መሬት ላይ መሥራት ከተማን መቀየር እንደሚያስችል ያመላከተው ካዳስተር

የሀገራችን ከተሞች መሬታቸውን ሲያስተዳድሩ የቆዩበት መንገድ ለመሬት ወረራ የተጋለጠ፣ የከተሞችን ገቢ ሲያሳጣ የኖረ ሆኖ ኖሯል። ይህ ኋላቀር አሠራር ነዋሪዎችን ለከፍተኛ እንግልትም ሲዳርግ የኖረም ነው። ይህ አሠራር ዘመኑን በሚመጥን አሠራር መተካት ጀምሯል። አሠራሩ የመሬት መረጃን በአግባቡ መያዝ የሚያስችል፣ የመሬት ወረራን የሚያስቀር አሠራር መተግበር ጀምሯል። መሬትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማስተዳደር የሚያስችለውና በተለያዩ የዓለም ሀገራት ጥቅም ላይ የዋለው ይህ ዘመናዊ አሠራር የካዳስተር ሥርዓት ይባላል። የኢትዮጵያ ከተሞችም ይህን መተግበር ጀምረዋል።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የመሬትና ካዳስተር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙአለም አድማሱ፤ ካዳስተር ብዙ ዓይነት መሆኑን ጠቅሰው፣ በሀገሪቱ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው ህጋዊ ካዳስተር መሆኑን ይገልጻሉ። ህጋዊ ካዳስተር የመሬት ባለቤትነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል፣ ማን ምን ያህል መሬት በእንዴት ዓይነት መልኩ እንደ ያዘ የሚያመላክት መረጃ መሆኑን አብራርተዋል።

ፊስካል ካዳስተር በይዞታው ላይ ስላረፈው ቋሚ ንብረት ዝርዝር መረጃ እና የመሬቱን ወቅታዊ ግምት ከይዞታው ካርታ ጋር የሚይዝ ሆኖ ለቦታና ለንብረት ግብር ክፍያ የሚያገለግል ሥርዓት ነው። ፊስካል ካዳስተር ትኩረቱ ባለቤቱ ላይ ሳይሆን ንብረቱ ምን አይነት ነው? ምን ያህል ያወጣል? የሚለው ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ የካዳስተር ዓይነቶች የሚገኙትን መረጃዎች የሚይዘውና በተጨማሪ የመሠረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች መረጃዎችን እና ካርታን አካቶ የሚይዘው የካዳስተር ዓይነት ሁሉን አቀፍ የካዳስተር ሥርዓት ይሰኛል።

የማዕድን ቦታዎች ካዳስተር፣ የውሃ አካላት ካዳስተርና ሌሎችም የካዳስተር ዓይነቶች ቢኖሩም፣ እንደ ሀገር ጥቅም ላይ የዋለው ህጋዊ የካዳስተር ዓይነት የተባለው ነው የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በሮድማፕም የተቀመጠው ቅድሚያ ህጋዊ ካዳስተርን መተግበርና በሂደት ፊስካል ካዳስተርን ተግብሮ በመጨረሻም ሁሉን አቀፍ ካዳስተርን የመተግበር እቅድ መሆኑን አብራርተዋል።

ለካዳስተር አተገባበር እየተሠራ ነው የሚሉት አቶ ብዙዓለም በተለይ ለህጋዊና ለፊስካል ካዳስተር እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ። ለፊስካል ካዳስተር የሚሰራ ቢሆንም፣ መሬቱን ማን እንደያዘው ሳይታወቅ ወደንብረት መግባት ስለማይቻል ህጋዊ ካዳስተር ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ቅድሚያ ወስደዋል። በሀገሪቷ ውስጥ ያለውን 60 በመቶ መሬት መዝግቦ ለመጨረስ እቅድ ተይዟል ብለዋል።

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ፤ አዲስ ሥራ የማስተዋወቅ ሥራ መፈለጉና ለማላመድ ጊዜ ይፈልጋል። የካዳስተር ሥርዓትንም ማለማመድ፣ ማስተዋወቅ ይጠይቃል፤ ቴክኖሎጂና አቅም ይፈልጋል።

