሪያዎች አሉት። የምዕራባውያኑን ስንመለከት የረቂቅ ሙዚቃ አጀማመርም ሆነ አጨዋወት ከፒያኖና ከቫዮሊን ጋር የተሳሰረ ነው። ከእኚህ ሁለት መሣሪያዎች የሚወጡ ድምጾች ከሥጋችን ይልቅ ለነብሳችን የቅርብ ናቸው። በውጫዊ አካላችን ከሚንጸባረቅ ደስታ ይልቅ፤ ከውስጣዊ መንፈሳችን የሚሰርጹ ናቸው።

ዓለማችን ረቂቅ ሙዚቃን አውቃ፣ ስለ ረቂቅ ሙዚቃ መናገር የጀመረችበት ጊዜ፤ ወደ 1750 ዓመተ ዓለም ከዚያም እስከ 1820 ባሉት ክፍለ ዘመናት ይወስደናል። ያ ጊዜ በዓለም የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂዎች የመራቀቂያ ሽግግር በማድረግ፣ በተለይ በምዕራባውያንና በሩቅ ምሥራቃዊያን ዘንድ አብዮት የፈነዳበት ነበር። ጥበብም ከአብዮቱ ብልጭታ መካከል አንዷ ነበረችና መርቀቋን ተያያዘች። በዚህም “ረቂቅ ሙዚቃ” የሚባል ነገር ታወቀ።

የምድራችንን የምን ጊዜም የሙዚቃ ጠበብት ተደርገው የሚወሱት ሞዛርት እና ቤንትሆቭንም የረቂቅ ሙዚቃ አባቶች ተደርገውም ይቆጠራሉ። ቀደም ሲል በተለይ በኃይማኖታዊ ሥፍራዎች በጥቂቱ ሲከወን የነበረ ቢሆንም፤ የረቂቅ ሙዚቃን ምንነትና ዓይነት ገልጦ በማሳወቅና በመፍጠር ግን እኚህ ሁለት ጠበብት ፈር ቀዳጅ ናቸው።

እኚህን ነገሮች ወደ እኛ ሀገር የሙዚቃ ጥበብ ስናመጣቸው፤ በምን ልንተካቸው እንችላለን የሚል ሃሳብ አይግባን። ምክንያቱም እኚህ መሣሪያዎች ሊሰጡት የሚችሉትን ድምጽ አስቀድሞ በእኛዎቹ ላይ ያሉ ናቸውና። “ቫዮሊን” የተሰኘውን ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ሊተካ የሚችል ያለን ምንስ ይሆን? ጥንቱን እረኞቻችን በዱር በገደሉ፣ በሜዳና በየወንዝ፣ ዳሩ ከተራሮች አናት ቢሆን ግርጌ ተቀምጠው የሚያንጧሩሩት ዋሽንት አለን። ቫዮሊን ምንም እንኳ ዘመናይ ብትሆንም ከምትሰጠው ድምጽና ሙዚቃዊ ንዝረቷ አንጻር፣ ከዋሽንት ጋር ስናስተያያት፤ እንደ ፈረንጅና እንደ ሀበሻ የላም ወተት ማለት ነው።

በምዕራባውያን ረቂቅ ሙዚቃ ውስጥ እንደ ዋልታ የሚታየው ሁለተኛው ደግሞ ፒያኖ ነው። ፒያኖ በድምጽ፣ በመጠን፣ በአጨዋወቱና በመሳሰሉት ይዘቶቹ ብዙ ዓይነት ቢሆኑም፤ በዋናነት በሁለት ይመደባሉ። እኚህም ‘ግራንድ’ እና ‘አፕ ራይት’ የተሰኙት ናቸው። በብዙ የሙዚቃ ጠበብት ዘንድ ተመራጭ የሆነውና ባለወፍራም ድምጹ ‘ግራንድ ፒያኖ’፤ የድምጽ ልኬቱን ወደኛ ልንስበው እንችላለን። ከባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻችን መካከል አቻውን ብንፈልግለት በገና ለመሆን አያቅተውም። የበገናን ያህል ባይሆንም ክራርም ወደ ፒያኖ ድምጾች የቀረበ ነው።

