
በደም ጠብታ የበቀለ ስሜት ሙዚቃን ወለደ። ሙዚቃም በሕይወት ላይ ነብስን ዘራ። ሙዚቃ ሕይወት ሆነ። ከዚህ ሕይወት ማሕፀንም ራጋ ብቅ ብሎ ታየ። ራጋም ሬጌን አስከተለ። ሬጌም የሙዚቃ ሁሉ ጣዕመ ልኬት ሆነ። የሙዚቃ ማደሪያ በሆኑ ጆሮና ልብ ላይ ሁሉም ነገሠ።
ከአንዲትም መንደር ተነስቶ፣ የካሪቢያንን ደሴቶች ሁሉ በማቋረጥ፣ ለወረራና ቅኝ ግዛት ሳይሆን ተፈጥሯዊውን ማንነቱን ፍለጋ፣ ጉዞውን ወደ አፍሪካ ምድር አደረገ። ከአፍሪካም የሰው ዘር መገኛ ወደሆነችው ኢትዮጵያ ገሰገሰ። አዲስ አበባንም አልፎ ሻሸመኔ ላይ ከተመ። ዘመናትን ሲናፍቃት የኖረችን ሀገር ተገናኝቶም በፍቅሯ ወደቀ። እግሯ ስር ተንበርክኮም ጉልበቷን ሳመ። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ዓርማዋንም፣ ልቡ ላይ እንደማኅተብ አሰረው። ራጋ ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን የባሕልና እምነት፣ የተስፋና የነብሳቸው አዱኛ ያደረጉ የጃማይካ ልጆች በራጋ የሙዚቃ ወንዝ ሬጌን እየዘመሩ በኢትዮጵያዊነት ተጠመቁ።
ዓለም ሁሉ በአንድ ድምፅ “የሬጌው ንጉሥ” ብሎ የሾመውም ታላቅ ሰው አልቀረም። ሁሉም ወደ ራስታ፣ ሁሉም ራስታ ሆኑ። ራስታዎቹም ሬጌን ይዘው ለኢትዮጵያዊነት፣ ሬጌን አስረው ለሙዚቃ መነኑ። ይህ ታሪክ ነው። ታሪኩም ብዙ መነሻ፣ ብዙም መድረሻ አለው።
ከዚህ ታሪክ መጀመሪያና መጨረሻ ጋር ላይ ታች ዘለል! ዘለል! እንድንል ያደረገን አንድ ምክንያት ከወዲህ አለ። ምክንያቱም የሬጌው ንጉሥ ቦብ ማርሌይ ነው። ገና በ36 ዓመቱ፣ ምድርንና ሬጌን ተሰናብቶ ከሄደ 44 ዓመታት ቢቆጠሩም፤ ከንግሥናው ሳይወረድ፣ ከክብሩ ሳይጎድል ዓለም ሁሉ በየዓመቱ ይዘክረዋል። በወርሐ ጥር መጨረሻ፣ ባሳለፍነው ሳምንት ይሄው ነበር። የነበረውንም ለመጨረሻችን እንስጠውና መነሻችንን እንጀምረው።
“ሙዚቃ ሕይወት ነው” ሲባል፤ በተዝናኖት መንፈስ ብቻ ከመሰለን ስተናል። ምክንያቱም የዚህ አባባል ትክክለኛው ቅኔ ሲፈታ፣ ሙዚቃ የተወለደው በሕይወት መስዋዕትነት ውስጥ ነው። ጊዜውን በሕይወት ፈረስ የኋልዮሽ ጋልበን፣ የኛ የሆነውን ልጓም ስንስበው፣ በብዙዎች ዕንባ ጥቂቶች የሚስቁበትን እናገኛለን። በትንሽ ሕይወት ውስጥ ያለ ግዙፍ ባርነት እንመለከታለን። እጅግ የሚያስፈራ፣ ረዥምና ወፍራም ቀንበር የተሸከመችው ምስኪኗ ነፃነት አንጀት ትበላለች። ያ ዘመን ጥቁሮች በመልክና ማንነታቸው ሰውነትን የተነፈጉበት ነው። እናም ምሬት ብሶት፣ ተስፋ መቁረጥና አመጽ ከውስጣቸው መቀስቀስ ጀመረ።