የካዳስተር ሥርዓትን ለመተግበር እያንዳንዱ ከተማ የአየር ካርታ ሊኖረው ይገባል። የሚዘጋጀው ወቅታዊ መረጃ ስለሆነ የአየር ካርታው ቅርብ ጊዜ የተዘጋጀ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ ዝግጅት ደግሞ የሀገሪቷን ከተሞች በሙሉ መብረር ያስፈልጋል። ከተሞቹን በሙሉ ለመብረር እንደ ሀገር ያለው አቅም ውስን እንደ መሆኑ ጊዜ ይፈጃል።

ሁሉንም ከተሞች በሮ ለመጨረስ ያለው አንድ ተቋም ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢኒስቲትዩት ነው። ይህ ተቋም በርካታ የቤት ሥራዎችን ይዞ ስለሚሠራ ከተሞቹን በሮ መጨረስ ጊዜ ይወስድበታል። በዚህ የተነሳ ካዳስተሩን በምእራፍ በምእራፍ በመከፋፈል ወደ መተግበር ተገብቷል፡፡

ካዳስተርን በመጀመሪያው ዙር 23 ከተሞች ላይ ተግባራዊ ወደ ማድረግ ተገብቷል። ለትግበራው ከተሞቹ በጀት መድበውና ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሥራው የተጀመረ ሲሆን፣ በሂደት የከተሞቹ ቁጥር ከፍ እያለ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት በ103 ከተሞች ካዳስተር እየተተገበረ ይገኛል።

ካዳስተርን ለመተግበር የቅየሳ መሳሪያዎች፣ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ አስፈላጊ አደረጃጀት፣ ሶፍትዌሮች እንደሚያስፈልጉ ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ የመሬት ሰነዶች በሙሉ ዲጅታላይዝ መደረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

እንደእሳቸው ማብራሪያ፤ ለትግበራው የአይቲ መሠረተ ልማት መሟላት ይኖርባቸዋል፤ ኮምፒውተሮችና የተዘጋጀ የሰርቨር ክፍል ያስፈልጋሉ። እነዚህን ነገሮች በእያንዳንዱ ከተማ ማሟላት የግድ ይሆናል፤ አንድ ከተማ ካዳስተርን ስለፈለገ ብቻ ወደ መተግበር ሊገባ አይችልም። የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት ወደትግበራው መግባት ይቻላል። ይህ ካልሆነ ግን ትክክለኛውን የካዳስተር ሥርዓት መመስረት አይቻልም። ሥራው አንዴ ተመዝግቦ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ ከተሞች ቋሚ አደረጃጀት ያስፈልጋቸዋል።

የመጀመሪያ ዙር ካዳስተር የተተገበረባቸው ከተሞች በሚኒስቴሩና በአጋር አካላት ተመርጠው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይ ክልሎች ከተሞቻቸውን እየመረጡ ወደ ካዳስተር ማስጀመር የገቡበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል። ከተሞች የካዳስተር ጥቅም እየገባቸው መምጣቱን ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ በራሳቸው ካዳስተርን እንጀምር የሚል ተነሳሽነት ውስጥ በመግባት የጀመሩ ከተሞች እንዳሉም ተናግረዋል።

‹‹እስከ ዛሬም መሬት እያስተዳደርን ነው፤ የምናስተዳድረው ግን በነባሩ የወረቀት ሥርዓት ነው፤ ከተሞቹም በዚሁ ነው እየሠሩ የቆዩት›› ያሉት አቶ ብዙዓለም፤ ሁሉም ከተማ ባለው አቅምና የገቢ ልክ መሬቱን እያስተዳደረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ከተሞቹ ወደካዳስተር ሥርዓት ይምጡ ሲባል፤ ትንሽ ከተማ ስለሆነ ይሄ ይቀነስለት፣ ትልቅ ከተማ ስለሆነ ይሄ ይጨመር የሚባል ነገር አይኖርም። መሰረታዊ ነገሮች በሙሉ መሟላት አለባቸው ሲሉ አስታውቀው፣ ይህን ሁሉም ከተሞች በአንዴ ማሟላት ስለማይችሉ ክልሎችና ከተሞች በራሳቸው ገቢ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እያደረገ 103 ከተሞች የካዳስተር ትግበራ ጀምረዋል ብለዋል።

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ፤ 103 ከተሞች ካዳስተርን እየተገበሩ ቢሆንም፣ በተለያየ የአተገባበር ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ለዚህም ለከተሞቹ አስፈላጊው ድጋፍ ከመቅረብና አለመቅረብ ጋር ተያይዞ ልዩነት ተፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ተግዳሮቶች ታይተዋል።