ስለ ረቂቅ ሙዚቃ ሳይንስ አጥንተው ለዓለም በማሳወቅ ምዕራባውያኑ ይቅደሙ እንጂ፤ በገናና ዋሽንት እንዲሁም ሌሎችም የባሕል ሙዚቃ መሣሪያዎቻችን በሀገራችን የተጀመሩበትን ጊዜ ካጤነው፣ ረቂቅ ሙዚቃን በማወቅ ደረጃ ቀዳሚዎች ስለመሆናችን ይገለጥልናል። ነገር ግን፤ ታላቁ የዜማ አባት የሆነው ቅዱስ ያሬድ፣ ከሞዛርትና ቤንትሆቭን ብዙ ክፈለ ዘመናትን ቀድሟል። ያሬድ እንደነሞዛርት ፒያኖና ቫዮሊን ይዞ ባይጫወትም፤ ረቂቅ ዜማን የፈጠረ ስለ ረቂቅ ሙዚቃ አያውቅም ልንል አንችልም። እንግዲህ ለዚህ ረቂቅ የሙዚቃ ንዝረት ስም በመስጠትና ለዓለም በማሳየት የቀደሙት ምዕራባውያኑ ናቸውና ረቂቅ ሙዚቃም የእነርሱ ባሕል ተደርጎ ይቆጠራል።

ረቂቅ ሙዚቃዎች፤ ረቂቅ ብቻ ሳይሆኑ የሚያራቅቁም ጭምር ናቸው። በመጀመሪያ ሙዚቀኛው ይራቀቅባቸዋል። ቀጥሎ ደግሞ ረቀው አድማጩንም ያራቅቁታል። “መራቀቅ” ማለት በአንድ ነገር ላይ የሚደረግ ጥልቅ የሆነ ሃሳባዊ የአዕምሮ ምጥቀት ነው። ዕውቀትና ጥበብን አዋህዶ በሃሳብ ውቅያኖስ ላይ በምስጠት መዋኘት ነው። ወዲህ ስንመጣ ደግሞ፤ ረቂቅ ሙዚቃዎች ጆሮ ከመግባታቸው ስሜትን ቋጥሮ የመያዝና በዚያ ስሜት ሀዲድ ውስጥ እንድንገባ የሚያደርግ ስበት አላቸው።

ውስጣችንን ረጋ ቀዝቀዝ፣ ሃሳባችንን ደግሞ ሰብሰብ የማድረግ ኃይል አላቸው። እኚህ ባሕሪያቱም ምናባዊውን የአዕምሮ ክፍላችንን በር በቀላሉ እንዲከፈት ያደርጉታል። ይህን ጊዜ ዓይናችን የሚመለከተውን ውጫዊ ሁኔታዎችን ረስተን የምንመለከተው ወደ ውስጥ ይሆናል። ትልቁ ነገርም፤ በምናብ ወደ ውስጥ እየተመለከትን ያለነው ነገር ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ወደ ውስጥ መመልከትና በሃሳብ መስመጥ ሁሉ መራቀቅ አይደለምና።

