
አድናን መሐመድ ትባላለች። የመጣችው ከሱማሌ ክልል ነው። በ14 ዓመቷ ቤተሰቦቿ በአካባቢው ባህል መሰረት ጋብቻ እንድትፈጽም አድርገዋታል። ይህ ደግሞ በበርካታ የጤና ችግር ውስጥ ለዓመታት እንድታሳልፍ አስገድዷታል። በተለይም የፌሱትላ ተጠቂ ከሆነች በኋላ የገጠማት ችግር ተዘርዝሮ የሚያበቃ አይደለም። ራሷን ለማጥፋት እስከመሞከር ድረስ የሚያስጨክኑ ውሳኔዎችን አሶስኗት ያውቃል። በበሽታው ምክንያት ከማኅበረሰቡ መገለሏ፣ የጤና ችግሩ ለዓመታት መፍትሄ ሳታገኝበት መቆየቱና በሕመሙ ሳቢያ መንቀሳቀስ አለመቻሏ እንዲሁም ሁልጊዜም በሰዎች ጫንቃ ላይ ሆና ነገሮችን ማድረጓ ስትታይ የአዕምሮ ጤና ችግር ሳቀር እንዲገጥማት ሆናለች።
ባለታሪኳ እንዳስረዳችው፣ የበሽታው መንስኤ በአልጠና የልጅነት እድሜዋ የልጅ እናት ለመሆን መገደዷ ነው። በወቅቱ የመጀመሪያ ልጇን ለመገላገል ስታስብ እንደ ባህሉ በቤት ውስጥ እንድትወልድ ሙከራዎች ተደረጉ። ቤተሰቡና የልምድ አዋላጆች በቻሉት መጠን ልጁን ለማውጣትም ሞከሩ። ሆኖም አልተሳካላቸውምና ወደ ሕክምና ተቋም ለመውሰድ ወሰኑ። ነገር ግን የሕክምና ተቋም በቀላሉ የሚደርሱት አይነት አልነበረም። በቅርባቸው ባለመሆኑ ከአንድ ቀን በላይ መጓዝ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ ለባለታሪካችን ትልቅ ፈተና ነው። ሕክምና ሳታገኝ ቀናትን እንድታሳልፍና ላልታሰበው የጤና ችግር እንድትጋለጥ ያደረጋት ነው። በሕይወት መቆየቷ ጭምር የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ እንጂ በተፈጠረው ነገር ምክንያት ዛሬን አታየውም ነበር።
ሕይወቷ ባያልፍም ለዓመታት የተሰቃየችበትና ዛሬም ድረስ መከራዋን እያየች ያለችበትን የፌስቱላ ጤና ችግር እንዲገጥማት አድርጓታል። አሁን ትንሽ እየተሻላት ትገኛለች። ምክንያቱም በ15 ዓመቷ ወደ ሐምሊን ኢትዮጵያ ሆስፒታል ለህክምና መግባት ችላለች። ይህን እድል በማግኘቷ ደግሞ እግሯም ሆነ ወገቧ ለመንቀሳቀስ ችሏል። ሁሉም ተግባሯ የሚከናወነው በድጋፍ ነበርና ይህ ነገሩም ቢሆን በመጠኑ መሻሻል ጀምሯል። ዛሬ 16 ዓመቷ ላይ የምትገኘው አድናን፣ ብዙ ለውጦችን በሕይወቷ አይታለች። የመኖር ተስፋዋ ለምልሟል። ለነገ የምትላቸውን ተግባራት እያከናወነች ነው። አንዱ ደግሞ ሰዎች ከኔ ይማሩ፣ ችግሮች በእኔ ይብቁ በማለት ለማስተማር በአደባባይ መውጣቷ ነው። ከዚህም በኋላ ጤናዋ ተመልሶ ወደነበረችበት ዓለም ስትገባ ለብዙ ወጣቶች መምህር፣ አርኣያ እንደምትሆንም አስባለች።
አዎ አድናን የበርካታ ሴት ወጣቶች ተምሳሌት ናት። በየቤቱ በአፍላ ወጣትነት እርግዝና ምክንያት የጤና ችግር ውስጥ የገቡትን ሴቶች በሚገባ ታሳያለች። ችግራቸውን ማንም ያልተረዳላቸው በርካታ ዜጎች መኖራቸውንም ትነግረናለች። ከምንም በላይ ደግሞ የጤና አገልግሎት በአቅራቢያ አለመኖር፣ ያለእድሜ ጋብቻና ያለእድሜ ለመውለድ መሞከር ምን ያህል ከባድ ችግር እንደሚፈጥርም የሚያስረዳ የሕይወት ታሪክ አላት። ይህንን በማስረጃ ስንደግፈው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃን ብቻ ማንሳት በቂ ነው።
መረጃው እንደሚያሳየው፣ በዓለም ላይ ወደ አምስት በመቶ የሚጠጉ ነፍሰጡር ሴቶች የምጥ ሂደት መስተጓጎል ይገጥማቸዋል። አስቸኳይ የወሊድ ወቅት ሕክምና የማይገኝ ከሆነ ደግሞ መፍትሔ ያልተገኘለት የምጥ ሂደት መስተጓጎል በወሊድ ወቅት ስለሚፈጠር የፊስቱላ በሽታ ተጠቂ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። የአፍላ ወጣትነት እድሜ ላይም የሚፈጠር ያልተገባ እርግዝና ከእነዚህ ችግሮች መነሻነት የሚፈጠር ነው።
እንደሚታወቀው፣ ወጣትነት አዕምሮ ለሥራ የሚዘጋጅበት፣ የአካል እድገት በፍጥነት የሚዳብርበት፣ ትምህርትና ልምድ የሚቀሰምበት ብሎም ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚሰጥበት የሽግግር ወቅት ቢሆንም በክትትልና ድጋፍ የሚመራ ካልሆነ የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙበት የሚችሉበት የእድሜ ክልል ነው። አፍላ ስሜትን በመቆጣጠር የወላጅ ምክርንም የሚሻበት ጊዜ ነው። ምክንያቱም ለጤና አደገኛ የሆኑ ተግባራትን የሚለማመዱበት የእድሜ ክፍል ነው። እናም በእድገት ውስጥ የሚከሰቱ አለመረዳቶችን፣ አርቆ አለማሰብና ስሜታዊነትን፣ የአቻ ግፊቶችን መቆጣጠር ስለሚሳነው የግድ ድጋፍና ግንዛቤ ማስጨበጥን ይሻል። ጥንቃቄ ባልተሞላው የግብረስጋ ግንኙነት ሳቢያ ያለድሜ እርግዝና መከሰት ደግሞ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ችግር ነው። ያለእድሜ ጋብቻ ሲጨመርበት ደግሞ ነገሩን የበለጠ ያከብደዋል። ስለሆነም እነዚህን ሊፈቱ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ደግሞ ለነገ የሚባል አይደለም።