በትግበራው ያጋጠመው አንዱ እንቅፋት ሥርዓቱ እንዲዘረጋ አለመፈለግ ነው። ሥርዓቱ ተዘርግቶ የመሬት አጠቃቀም ከተስተካከለ በመሬቱ ሲጠቀሙ የነበሩ አካላት ጥቅማቸው ይቀራል። እነዚህ አካላት ፊት ለፊት ይሄ ሥርዓት አያስፈልግም ይቅር ባይሉም፤ ከጀርባ ሆነው ሥራው ወደፊት እንዳይሄድ የሚያደርጉ ስልቶችን ይጠቀማሉ።

ይሄ አመራሮችንና ባለሙያዎችንም ይጨምራል። ከውጭ ሆነው በመሬት ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑ ደላሎችም ሥርዓቱ እንዳይተገበር ይሰራሉ፤ ማኅበረሰቡም ከግንዛቤ እጥረት ጋር በተያያዘ ተባባሪ አለመሆን ይስተዋልበታል።

ካዳስተር በከተሞች የተንሰራፋውን የመሬት ወረራ ለመቅረፍ ያስችላል የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ የመሬት ወረራ ከተሞች የራሳቸውን መሬት ቆጥረው መዝግበው ባለመያዛቸው የሚከሰት ችግር መሆኑን ገልጸዋል።

በነባሩ አሠራር ከተሞች የአስተዳደር ወሰናቸውን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚጠየቁበት ሁኔታ አልነበረም። ስለዚህም ከፊሉን የከተማ አካባቢ መዝግበው እያስተዳደሩ ሲቆዩ፤ የተቀረው ክፍል ከቁጥጥራቸው ውጪ የሚሆንበት አግባብ ነበር።

ካዳስተርን ለመተግበር መሟላት ካለባቸው መስፈርቶች አንዱ የአስተዳደር ወሰን መሟላት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሲሆን ከተሞች የአስተዳደር ወሰናቸውን ስለሚያውቁ መሬታቸውን በትክክል ያስተዳድራሉ ሲሉ አስታውቀዋል።

ከተሞች የተወሰኑ ይዞታዎችን መዝግበው ያስተዳድሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ብዙአለም፤ ካዳስተር ምዝገባው ሲጀመር ከተሞች ሙሉ ይዞታቸውን ወደ መመዝገብ ተሸጋግረዋል ብለዋል። ይዞታዎችን በአንዴ መዝግቦ የመያዝ አቅም እንደሌለም ተናግረው፣ምዝገባው በሂደት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የካዳስተር ምዝገባው በመኖሩና ህገወጥ ግንባታ እንደማይመዘገብ በመታወቁ በሕገወጥ መንገድ መሬት የመያዝ ሁኔታ ቀንሷል ሲሉም ጠቅሰው፣ “ሰው ህገወጥ ግንባታ የሚይዘው ነገ ይጸድቅልኛል” በሚል ተስፋ መሆኑን አስታውቀዋል። መሬቱ አስቀድሞ ከተመዘገበ ቢሠራ ራሱ እንደማይጸድቅለት ስለሚያውቅ ህገወጥ ግንባታ ላይ የሚሳተፈው ቁጥር ይቀንሳል ብለዋል።

ከተሞች መሬት እንደከዚህ ቀደሙ ሳይመዘግቡ ቢያስቀምጡ ወደፊት መንግሥት የተወሰነውን ቢወስድ እንኳን ትንሽ ቅጣት ጥሎብን የተወሰነ ይቀርልናል የሚል ታሳቢ ይደረግ ነበር ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ካዳስተር ይህን ማስቀረቱን ገልጸዋል። ምክንያቱም የተመዘገበን መሬት አንድ ግለሰብ ቢወር የሚጸድቅበት አሠራር እንደሌለ አስታውቀዋል፤ ካዳስተር ይህን ዓይነቱን ሕገወጥ ወረራ ማስቀረቱን ጠቅሰዋል።

የካዳስተር ምዝገባው የሚከናወነው ባለይዞታ ለሆነና ለዚህም የካርታ ማረጋገጫ ላለው ሰው መሆኑን አስታውቀው፤ የይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖረው መሬቱን ስለያዘ ብቻ ምዝገባው አይካሄድለትም ብለዋል።