ብዙ ሰዎች ወይንም አንዳንድ ሰዎች፤ ሥራዎቻቸውን ከመጀመራቸው በፊት ለስለስ ያለ ሙዚቃ አሊያም ረቀቂ ሙዚቃ ካልከፈቱ በስተቀር እጅና እግራቸው እሺ ብሎ የሚታዘዝላቸው የማይመስላቸው አሉ። አንዳንዶች ለስለስ ባሉ ሙዚቃዎች፣ ሌሎችም በረቂቅ ሙዚቃዎች ወደ ተመስጦ ግብር ይገባሉ። ሁለቱም በምናብ የማስመጥ አቅም አላቸው። ነገር ግን፤ በሁለቱ መካከል ያለው ምናባዊ ምጥቀት ግን ልዩነት አላቸው። በድምጽ እንጉርጉሮ በታጀቡና ለስለስ ባሉ ሙዚቃዎች ውስጥ ዜማ ብቻ ሳይሆን ግጥማዊ ድምጾች አሉበት። እኚህም ነገሮች ለአድማጩ ሃሳብና መልዕክት የሚያቀብሉ በመሆናቸው፣ ከሙዚቃዊው ሃሳብ ውስጥ ወጥቶ ከራሱ የምናብ ጓዳ እንዳይዘልቅ አስሮ ይይዘዋል።

አንዳንዴም የያዘውን ረስቶ ወደማይፈልገው የሃሳብ ምጥቀት ሊወነጨፍ ይችላል። ስለዚህ ምናብን ዘዋሪው ራሱ ሙዚቃው ይሆናል። ረቂቅ ሙዚቃዎች ግን እንዲህ አይደሉም። ተጨማሪ ልሳናዊ ድምጽና ዜማ ላይ መሠረት ያደረጉ ባለመሆናቸው፣ በምናብ መምጠቅና መራቀቅ ከምንፈልገው ሃሳብ አይነጥቁንም። የምንፈልገው እንቅልፍ ቢሆን እንኳን በሃሳብ ጠልፈው አይነፍጉንም።

ረቂቅ ሙዚቃ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ማንነት ጋር የተቆራኘ ነው። ከመሣሪያዎቹ ውስጥ ከሚወጡ ለስለስና ቀዝቀዝ ካሉ ድምጾች ጋር በጆሮና በልብ ለመጣጣም የሚችሉ፤ ተፈጥሯዊ ማንነታቸውና ውስጣዊ ስሜታቸው የረጋ ብቻ ናቸው። ካልሆነ ቢያደምጡትም ሊረዱት አይችሉም። ረቂቅ ሙዚቃ ልክ እንደ ውቅያኖስ፣ በዝምታ እንደሚሄድ ወንዝ ነው። በዚህ ወንዝ ውስጥ እንቅስቃሴ የምናበዛ ከሆነ፤ ከውሃው ሞገድ ጋር መጋጨታችን አይቀርም። በወንዝ ውስጥ ለመዋኘት የምንችለው፣ ወንዙ ወደሚሄድበት አቅጣጫ ለመሄድ ስንችል ብቻ ነው። ከረቂቅ ሙዚቃ ውስጥ የምትወጣ እያንዳንዷ ልቡ ውስጥ ማረፊያ ትፈልጋለች። በጆሮ ቁልቁል በደምስር መውረጃ ትሻለች። ከስሜት ጋር ተዋዳ መዋሃድ ግድ ይላታል። እናም ራሳቸውን ለእርጋታ ባላዘጋጁ ሰዎች ስሜት ውስጥ ረቂቅ ሙዚቃ ጭንቀት የሚዘራ ይሆንባቸዋል። በሚሰሙት ኩልል ባለ የዜማ ፍሰት ውስጥ በተመስጦ ከመዋኘት ይልቅ፤ በስሜት መወራጨትና መነጫነጭም ሊያስከትል ይችላል። ከተዝናኖት ይልቅ በድባቴ ሲወቁ ልንመለከታቸው እንችላለን።