በዚህ የብሶት አደባባይና የነፃነት ፍለጋ ውስጥ በጥቁሮች እልፍ ጥበብ ተወልዷል። ሙዚቃም አንደኛው ነው። ከሙዚቃ መካከልም ሦስቱን ለአብነት ያህል ገረፍ እናድርጋቸው። ካለንበት ዘመን ቀደም ብሎ የዓለምን ጨርቅ ያስጣለው “ብሉዝ” አንደኛው ነው። የዚህ የሙዚቃ ስልት አጀማመር፣ በባርነት ወጥመድ ውስጥ ከነበሩ ጥቁር አሜሪካውያን ጋር ይተሳሰራል። በሚደርስባቸው መከራ ብሶት ላይ ወደቁ። በብሶት ውስጥ ሆነውም ሕመማቸውን በትዝታ ማንጎራጎር ጀመሩ። እህህ!..ማለቱ ቁስልን ባይሽርም፣ ቢያንስ ማስታገሻ መድኃኒት ሊሆንላቸው እንደቻለ ተመለከቱ። ውስጣዊ ደስታን የሚሰጥ ሙዚቃዊ ፍስሐ ሆነላቸው። ደስታ ግን ለእነርሱ ያልተፈቀደ አደንዛዥ ዕፅ ነበርና ነጮቹን ጌቶቻቸውን ለማስደሰት አደረጉት። ለጌቶችም ዳንኪራ የሚመታበት መሳከሪያ ሆነ። ይህ የብሉዝ ሙዚቃ ስልት በቀደመው ኃያልነቱ ባይሆንም አሁንም ድረስ የሚገለገሉበት ብዙዎች ናቸው። የሬጌዎች መጀመሪያም በብሉዝ ድልድይ የተሻገረ ነው።
ዓለማችን ላይ፣ በተለይ በወጣቱ ክፍል እጅግ ተወዳጅ በሆነው የራፕ ሙዚቃ ውስጥ፣ ስለምንድነው የጥቁሮች ብቻ እስኪመስል የፈሰሱበት? የሚል ጥያቄ ያጫረብን ስንቶቻችን እንሆን…ይሁንና ለጥቁሮች ብቻ የተሰጠ ባይሆንም፤ አምጠው የወለዱት ግን እነርሱ ናቸው። ዛሬ የነፃነት ባሕር ዳርቻ ባደረጉት የራፕ ሙዚቃ ውስጥ፣ በጥቁሮች አንገት የምንመለከተው ሠንሠለት፣ ያኔ ለፋሽን ሳይሆን በባርነት የሚታሠሩበት ነበር። ከወገብ ወርዶ የምንመለከተው የራፐሮቹ ሱሪ፣ ያኔ በጫንቃ የተሸከሙትን ሸክም በሁለት እጅ ደግፈው፣ ማሠሪያ የሌለውን ሱሪ ሲወርድ ከፍ ለማድረግ ካለመቻል ነበር። ይሄኛውን ስልት፣ ከግጥሞቹ አንስቶ እስከ ሙዚቃው ምት ያለውን ብንፈትሸው፣ ከብሶት ይልቅ አመፅ የሚታይበት ነው። በጉልበት የተወሰደውን ነፃነት፣ በሙዚቃዊ ወኔ ጀግነው ለማስመለስና ለማስከበር የሚደረግ ትግል እንመለከትበታለን። ውስጡ ሲፈለቀቅ “እሾህን በእሾህ” የሚመስል ነገርም አለው። እንደ ሽለለና ፉከራ ሁሉ ከድምፅ ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ የሰውነት እንቅስቃሴ ይገኝበታል። የራፕ ሙዚቃ ስልት ንጉሥ የነበረው ጥቁሩ አቀንቃኝ ቱፓክ ሻኩር፣ የዓለምን የሙዚቃ ልብ በፍቅር እንደሰቀለ፣ ገና በወጣትነቱ ሕይወቱን እንዲሰዋበት ሆኗል።
በሦስተኛ ደረጃ፣ ለዘመናት ነግሦ የዘለቀውን የሬጌ ሙዚቃን እናገኛለን። ይሄኛው የሙዚቃ ስልትም፣ ነፃነትን ከሚናፍቀው፣ ከጥቁሮች የጥበብ ልብ ውስጥ ብቅ ያለ ቢሆንም፤ ከሁሉም በሁሉም የተለየ ነገር አለው። ሬጌ የይቅርታና የንፁሕነት ቤት ነው። “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እያለ ጥላቻን በፍቅር ይሽራል። ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ነፃነት፣ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለጠላቶቻችንም ጭምር ይሁን የሚል መንፈስ አለው። በዚህ ሁሉ መሐል ታዲያ፣ ሬጌ እኩልነትን እንጂ ባርነትን አይወድም። ምርጫ አሳጥተው እስትንፋሱን ለመቀማት የተነሱ ዕለት ግን “ለወደደን ማር፣ ለጠላት እሬት” ነውና የኢትዮጵያዊነትን ደም የመሰለ መሆኑ አንድም ለዚህ ነው።
ሬጌ የተወለደው የቱ ጋር ነው ካልን፣ ጥቁሮች ከአካላዊ ባርነት እያመለጡ፣ ስለ መንፈሳዊው የውስጥ ነፃነት ከሚታገሉበት ነው። አፈር ከሚበላው ሥጋ ይልቅ፣ ምስጥ ለማያውቀው የውስጥ ማንነት መጨነቅ ሲጀምሩ ነበር። ፈጣሪ በአምሳሌ ፈጥሬዋለሁ ያለውን የተፈጥሮ ሰውነት ፍለጋ የተወጣበት ነው።
ዛሬ ዓለም ሁሉ ልብን የሚያርስበት ቅባት የሆነው የሬጌ ሙዚቃ መነሻው ጃማይካ ውስጥ ነበር። ነገር ግን ከጥንት ጃማይካ ውስጥ የነበረው፣ ቱባ ማንነትን የያዘው የሙዚቃ ስልት ሬጌ ሳይሆን “ራጋ” ነበር። አሁን ላይ ራጋ፣ አንደኛው የሬጌ ስልት ዓይነት ነው። “ሬጌ” የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዓለም እየታወቀ ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምር ነበር። ብዙዎች እንደሚሉት፣ የዚህ ስያሜ መነሻው በ1968 ዓ.ም፣ በጃማይካዊው ፍሬድሪክ ናትናኤል (ቱትስ) ሂበርት፣ የተሠራው “ዱ ዘ ሬጌ” ሙዚቃ ነው። ንግሥናው የቦብ ቢሆንም፤ ቱትስ የሬጌ አባት ለመባልም በቅቷል። ሁሉም ጃማይካውያን ቢሆኑም የሁሉም ልብ ግን ኢትዮጵያዊ ነበር።
ነገሩ አባባል አይደለም…ጃማይካውያንን ከኢትዮጵያ ጋር ያዛመደው ድልድይ፣ ኃይለ ሥላሴያዊው ፍቅር ብቻ ነው ብለን ካሰብን አሁንም መሳሳታችን ነው። ይህ በእርግጥ ትልቁ እውነት እንጂ ብቸኛው እውነት አይደለም። ከኢትዮጵያዊነት ጋር ድልድይ የሆነላቸው “ራስ ተፈሪያን” የመጣው ከጃንሆይ ትውውቅ በኋላ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያዊነት ያመኑት ግን ገና ሳያውቋቸው በፊት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ፤ በባርነት ከኢትዮጵያ ምድር ተሽጠን የመጣን ነን ብለው ያምኑ ስለነበር። በዚህ መሐልም፤ ጃማይካውያኑ ነቢያችን ብለው የተቀበሉት ማርከስ ጋርቬይ አንድ ትንቢት ነገራቸው። ቅሉ የማርከስ ማንነት በሃይማኖታዊነት ሳይሆን በጥቁሮች መብት ተሟጋችነት የተገነባ ነፃነት ናፋቂ ነበር። አሜሪካ ውስጥ የሚኖር ጃማይካዊ ቢሆንም ትግሉ ለሁሉም ጥቁር ነበር። “ጥቁሮች ወደ እናት ምድራቸው መመለስ” በሚለው እንቅስቃሴው ዓለም ሁሉ ያውቀዋል። የጃማይካውያን እናት ምድርም ኢትዮጵያ ናት ብሎ ያምናል። ለጃማይካውያኑ ዘመዶቹ የነገራቸው ትንቢትም “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ። እኛን ከባርነት ነፃ ለማውጣት፣ ከወደ ምሥራቅ የሚመጣ ታላቅ ሰው አለ” የሚል ነበር።
እዚህ ጋር ከፊትም ሆነ ከኋላ አንድ መጽሐፍ ሊወጣው የሚችል ታሪክ ያለ ቢሆንም፤ ሲጠብቁ የነበረው ነፃ አውጪ፣ ጃንሆይ ናቸው ብለው ያመኑትም ሆነ ያወቋቸው፣ ትንቢቱን ከሰሙ ከዓመታት በኋላ ነበር። ጃንሆይ እንደሆኑ በመቀበል ራስ ተፈሪነትን ያስነሱት ከ1923 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ ጃንሆይን የተገናኙት ግን በ1958ዓ.ም ነው። ጃንሆይ የጃማይካን ምድር በረገጡ ጊዜ የተከሰተው የዝናብ ሁኔታ ደግሞ፤ እሳቸውን የፈጣሪ መልዕክተኛ ናቸው ብለው የማመናቸውን ትክክለኛነት አረጋገጠላቸው።
በዚያው ዓመት ስምንት ጃማይካውያን ብቻ ኢትዮጵያን ረገጡ። ሻሸመኔንም ቤታቸው አደረጉ። ከዚህ በኋላ ማን ቀረ…ልቡ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፍቅር የሚቃጠለው የሬጌው ንጉሥ ቦብ ማርሌም ወዲህ ተጓዘ። ወደቀደመው የተፈጥሮ ማንነታችን እንመለስ የሚለው የሬጌ ሙዚቃ ቅኔም ሲፈታ፣ የሁሉም መጀመሪያ ወደሆነችው ኢትዮጵያ መመለስ አንደኛው ነው። ከራጋ የማንነት አፈር ላይ የበቀለውን ሬጌም ከተነሳበት የኢትዮጵያ አፈር ላይ ዘሩት። ከዘሪዎቹም አንደኛው ታላቁ ቦብ ማርሌ ነበር።
አሁንም ብዙ ታሪኮችን ዘለን፣ ፊታችንን ወደ ቦብ ማርሌይ እናዙር። ቦብና ሙዚቃዎቹ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የነፃነት ሰንደቅ ነበሩ። የፍቅር ተምሳሌት፣ የአንድነት ማሰሪያ ክታብ ናቸው። ከአፍሪካ መሪዎች ፊት ከነጊታሩ ሰተት ብሎ ወጥቶ “አፍሪካን ዩናይት” በሙዚቃው እንደ ተዓምር ያለውን ነገር ሠርቶ የወረደ ጀግና ነው። ማጨብጨብ ብቻ ሳይሆን እጁንም ስመውታል። ይህንን ታላቅ ጀብዱ ሲሠራም በሬጌ ሙዚቃ ነበር። ነገሩም የግጥምጥሞሽ ሳይሆን የሬጌ ሙዚቃ መንፈስ የሚገነባው ከአንድነት፣ ሰላም…በመሆኑ ነው። ቦብ ማለት ሬጌ፣ ሬጌ ማለት ቦብ እስኪመስለን ድረስ ተመሳስለዋል። የሙዚቃን ሕይወትነት ሳይሸራርፍ የምናገኘውም በሬጌ ውስጥ ነው።
የሬጌው ንጉሥ፣ ታላቁ ቦብ ማርሌ የተወለደው፣ በአውሮፓውያኑ ጥር 29 ቀን 1934 ዓ.ም በጃማይካዋ የኪንግስተን መንደር ውስጥ ነበር። ድህነት አፉን የከፈተባት ከተማ ነበረች። ለዚህ ሕጻን ወላጆቹ ያወጡለት ስም ታዲያ፤ ቦብ ማርሌ አልነበረም። ብዙዎች የማያውቁለት የልጅነት ስሙ “ሮበርት ኔስታ ማርሌ” ነበር። ይህ ስም ግን፣ በአመዛኙ የሴቶች መጠሪያ መሆኑን ሲገነዘብ “ቦብ ማርሌ” ሲል ለራሱ አዲስ ስም ሰየመ። ቦብ ልጅነቱን በፍቅር የሰጣቸው ሁለት ነገሮችም ሙዚቃና እግር ኳስ ነበሩ። የሙዚቃ መድረኮች ላይ ከመውጣቱ አስቀድሞ፣ ሁሌም እግር ኳስ የመጫወት ልማድ ነበረው። ቦታው ስቱዲዮ ቢሆን እንኳን በእግሩ ኳስን ሳያንጠባጥብ ወደ ሙዚቃ አይገባም። ለመድረክ የሚሆነውን ነፃነት የሚሰበስበው ከእግር ኳስ ላይ ነበር። ቦብን በዝና ያናኘው፣ ወደ ሙዚቃው ከገባ ከጊዜያት በኋላ ያቋቋመው “ዘ ዌይለርስ” የተሰኘው የሙዚቃ ባንድ ነበር። ከባንዱ አባላት ጋር በመሆኑ በአሜሪካ፣ በእስያና አፍሪካ ጭምር እየተዘዋወሩ የሬጌን ድምፅ አሰምተዋል።
ቦብ ደስታን ብቻ ሳይሆን አዕምሯዊና ሥነ ልቦናዊ ለውጥን መፍጠር ይችልበታል። የሀገሩን ሁለት ደመኛ ፓርቲዎችን ወደ አንድ ለማምጣት የወጣበት መድረክ አይዘነጋም። በነበረው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ፣ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ በሙዚቃው ገድል ሠርቷል። “ባቢላን” የሚለው ሙዚቃው ምድራችን ላይ የባርነትና የጭቆናን ግንብ እየገነቡብን ነው ስለሚላቸው ነጮች ነው። ቡፋሎ ሶልጀር፣ ሪዴምሽን ሶንግ…በበርካታ የትግል ሙዚቃዎቹ የአሜሪካን ሲአይ ኤ’ን ጨምሮ፣ በብዙ የነጭ መንግሥታት፣ በክፉ ዓይን እንዲታይ አድርጎታል። ቢሆንም ግን፤ በቦብ ማርሌይ ተማርከው የአድናቆት እጃቸውን የሰጡት ከጥቁሮች ይልቅ ነጮች ናቸው። የአብዛኛዎቹን በዘረኝነትና ጥላቻ የጎደፈውን ልባቸውን በሙዚቃዎቹ አጥቦላቸዋል።
ዓለም ሁሉ አፉን ከፍቶ በሚያደምጠው ሰዓት፣ ለሚወደው ነገር ኖሮ በሚወደው ነገር ሕይወቱን አጣ። ገና በ36 ዓመቱ ሥጋው ከአፈር ላይ አረፈች። ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ ለሆነው ሞቱ፣ ከወዲህና ወዲያ የሚጎርፉ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ የእግር ጣቱ ላይ በተፈጠረችው ቁስል እንደሆነ ብዙኃኑ ይስማማበታል።
የሙዚቃ ምቱ አንድ ወደላይ አንድ ወደታች ባለቁጥር ሁሉ የቦብን ስም ይጠራል። ይህን ሁሉ ያናዘዘችን፣ ሰሞነኛዋ የቦብ ማርሌይ የመታሰቢያ ልደት ቀን፣ ስሙን ይዛ ሉሏን ዓለም ዞራለች። የንጉሡን ንግሥና ሳትሽር፣ ከፍ አድርጋ አውለብልባዋለች። ሁሌም በሁሉም ልብ ውስጥ እንደነገሠ ቢኖርም፤ የሁሌም ጥር 29 በመጣች ቁጥር ሁሉ ግን የእርሱ ቀን ናት። በየዓመቱ፣ በየዓለማቱ ስምና ሥራውን እያወሱ፣ በፌስቲቫልና የሙዚቃ ድግሶች ይዘከራል። ሬጌም የክት ቀሚሷን የምትለብሰው የዚያን ዕለት ነው። ከካሪቢያን ደሴቶች እስከ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ፣ የሚነፍሰው አየር ሳይቀር፣ ቦብና ሥራው ነው።
ስሙ ከሀገራቸው ጋር ተያይዞ እንዲነገርላቸው የሚፈልጉ ብዙ ቢሆኑም፤ እንደ ሀገሩ በሚመለከታትና በሚወዳት ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ቦብ ማርሌይ የሚታሰብበት ዝግጅት በትንሹ ነው። በአዲስ አበባና በሻሸመኔ ከተሞች ውስጥ እንዲሁ በፍላጎት ሰብሰብ ተብሎ ከሚያዘጋጅ በቀር ጎልቶ ሲወጣ አይታይም። ምናልባትም ካነሳንም የዛሬ 20 ዓመት በመስቀል አደባባይ፣ 250 ሺህ ያህል የታደሙበት የ60ኛ ዓመቱን ነው። በዘንድሮው መታሰቢያውም፣ በጥር 29 ቀን 2017ዓ.ም፣ በመሶብ የሙዚቃ ማዕከል በማይናቅ ሁኔታ ተከብሯል። ይህን የ80ኛ ዓመት መታሰቢያውን በማዘጋጀቱም፣ የአራዳ ኤፍ ኤም 95.1 “የጥበብ ሞገድ” እንዲሁም ኢቢሲ ኤፍ ኤም 104.5 “ዋት ኤቨር ኢዝ ክሌቬር” በጋራ በመጣመር ዝግጅቱን የተዋበ አድርገውታል። በዘንድሮው ብቻ ሳይሆን ሁሌም በየዓመቱ፣ የሀገራችን የሬጌ ሙዚቃ ፈርጦችና ልዩ ልዩ ባንዶች ዕለቱን ያደምቁታል። በዚህ ዝግጅት ላይ ወንበሮቹም እነርሱን ይናፍቃሉና የራስታ ማኅበረሰብ አባላት አልቀሩበትም።
ቦብ ማርሌ ለበርካታ ዓመታት በሀገራችን ሲኖር፣ ስምና ዝናውን ለመጠቀም ሳንችል ቀርተናል። በደርግ መንግሥት ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ ባዘጋጀው ኮንሰርት የታደሙለት በቁጥር የአንድ ክፍል ተማሪ የማይሞሉ ነበሩ። ይህ የሆነበት ምክንያትም፤ የአንበሳውን ምስል ይዞ ደርግ ፊት ይወጣና ያስፈጀናል ከሚል ስጋት ነበር። ወደ ኮንሰርቱ የገቡትም ዲፕሎማትና ጥቂት ባለሥልጣናት ነበሩ። ቢገባን ሀገራችንን ለዓለም ለማስተዋወቅ የምንጠቀምበት ሰው ነበር። ከሀገሩ አልፎ፣ በሙዚቃዎቹ አፍሪካን ከአብዛኛው የዓለም ማኅበረሰብ ልብ ውስጥ ለማስረጽ የቻለ ድንቅ የሬጌ ጠቢብ ነበር።
ቦብ በእርግጥም በኢትዮጵያ ፍቅር ተነድፎ ነበር። “ፍቅረ ሥላሴ” ተብሎ እስከመጠራት ደርሷል። ታላቁን ልጁን ዚጊን ጨምሮ ባለቤቱም ሪታም እንዲሁ ናቸው። ከኢትዮጵያ ወደ ጃማይካ በሄደ ጊዜ እንኳን ከነበሩት 13 ልጆች መካከል አንደኛው ኢትዮጵያዊ ነበር። እርሱም በጉዲፈቻ መልክ ሲያሳድገው የነበረው አሰፋ አበበ ነው። አሰፋ የሚለውንም ስም በብዛት በጃማይካ አትሌቶች ውስጥ ሰምተነው ይሆናል፤ ለአብነትም አሰፋ ፖል። በዚህና በሌሎችም በበርካታ የጃማይካ ቤተሰቦች ውስጥ አሰፋን እናገኛለን። ሬጌም በራጋ ተወልዶ፣ በንጉሡ ቦብ ማርሌ የሙዚቃ ጣዕመ ልኬት ሆነ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም