“በእድሜ ማጭበርበር ሀገር ተተኪ አትሌት እያጣች ነው”-ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ

በአትሌቲክሱ ዓለም አበረታች ንጥረ-ነገር (ዶፒንግ) ተጠቃሚነት እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ ነው። ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን ስኬታማ ለሆነችው ኢትዮጵያ ከዶፒንግም በበለጠ የአትሌቶች የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑ ሲገለፅ ዓመታት ተቆጥረዋል። ያም ሆኖ ከእድሜ ጋር የተያያዘው ችግር እየተሻሻለ ሳይሆን እየባሰበት ነው የመጣው። በቅርቡ በድሬዳዋ በተካሄደው የኢትዮጵያ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከስፖርት ቤተሰቡ እስከ ባለሙያዎች፣ ከአሠልጣኞች እስከ ራሳቸው ተወዳዳሪ አትሌቶች እንዲሁም የውድድሩ ባለቤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረስ የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ ማድበስበስ በማይቻልበት ሁኔታ ጎልቶ መታየቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስያሜው ባጭሩ ሀገር አቀፍ የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በተግባር ግን ፈፅሞ የወጣቶች ሻምፒዮና መሆን አልቻለም። እንደ አጠቃላይ ይህ ሻምፒዮና ከዓላማው አኳያ መክሸፉን ብዙዎች ይስማሙበታል።

በዚህ ሻምፒዮና በጣት የሚቆጠሩ (በተለይም በአጭር ርቀት ሴቶች) ወጣቶች ተወዳዳሪ ሆነው ከመቅረባቸው ባሻገር በአጠቃላይ በሁሉም የውድድር አይነቶች በተገቢው እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ማየት አልተቻልም።

አንጋፋው ኦሊምፒያን ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ከብሔራዊ ቡድን ጀምሮ በተለያዩ በርካታ ክለቦችንና ትልቅ ስም ያላቸው አትሌቶችን በማሠልጠን ይታወቃሉ። የሞስኮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊው ሻምበል ቶሎሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታላላቅ አትሌቶችን በማፍራት የሚታወቀው የመቻል ክለብ የአትሌቲክስ የቴክኒክ ኃላፊ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ። እሳቸው ይህን የወጣቶች ሻምፒዮና ሳይሆን “ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ነው” ሲሉ ከእድሜ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ይገልፁታል። “ይህ የወጣቶችን ሕልም የሚያጨልምና የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚገድል ነው” የሚሉት ሻምበል ቶሎሳ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለአዲስ ዘመን የሰጡት ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይነበባል።

አዲስ ዘመን:- ሻምበል ቶሎሳ ከአትሌቶች የእድሜ ተገቢነት ጋር ያለውን ችግር እንዴት ገመገሙት?

ሻምበል ቶሎሳ:- እኛ እንደ መቻል የአትሌቶችን አቅም አይተን በሕክምና ባለሙያዎች ምርመራ በማድረግ ቢያንስ ለእድሜ ተገቢነት ቀረብ ያሉትን አትሌቶች መርጠን ነው ያመጣነው። በዚህም ተገቢ አይደሉም ብለን የለየናቸውን በርካታ አትሌቶች ከሻምፒዮናው አስቀርተናል። ሻምፒዮናው ላይ ግን ሌላ ታሪክ ነው ያየነው። በአዋቂዎቹ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፉ አትሌቶች በወጣቶች ሲወዳደሩ ነው በግልፅ ያየነው። የአዋቂዎቹ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከሦስት ሳምንት በፊት አዲስ አበባ ላይ ተካሂዷል፣ ይሄም (የድሬዳዋው) ሌላ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ነው ማለት ይቻላል። ይሄ ካልተስተካከለ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚገድል ነው። ምክንያቱም በተገቢው እድሜ የሚሮጡት ወጣቶች ተገቢ ባልሆነ እድሜ እያጭበረበሩ በሚሮጡ አትሌቶች እየተዋጡ ነው። ወጣቶች እንዳያድጉና የአትሌቲክስ ሕልማቸውን እውን እንዳያደርጉ እየቀጠፍናቸው ነው።

አዲስ ዘመን:- የዘንድሮው የወጣቶች ሻምፒዮና ከዓላማው አንፃር ከሽፏል ማለት ይቻላል?

ሻምበል ቶሎሳ:- ሻምፒዮናው የሚካሄደው ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች ነው፣ በተግባር ግን ፈፅሞ እንደ ስያሜው አይደለም። በዚህ ረገድ ዓላማውን አሳክቷል ማለት አይቻልም።

አዲስ ዘመን:- የእድሜ ማጭበርበር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዘላቂ ውጤት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እንዴት ይገልፁታል?