ከዚህ አንጻርም ይመስላል ከሰሞኑ አራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችንና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በጋራ ለመስራት የሚችሉበት የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን የሚቀንስ ፍኖተ ካርታ ይፋ ማድረግ የተቻለው። ፍኖተ ካርታው በርካታ ሰዎችንና ተቋማትን ያሳተፈ በመሆኑ የችግሩን ግዝፈት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ምን ምን ተግባራት ማከናወን እንደሚገባ በሚገባ ያመላከተ ነው። ለአብነት የችግሩ አሳሳቢነትን ስንመለከተው ያለእድሜያቸው የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 13 በመቶ ነው፣ ያለእድሜያቸው የሚዳሩ ሴቶች ቁጥርም 40 በመቶ ነው። የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ብንመለከትም ከ45 በመቶ በላይ አይደለም።
ስለሆነም አሁን በጋራ እንሠራለን ብለው የተነሱት ተቋማት በቀጣይ ይህንን እቅድ እንዲተገብሩት ተደርጎ ተቀምጧል። እርሱም ያለእድሜያቸው የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ወደ ሦስት በመቶ ዝቅ ማድረግ፣ ያለእድሜያቸው ጋብቻቸውን የሚፈጽሙ ሴቶችን ቁጥር ደግሞ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ማድረግና የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በማስፋት 90 በመቶ ላይ ለማድረስ በሚያስችለው ጉዳይ ላይ እንደሚሠሩ በኃላፊዎቻቸው በኩል ቃል ገብተዋል። ከዚህ አንጻርም ኃላፊነቱን የወሰዱ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች የተለያዩ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩባቸው ጉዳዮች እንዳሉም አንስተዋል።
ጉዳዩ የጤና ሥራ በመሆኑም ትልቁን ድርሻ ወስዶ የሚሠራው የጤና ሚኒስቴር ሲሆን፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ድጉማ፤ ያላቸውን እቅድና ቀደም ሲል የነበረውን ሥራ ፍኖተ ካርታው ይፋ በተደረገበት ወቅት ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳሉትም፤ የአፍላ ወጣቶች እርግዝና ጤና ጉዳይ ከሁሉም ችግሮች የሚከፋው የጤናው ጉዳይ ላይ ነው። ይህ እርግዝና ሲኖር እናቶች የተራዘመ ምጥ እንዲያጋጥማቸው፣ ተያያዥ ለሆኑ የጤና ጉዳቶች እንዲጋለጡና ሕመሙ በቀላሉ ሳይታከም ሲቀር ሕይወታቸውን እስከማጣት የሚደርሱበት ነው። ከጤናው ሻገር ስንል ደግሞ የትምህርትና ሌሎች ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዳይችሉ የሚሆኑበት ነው። በቤተሰብ ላይም ጥገኛ ሆነው ዓመታትን እንዲያሳልፉ ያስገድዳቸዋል።
ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሰሃራ በረሃ በታች ባሉት ሀገራት ላይ ይበረታል። ሀገራችንም ይህ ችግር በስፋት ከሚታይባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነች። ባለፉት ዓመታት በተሠሩት ጥናቶች ብቻ ብንመለከተው 16 ከመቶ የሚሆኑ አፍላ ወጣቶች ያልተፈለገ እርግዝና ገጥሟቸዋል። ይህም ከ33 በመቶ በላይ ከሚሆኑ ወጣቶች ውስጥ ነው። ስለዚህም ቁጥሩ በከፍተኛ የጤና ችግር ውስጥ መግባታችንን በእጅጉ የሚያሳየን ነው። እናም በቀላሉ ልናየው የሚገባ አይደለም። ችግሩ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል ተገንዝቦ መስራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የተቋማቱ ሕብረት በእጅጉ መፍትሄ የሚሰጠው ነው ሲሉም አብራርተዋል።