ለዚህም መብቱን የሚፈጥሩና የካዳስተር ሥራውን የሚሠሩ ሁለት ተቋማት እንዳሉ አስታውቀው፣ በካዳስተር የሚመዘገቡት የመሬት ባለመብትነታቸው የተመሰከረ ሰዎች ናቸው፤ ሰው መሬቱን በሕገወጥነት ስለያዘ አይመዘገብም፤ ለመመዝገብ መብት መፈጠር አለበት ብለዋል።

የካዳስተር ሥርዓት መተግበሩ በከተሞች ገቢ አሰባሰብ ላይ ያመጣውን ለውጥ የሚገርም ሲሉ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፤ ከከተሞች ጋር በሚያደርጉት ውይይት ካዳስተር ለከተሞች የተሻለ ገቢ እንዳመጣላቸው የከተሞች ኃላፊዎች እንደሚገልጹ ተናግረዋል።

ሥራ አስፈጻሚው፤ ከተሞች ካዳስተር በመጀመራቸው ገቢያቸው ከእጥፍ በላይ እያደገ ነው፤ ለዚህም በሀገሪቱ በካዳስተር ምሳሌ ተደርጋ የምትወሰደው አዳማ ከተማ ናት ሲሉ ከተማዋን ጠቅሰዋል።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በከተማዋ ካዳስተርን ለመተግበር ወደ ሥራ ሲገባ 40 ሚሊየን ብር በጀት ተይዞ ነው። በዓመቱ መጨረሻ ከመሬት አስተዳደር ብቻ በከተማዋ 124 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል። በአሁኑ ወቅት ይህ ገቢ ከዚህም በላይ ከፍ ብሏል። ካዳስተርን የተገበሩ ከተሞች በሙሉ ከመሬት የሚሰበስቡት ገቢ እንዲጨምር ትግበራው ምክንያት ሆኗል።

እንደ አቶ ብዙነህ ገለጻ፤ የካዳስተር መተግበርን ተከትሎ በከተሞች ከመሬት የሚገኘው ገቢ የጨመረበት አንዱ ምክንያት የገቢ አሰባሰቡም ስለተሻሻለ ነው። ከዚህ ቀደም ከመሬት የሚሰበሰብ ገቢ የሚገኘው ግለሰቦች ቢሮ ሄደው ሲከፍሉ ብቻ ነበር።

በካዳስተር ትግበራ ግን ቤት ለቤት በመሄድ የመሬት ልኬት ተወስዷል። በዚህም በርካታ መሬት አጥረው የያዙና ከዚያ ውስጥ የተወሰነውን ብቻ የሚገብሩ የተቀረው ላይ የማይገብሩ እንዲሁም ለሙሉ ይዞታቸው ምንም የማይከፍሉ ተገኝተዋል። የተያዙ መሬቶች በሽያጭ የባለቤትነት ለውጥ ቢደረግባቸውም ውል ይዘው ስማቸውን ሳያዞሩ የቆዩም በርካታ ሰዎችም ተገኝተዋል። የካዳስተር ትግበራው ሰዎች ለያዙት ይዞታ በትክክል እንዲገብሩ፤ ሥማቸውን ያላዞሩም በህጋዊ ሥማቸውን እንዲያዞሩ በማስደረጉ ለከተሞች ተጨማሪ ገቢ መገኘት ምክንያት ሆኗል።

ካዳስተር ከተሞች ሀብታቸው የት እንዳለ እንዲገባቸው አድርጓል የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ መሬት ላይ የሠራ ከተማ ከተማውን መቀየር እንደሚችል በተግባር ተረጋግጧል ብለዋል።

እስከ 2017 በጀት ዓመት መዝጊያ ካዳስተር የሚተገብሩ ከተሞችን ብዛት 157 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከተሞቹ አስቀድመው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። የቀረው ይፋ ማድረግ ብቻ መሆኑንና እቅዱም እንደሚሳካ አስታውቀዋል።

‹‹ካዳስተርን የጀመሩ ከተሞች እየጨረሱ መሄድ አለባቸው፤ ያልጀመሩ መጀመር አለባቸው የሚል እቅድ አለ። አዳማ፣ ሞጆ፣ ቢሾፍቱ፣ ባቱ፣ ጅማን ጨምሮ ሌሎችም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ትንንሽ ከተሞችም መዝግበው ጨርሰዋል›› ሲሉም አስታውቀዋል።

ካዳስተርን ያልጀመሩ እንዲጀምሩ፤ የጀመሩ መዝግበው እንዲጨርሱ እየተደረገ መሆኑን አቶ ብዙአለም አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁለት ሺ 500 ከተሞች በላይ እንዳሉ ጠቅሰው፣ በእነዚህ ከተሞች ካዳስተርን የመተግበር ፍላጎት እንዳለም ተናግረዋል። ህጋዊ ካዳስተር የሚጠናቀቅ እንዳልሆነም አመልክተው፣ ህጋዊ ካዳስተርን ሙሉ በሙሉ ተግብረው ሲጨርሱ ፊስካል ካዳስተር ወደ መተግበር ይሸጋገራሉ ብለዋል። ለእዚህም አዳማና ሌሎች ከተሞች ንብረት መመዝገብ ጀምረዋል። ይሄንን ሲጨርሱና የመሰረተ ልማት መረጃዎች ልክ እንደ መሬቱ ዲጅታል ሆነው ሲጠናቀቁ ወደሁለገብ ካዳስተር እንደሚሸጋገሩ ተናግረዋል።

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ካዳስተርን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎች የሚሠሩት በዋናነት ዜጎች በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ነው። በተጨማሪ መንግሥት የተሻለ ገቢ አግኝቶ በቀጣይ ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ ሌሎች ሥራዎች እንዲሠሩ ለማስቻል ነው።

ከመሬት ጋር ተያይዞ የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥ እንዲዘምን እየተሠራ ይገኛል። አገልግሎት ሲፈለግ ቢሮ ሳይሄዱ በሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠይቆ ማግኘት የሚቻልበት አሠራር ለመዘርጋት እየተሠራ ነው። በዚህም ካዳስተርን በጨረሱ ከተሞች በስልክ ብቻ አገልግሎት ማግኘት ተችሏል።

‹‹ካዳስተር ትልቅ የአመራር ቁርጠኝነት ይፈልጋል›› ያሉት አቶ ብዙዓለም፤ ሥራው የሚፈልገውን በጀት፣ ቴክኖሎጂ ለመመደብና ከውስጥና ከውጭ ያለውን ጫና ለመቋቋም የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል። የተሻለ የአመራር ቁርጠኝነት ባለባቸው አካባቢዎች ካዳስተር በጥሩ ሁኔታ ሲተገበር፤ በአንጻሩ የአመራር ቁርጠኝነት በሌለባቸው አካባቢዎች ዝቅ ያለ አፈጻጸም እንደሚታይ አስታውቀዋል።

አመራሮች ለካዳስተር ትግበራ ቁርጠኝነት ሳይኖራቸው ሲቀር፤ አነስተኛ በጀት መመደብ፣ ለቦታው ብቃት የሌላቸውን አመራሮች መመደብና መሰል ሁኔታዎች ይስተዋላሉ ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህ በሚሆንበት ወቅት ባለሙያዎቹ የተሻለ አቅምና ተነሳሽነት ቢኖራቸውም የሚያስፈልጉ ነገሮች ባለመሟላታቸው ሳቢያ ካዳስተሩ ውጤታማ መሆን አይችልም ይላሉ።

ለካዳስተር ትግበራ ስኬት የማይሠሩ አንዳንድ አመራሮች፤ ሚኒስቴሩ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች በመገኘት ጥሩ አሠራር እንደሆነና ለመተግበር ዝግጁ እንደሆኑ ማረጋገጫ ቢሰጡም በተግባር ግን አስፈላጊ ነገሮችን ባለሟሟላት እንቅፋት መሆናቸው ችግር ነው ሲሉ አመልክተዋል።

ካዳስተርን በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል ጥሩ የአመራር ቁርጠኝነት አለ የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ሥራዎች በርዕሰ መስተዳደሩ በየጊዜው እንደሚገመገሙም አስታውቀዋል። በግምገማው በክልሉ በካዳስተር ጥሩ አፈጻጸም ያላመጡ ከተሞች አመራሮችን “መሬት መስረቅ ስለምትፈልጉ ነው” በማለት በግልጽ እንደሚነገራቸውም ገልጸዋል። የከተማ አመራሮቹም ለስርቆት እንዲመቻችሁ ነው መባልን ስለሚፈሩ በቁርጠኝነት ይሠራሉ ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህም የክልሉ ከተሞች የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው አስታውቀዋል። ሌሎች ክልሎችም መሰል የአመራር ቁርጠኝነት ካሳዩ በካዳስተር ውጤታማ መሆን እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡

በቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You