በዚህ ዙሪያ የተሠራ ጥናት ባልመለከትም፤ ከረቂቅ ሙዚቃ ጋር ከመጣጣም አንጻር፣ በዕድሜ ከፍ ያሉት የተሻሉ ይመስለኛል። ምናልባት አጢነነው ከሆነ፤ ብዙውን ጊዜ የሕፃናት ልጆች ጆሮና ልብ ለረቂቅ ሙዚቃ ቦታ የላቸውም። በልጅነትና በወጣትነት አልፈን አሁን በእድሜ መግፋት ያለን፤ ስለራሳችን በማስታወስ ይህን እውነት ከማንም በላይ ለማረጋገጥ እንችላለን። በተቃራኒው ደግሞ፤ እንደ ቺግቺጋና ቡጊቡጊ ወይንም እንደ ሮክና ዳንስሆል ያሉ ሞቅ ደመቅ ያሉ የጭፈራ ምቶችና ድምጾች፣ ከማንም በላይ የሕፃናትን ቀልብ የሚስቡ ሲሆኑ፣ በእድሜ ለገፉት ደግሞ ረብሻና ጩኸት ነው። እንግዲህ እንዲህ ያሉ ቀለል ያሉ እውነታዎችን ካጤንን፣ የረቂቅ ሙዚቃን ውስጣዊ ባሕሪ ለማወቅ እንችላለን።

ረቂቅ ሙዚቃ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ፍቱን መድኃኒት ሆኗል። ከአካል መጉደልና መቁሰል በላይ ለሆኑት የሥነ ልቦና እና ሥነ አዕምሮ ሕመም፣ ረቂቅ ፈዋሽነቱን የዘርፉ ሳይንቲስቶችም አረጋግጠውታል። የታካሚያቸውን ህመም የተረዱት እልፍ ሐኪሞችም፤ ማን እንደ ረቂቅ ሙዚቃ በማለት ላይ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ህሙማን ባሉባቸው ስፍራዎች ሁሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን መመልከት፣ ዛሬ ላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል የተለመደ ሆኗል። ከላይ አካላቶቻቸው ደንዝዘው፣ ከውስጥ ግን አዕምሯቸው በቀውጢ ረብሻና መታወክ ውስጥ ለገባባቸው፤ ማሠሪያው ሙዚቃ ነው። ከሙዚቃም አለሳልሰው ስሜትን የሚቆነጥጡ፣ ከእነዚህም ደግሞ እንደ ረቂቅ ሙዚቃ ያሉት፤ ምንም ላብራቶሪ፣ ምንም ቀዶ ጥገና የማያስፈልጋቸው ረቂቅ የተፈጥሮ ማሽኖች ናቸው። ቴክኖሎጂ እና ዕውቀት ተጣምረው የቱንም ያህል ቢረቁም፣ የጥበብን ቅንጣት ለማከል አይቻላቸውም።

የእኛስ የሙዚቃ ረቂቅነት ከምን ደረሰ? በርግጥ እንደኛ ሀገር የሙዚቃ አፍቃሪ፣ እንደ እኛ ባለው የሙዚቃ ጥበብ ውስጥ፣ ለረቂቅ ሙዚቃዎች ያለን ስፍራ አናሳ ነው አለማለት አይቻልም። ምዕራባውያኑን ጨምሮ በብዙዎች ዘንድ እንደ አንድ የሙዚቃ ክፍል የሚቆጠር፣ እጅግ ተመራጭና ዕለት ዕለት በጆሮ የሚንቆረቆር ነው። እኛም ጋር የሚደመጥ ቢሆንም፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን ወደ አንድ ዝግጅት ለመግባት ማሟሟቂያ ሲሆን ይታያል። ወደ እግር ኳስ ሜዳ ለመግባት፣ በስታዲየሙ ተመልካች ፊት እንደሚደረግ የሰውነት ማፍታቻ እንቅስቃሴ ዓይነት ይደረጋል። በመድረኮች ላይም ሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሁሉ ከበስተጀርባ ለዝግጅታችን ማጀቢያ ይሆናል። ጠዋት ላይ ወደ አንደኛው ሆቴል፣ ካፍቴሪያ፣ በተለይ ደግሞ ወደ መዝናኛ ሎጆች ብቅ ስንል ገና ከበሩ ላይ እናደምጠዋለን። እኚህና መሰል አጋጣሚዎቻችን መልካም እንጂ የሚነቀፉ አይደሉም። ያነሳንበት መንገድም፤ እንደ አንድ የሙዚቃ ዓይነት ቆጥረን፣ ሆነ ብለን የማድመጥ ባሕል የለንም ለማለት ያህል ነው።