‹‹አሁን በጋራ ለመሥራት የተፈራረምናቸው ሚኒስቴር መስሪያቤቶችና ሌሎች አጋር አካላት ስብስብ በእጅጉ ለተሻለ ለውጥ የሚያነሳሳ ነው። ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንደሚባለው ሴቷን እየደረሰባት ካለው ከፍተኛ የጤና ችግር ፈልቅቀን እንድናወጣት ያግዘናል። ይህ የሚሳካው ግን ሁላችንም የተሰጠንን በአግባቡ መወጣት ከቻልን ነው። ከፍተኛ ጥረትን ይጠይቃል። ሥራው በአንድ ተቋም ብቻ የሚከናወንም ሊሆን አይችልም። ሁሉም በጋራ መቆም አለበት›› ሲሉም መልእክታቸውን ሰንዝረዋል።
አክለውም፣ እንደጤና ተቋም የሚሠሩ በርካታ ተግባራት አሉ። አንዱና ትልቁ ደግሞ የሥነ-ተዋልዶ አገልግሎት በሁሉም ተቋማት እንዲዳረስ ማድረግ የሚለው ነው። በተለይም ለአፍላ ወጣቶቻችን ግብዓቶችን በሁሉም ተቋማት ተደራሽ ማድረግ፣ ጤና ተቋማት ለሁሉም ሰዎች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ የግድ ይላል። ምክንያቱም አፍላ ወጣቶች በተለመደ ሰዓት ወደ ጤና ተቋም አይመጡም። ከትምህርት ቤት መልስ፣ ቅዳሜና እሁድ፣ በበዓላት ወቅት ሊሆን ይችላል የሚመጡት።
ስለሆነም ለእነርሱ የሚሆኑ የሕክምና አገልግሎቶችን ማስፋት፣ በዘርፉ ሥልጠና ያገኙ የጤና ባለሙያዎችን በስፋት ማሠማራት፣ እንደ ተቋም በጀትም ሲያዝ ጭምር አፍላ ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ ማድረግም ይገባል። በዚህም አሁን ላይ በስፋት እየሠራንበት ይገኛል። በተለይም የሥነ-ተዋልዶና የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በስፋት ማድረስ ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ነገር ግን በቂ ነው ለማለት አይቻልምና በመተባበር ተግባሩን በስፋት ማከናወን ያስፈልጋል።
የአፍላ ወጣቶች እርግዝናን ለመቀነስ ከሚሰሩት ተግባራት መካከል አንዱ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ማዕድናት ላይ ተሰማርተው የሚሠሩ ወጣቶች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሆነ የሚያነሱት ዶክተር ደረጄ፣ እንደ ጤና ሚኒስቴር የሚሠሩ ተግባራት ቢኖርም አሁን በፍኖተ ካርታው ላይ ተሳታፊ የሆኑና የቀጣይ እቅዳቸው ያደረጉ ተቋማትም ኃላፊነት መሆኑን አበክረው አስረድተዋል።
ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ሴቶች እስካሁን ድረስ ሐኪም ወይም ነርስ አካባቢያቸው ሳይኖር ቤታቸው ውስጥ እንደሚወልዱ ይገለጻል። ይህ ደግሞ ከግንዛቤ እጥረት አኳያ የሚመጣ እንደሆነ ማንኛውም ሰው የሚረዳው ነው። ከዚህ አንጻርም ትምህርት ሚኒስቴር እንደሚሠራ ፍኖተካርታው ላይ በነበረው ውይይት ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ- ትምህርት ማበልጸጊያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ ሸዋእርገጥ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የሥነ-ተዋልዶ ትምህርትን በተመለከተ እንደ ሀገር ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር በክበባትና በመጻሐፍት የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተጀምሯል፣ ሆኖም ተግባሩ በትኩረት አቅጣጫ ተለይቶ መሰራት እንዳለበት ይታወቃል። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ መደላደሎች አሉ። አንዱ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጁ ለሴቶች የሰጠው ትኩረት ነው። ሴቶች በትምህርቱ ዘርፍ የተሻሉ እንዲሆኑ በሚገጥሟቸው ችግሮች ሁሉ ቀድሞ መድረስ የሚቻልበትን አሠራር ይፈጠራል። በተለይም መጠነ ማቋረጥና ትምህርትቤት ያለመግባትን ሁኔታ የሚጨምሩት ላይ በስፋት የሚሠራ ይሆናል።