ሻምበል ቶሎሳ:- ተገቢ ባልሆነ እድሜ እዚህ ውጤት የሚያመጡ አትሌቶች እድሜና አቅማቸውን ታዳጊ እያሉ ስለሚፈጁ ከፍ ብለው ለብዙ ዓመት መወዳደር አይችሉም። እኛ አሠልጣኝ በነበርንበት ወቅት እነ ቀነኒሳና ከእነሱም በፊት የነበሩ አትሌቶች ወጣቶች እያሉ “እኛ በአዋቂ እንጂ በወጣቶች አንወዳደርም” ብለው ከስር ላሉ ለሌሎች ወጣቶች ዕድሉን ይተዋሉ። አሁን ግን እድሜውን እያጭበረበረ ሁሌም እዚያው ተቀምጦ መኖር የሚፈልግ አትሌት ተፈጥሯል። ይሄ ሀገርን ማታለል ነው፣ አሠልጣኞች ለራሳቸው ጊዜያዊ ጥቅም ብለው ተገቢ ያልሆነ ከእድሜው በላይ አትሌት ይዘው ይመጣሉ፣ እነሱ ተጠቅመው ሊሆን ይችላል፣ ሀገርን ግን እየጎዱ ነው። በተገቢው እድሜ የሚወዳደሩ ወጣቶችን በ4 እና 5 ዓመት ወደ ኋላ እያስቀረን ነው፣ በዚህም ምክንያት ሀገር ተተኪ እያጣች ነው።

አዲስ ዘመን:- በእድሜ ገደብ የሚካሄዱ ውድድሮች ከሕግና ደንብ ጀምሮ ብዙ ችግሮች አሉባቸው፣ ለዚህ አንዱ ማሳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሳተፉ አትሌቶች መወዳደራቸው ነው፣ ይሄ ተገቢ ነው ይላሉ?

ሻምበል ቶሎሳ:– ሻምፒዮናው በራሱ ችግር አለበት። ለዚህ አንዱ ማሳያ እንዳልከው በዓለምና አሕጉር አቀፍ መድረክ ሀገር ወክለው የተወዳደሩ አትሌቶች እድሜያቸው ተገቢ ቢሆን እንኳን ተመልሰው በሀገር አቀፍ የወጣቶች ውድድር ላይ መሳተፍ መቻላቸው ነው። በዘንድሮው የወጣቶች ሻምፒዮናም በ2024 ፔሩ ሊማ የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ተሳትፈው ውጤታማ የሆኑ በርካታ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል። ይሄ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፣ ሀገርን በተለያዩ ውድድሮች የወከሉ አትሌቶች ወጣቶች ቢሆኑም ከፍ ማለት እንጂ እንደገና ወርደው መወዳደር የለባቸውም። ወደ አዋቂዎች ውድድር መሄድ አለባቸው። ይሄን ማድረግ ደግሞ የፌዴሬሽኑ ሥራ ነው።

አዲስ ዘመን:- ፌዴሬሽኑ የእድሜን ችግር ለዓመታት መቅረፍ ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው ይላሉ?

ሻምበል ቶሎሳ:- ሁሉም ወደዚህ ውድድር ሲመጣ የራሱን ማጣሪያ ያደርጋል፣ ፌዴሬሽኑ ብዙ ባለሙያዎች አሉት፣ ክልሎችና ክለቦች የራሳቸውን ማጣሪያ ሲያደርጉ እነዚህ የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ሄደው ማጣራትና ማስተካከል የሚችልበት ዕድል አለ። ያሳዝናል ይሄ ለበርካታ ዓመታት ብዙ ሲባልለት የኖረ ችግር ነው፣ ዛሬም ግን አልተቀረፈም፣ እንዲያውም ተባብሶ ቀጥሏል። ፌዴሬሽን ውስጥ ያሉት የእኛው ልጆች ናቸው፣ እዚህ ላይ የማያዳግም መፍትሔ መውሰድ ለምን እንዳልቻሉ አይገባኝም። መጨከን ለምን እንደሚያስፈራቸው አላውቅም። ሙያተኛ ሀገር ውስጥ ሞልቷል፣ ወደ ክልል ወርዶ በነፃነት ሠርቶ እንዲያጣራ ማድረግ ከባድ አይደለም።

እዚህ ላይ ክለቦችና ክልሎችም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ተገቢ ያልሆኑ አትሌቶች ውድድር ላይ ከመጡ በኋላ እንዴት ይመለሳሉ ብሎ ከመጨነቅ እዚያው ባሉበት ይሄ መወዳደር አይችልም/የለበትም ሊባሉ ይገባል። እንግዲህ መሥራት ያቃተን ይሄንን ነው።

አዲስ ዘመን:- የሚሊተሪ ተቋማት ክለቦች አትሌቶችን ሲቀጥሩ እንደ እግር ኳስ በሲቪል አይደለም። አንድ ሰው ደግሞ የሚሊተሪ ቅጥር ለመፈፀም ከ18 ዓመት በላይ መሆን እንዳለበት በሕግ ተቀምጧል። ታዲያ በዚህ መንገድ የተቀጠረ አንድ የሚሊተሪ ተቋም አትሌት እንዴት ከ18 ዓመት በታች የወጣት ውድድር ላይ ሊሳተፍ ይችላል። ወይንስ በሚሊተሪ የሚቀጠረው እድሜው ከ18 ዓመት በታች ሆኖ ነው?

ሻምበል ቶሎሳ:- እኛ በዚህ የወጣቶች ሻምፒዮና በመቻል ከተቀጠሩ ዓመት ያልሞላቸውን አትሌቶች ነው ያመጣነው፣ የምንወዳደረውም ከ20 ዓመት በታች ባለው ነው። እርግጥ ነው እኛ እንደ ሚሊተሪ/ወታደር የምንቀጥረው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑትን ነው፣ ያም ሆኖ ሌላው ክለብ እንዲህ እያደረገ የሚል ነገር ይነሳብሃል፣ እኔ በአመክንዮ ነው የማምነው፣ በዚያ መንገድ ሄጄ ውጤት ባጣ እመርጣለሁ፣ በእርግጥ አንዳንዱ የሚሊተሪ ክለብ ወጣት አትሌት ላይ ለመሥራት ብሎ ከ18 ዓመት በታች የሚቀጥር አለ፣ ይህ ደግሞ ለስፖርት ብቻ ተብሎ ከተቀጠረ በኋላ 18 ሲሞላው ሚሊተሪ ሊሆን ይችላል፣ ይህ ማለት ግን ችግር የለም ማለት አይደለም፣ ችግሩ የኛው የአሠልጣኞች ሲሆን ለውጤት ብለን የምንፈጥረው ነው፣ አሁን ፌዴሬሽኑ ያደረገው ነገር ጥሩ ነገር በዚህ ሻምፒዮና የዋንጫ ሽልማት ማስቀረቱ ነው፣ ይሄ በእድሜ ጉዳይ ለሚነሳው ችግር አንድ ርምጃ ነው፣ እስከታች ወርዶ ግን ከሙያተኛው ጋር ይህን የእድሜ ችግር ማጥራት ይችላል።

አዲስ ዘመን:- መቻልን በተመለከተ በተለያዩ ሀገር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በውጤት ረገድ ቀዳሚ ሲሆን ማየት የተለመደ ነው፣ አሁንም በተለይ በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ጥሩ ውጤት ያስመዘግባል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይም በረጅም ርቀት ውድድሮች የቀድሞውን ስኬታማነት እየተመለከትን አይደለም፣ በዚህ ረገድ መቻል የገጠመው ችግር አለ?

ሻምበል ቶሎሳ:- መቻል በሥነሥርዓት የታወቀ ነው፣ የወታደር ቤት ነው፣ ሥራ የተባለበት ቦታ ነው የሚሠራው፣ አሁን ምንድነው በመቻል አትሌቲክስ የተበላሸው ነገር… አትሌቶች ለማኔጀሮች ተላልፈው ተሰጡ፣ ገና ጀማሪውንም ውጤት ያለውንም አትሌት አሳልፈው ለማኔጀር ነው የሰጡት፣ ክለቡ ነው ይህ እንዲሆን የፈቀደው፣ ይሄ ደግሞ አትሌቶቹ የክለብ አሠልጣኝ ጋር ሄደን ነው የምንሠለጥነው ለማለት አቅም አሳጥቷቸዋል። ይሄን መቆጣጠር አልተቻለም፣ ስለዚህ ረጅም ርቀት ላይ ያሉት አትሌቶች አንዱም ከክለቡ ጋር እየሠራ አይደለም፣ ይሄን ለማስተካከል ጊዜ ይጠይቃል፣ ገና አዲስና ውጤት የሌለው አትሌት ጭምር ማኔጀር ጋር ለምኖ እየሄደ ይሠራል፣ ይሄ የራሱ የመቻል አሠልጣኞች ጋር የነበረው የአቅም ችግር የፈጠረው ነው። ይሄን ለማስተካከል ለወደፊቱ የአሠልጣኞችን አቅም በየጊዜው ማሳደግ ያስፈልጋል፣ በዚህም አትሌቱን እዚሁ ትሠራለህ ብሎ ወደ ማኔጀር እንዳይሄድ ማስቆም አለበት። እኔም ይህን ለማስተካከል ከስፖርቱ ኃላፊዎች ጋር እየተነጋገርኩና እየሠራሁ ነው።

አዲስ ዘመን:- አትሌቶቹን ማኔጀር ጋር እንዳይሄዱ ማድረግ የራሱ አደጋ/ችግር የለውም?

ሻምበል ቶሎሳ:– ልጆቹ ማኔጀር ጋር ቢሄዱ አይከለከሉም፣ ነገር ግን ከስር ጀምሮ ሠልጥነው ብቁ ሆነው መሆን አለበት። ሂደቶችን ማለፍ አለባቸው፣ መቻል ውስጥ ያለው ችግርም ይሄ ነው። ይሄ በአንዴ አይቀረፍም ደረጃ በደረጃ ነው፣

አዲስ ዘመን:- ስለዚህ መቻል በአትሌቲክሱ ሪፎርም ላይ ነው ማለት ይቻላል?

ሻምበል ቶሎሳ:- አዎ! ብዙ ማጥራት የሚፈልጉ ነገሮች አሉ።

አዲስ ዘመን:- ሻምበል ቶሎሳ ለሰጡን ጊዜና ላካፈሉን ሀሳብ ከልብ እናመሰግናለን።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You