ሌላ አንድ ማስተካከል ያለብን ነገር ደግሞ ያለ ይመስለኛል…የትኛውም የሙዚቃ አፍቃሪም ሆንን ሌሎቻችን፤ የአንድን ድምጻዊ ሙዚቃ ስናደምጠው የወደድነውን እንደሆን፣ የሥራውን ባለቤት የማናውቀው ቢሆን እንኳን ማን እንደሆን ለማወቅ እንጥራለን። በሌሎች ነገሮች ውስጥም እንዲሁ ከወደድናቸው ነገሮች ጋር፣ ውዱን ነገር የሰጡንን እናውቃቸዋለን። እናስታውሳቸዋለን። ነገር ግን፤ የቱንም ያህል አዘውትረን የምናደምጠው ቢሆን እንኳ፤ አብዛኛዎቻችን የረቂቅ ሙዚቃዎቹን ፈጣሪዎች ስለማውቅ ትዝ አይለንም። አብዝተን ወደን፣ አዘውትረን የምናደምጠው ረቂቅ ሙዚቃ ባለቤት አናውቀውም። አንዳንዶቻችን ከነጭራሹም የፈጠራ ባለቤት ያለው መስሎ አይሰማንም። እኚያን በመሳሰሉ ውብ የሙዚቃ ሥራዎች ውስጥ፤ የሠሪው ስም አብሮ ስለማይነሳባቸው፣ መሣሪያዎቻቸውን እንደታቀፉ እንደ ባህታዊ ሆነው ያልፋሉ። ከዚህም ቀደም የነበሩ የረቂቅ ሙዚቃ ጠቢባን ስም አደባባይ መውጣት የጀመረውም፣ ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ ከሞቱ በኋላ ነው። እንደሌላው የሙዚቃ ሥራ ሁሉ በሕይወት ሳሉ ዕውቅና ሰጥተን፣ በሕይወት ሳሉ እነማን ናቸው ልንል ይገባል። ሥራዎቹን ባደመጥን ቁጥር ሁሉ የማን እንደሆኑ ስናውቅና እኩል ከሙዚቃው ጋር ስናስታውሳቸው መልካም ይሆናል።

ቅሉ ያም ቢሆን ይሄ፤ በእኛ ሀገር፣ በእኛ ሙዚቃ ረቀው የተጠበቡበት፣ የረቂቅ ሙዚቃ እናትና አባት የሆኑ ብዙዎች አሉን። የእማሆይ ጽጌ ማርያም ጣቶች፤ ከእነ ሞዛርትና ቤንትሆቭን ጣቶች ቢረዝሙ እንጂ አያጥሩም። “ጥቁሩ ኮዳሊ” የተባለለት በለዋሽንቱ እረኛ፣ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደም ኮዳሊን የሚያስንቅ ነበር። ግርማ ይፍራሸዋስ ቢሆን ከየትኛው የምዕራብ ሊቅ ያነሰ ቀመር ነበረው? በርግጥ ይህን ስንል ረቂቅ ሙዚቃን ለዓለም ያስተዋወቁትን የምዕራባውያኑን የሙዚቃ ጠቢባን ታላቅነትና ፈር ቀዳጅነት የምንዘነጋው አይደለም። የእነርሱ ረቂቅ ጠቢባን እንደነርሱ፣ የእነርሱን ሠርተዋል። የእኛዎቹም እንደኛ፣ የእኛን ሠርተዋል። የፒያኖን ሻርፕና ፍላት ቁልፎች ነካክተው ረቂቅ ሙዚቃን ለፈጠሩ ጣቶች፣ በዋሽንት በቫዮሊኑ እፍ! ብለው ላረቀቁ ትንፋሾች ሁሉ ምሥጋና ይግባቸው ከማለት አንጎድልም።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You