ሴቶችን ከትምህርት ገበታቸው እንዲቀሩ ከሚያደርጓቸው ችግሮች መካከል ያለ እድሜ ጋብቻ፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ያልተፈለገ እርግዝናና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች መሆናቸው ግልጽ ነው። ስለሆነም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ድጋፍ ድረስ የሚደርሱ ሥራዎችን በማከናወን ጤናማ እናቶችን የምንፈጥር ይሆናልም ሲሉ የፍኖተ ካርታው በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እንዴት እንደሚተገበር አብራርተዋል።
ሌላዋ በመድረኩ ላይ የተገኙትና የአፍላ ወጣቶችን እርግዝና ለመቀነስ በሚያስችለው ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ጥብቅ ተሳትፎ የሚያደርጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሆኑ፣ የሴቶችና ሕጻናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ሂክማ ኸይረዲን እንደተናገሩት፤ እንደ ጤና ሚኒስቴር ሁሉ የእናቶች፣ የአፍላ ወጣቶችና ሕጻናት ጉዳይ የእኛም ጉዳይ ነው። ስለሆነም እጅና ጓንት ሆነን ተግባሩን ለመፈጸም ቁርጠኛ ነን። በተለይም ከጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችና ጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ጤናቸውን የሚያጡ ሴቶችን በመደገፍ በኩል የተጀማመሩ ሥራዎች ቢኖሩም እንደዚህ ተሰባስበን ስንሠራበት ጠንካራና ስኬታማ ውጤት እንደምናመጣ በማመን ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን።
በመጨረሻ ሀሳባቸውን የገለጹት ደግሞ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ወይዘሮ ጥሩማር አባተ ናቸው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ በፍኖተ ካርታው ዙሪያ የተለዩ ሀሳቦችን ሰጥተዋል። የአፍላ ወጣቶች ጤና ችግር ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ነው። በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ስናስበው እጅጉን የሚከብድና ብዙ ሴቶችን ለችግር የዳረገ፣ ዛሬም መፍትሄ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎችን የምናይበት ነው። እናም እኛ ዋጋ ተከፍሎልን እዚህ ከደረስን እኛም ጠጠር ወርዋሪዎች ሆነን የነገዎቹን ሴቶች መታደግ ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ ፍኖተ ካርታውን ተከትለን በተሰጠን ኃላፊነት ልክ ከሠራንበት በእጅጉ ይጠቅመናል።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በአፍላ ወጣቶች እርግዝና ምክንያት በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ሴቶች ደህንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ ይገጥማቸዋል። ይህም የሚሆነው ደግሞ በአብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ሲሆን፣ 95 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል። ከአፍላዎች የሚወለዱ ሕጻናትም ቢሆኑ ለተለያዩ ከባባድ ችግሮች የሚጋለጡ ናቸው። ይህ ብቻም አይደለም እናቶቹ ለደም ግፊት፣ ለደም ማነስ፣ ጊዜውን ላልጠበቀ ምጥና ፌስቱላ የመሳሰሉ ችግሮች ይጋለጣሉ። የአፍላ እድሜ ወጣት ሴቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አጠቃላይ ሴቶች አንድ አራተኛ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፣ ጠቅላላ ከሚወልዱ ሴቶች ውስጥ 12 በመቶ ድርሻን ይይዛሉ። እናም ይህንን ለመታደግ ደግሞ ፍኖተ ካርታው መኖሩ፣ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ተቋማት መፈጠራቸው ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፣ ግን ተነሳሽነቱ በተቀበልነው ልክ ይሁን በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን።
በጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም