
የየካቲት ወር ከኢትዮጵያ አራቱም አቅጣጫ የጠላትን ወረራ ለመከላከል የከተተው የኢትዮጵያ ጦር በዓድዋ ጣፋጩን የድል ጽዋን የተጎነጩበት የጠላት ጦር ደግሞ መሪር የሽንፈት ጽዋ የቀመሱበት ነው:: ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል በአሸናፊነት ደስታ ሲሰክሩ ጠላት ደግሞ በተሸናፊነት አንገት የደፋበት ነው ::
ሸንፈቱ አፍሪካን ለመቀራመት በበርሊን የተመካከሩትን ቅኝ ገዥዎች ሁሉ ያሸበረ፤ የቅኝ ገዥዎችን ልብ የሰበረ ነው። ኋላቀር መሣሪያውን ታጥቆ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከፍ ባለ የሀገር ነፃነት እና የሀገር ፍቅር መንፈስ ለትውልዶች የሚተላለፍ አንፀባራቂ ድል የተቀዳጁበት ነው::
በሀገራችን ብሂል ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንደሚባለው ሁሉ የካቲት መካተት ክተት ማለት ነው:: ገበሬው በክረምቱ ያረሰውን አጭዶ ወቅቶ አበራይቶ ወደ ጎተራው የሚከትበት ወቅት ነው:: በአጋጣሚ ደግሞ በየካቲት በዓድዋ ለመዝመት ክተት ሲባል የዘመተበት ነው:: የተደረገው ጦርነት በአብዛኛው ሕዝቡ በግብርና ለሚተዳደርባት ሀገራችን ምቹ ነበር:: የጦርነት ምቹ ባይኖረውም ወቅቱ የገበሬው እረፍት ወቅት ስለነበር ማለት ነው::
ዓድዋ ማለትም ተሰባሰቡ ተመካከሩ የሚል ብያኔ አለው በትግርኛ:: ዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ ሲሰደዱ መጀመሪያ በአክሱምና በዓድዋ ነው የተገኙት፤ እናም ተሰዐቱ ቅዱሳን በዓድዋ ተሰባስበው ተመካክረው ስለነበረ ቦታው ዓድዋ እንደተባለ አንዳንድ ሰነዶች ያስረዳሉ:: ከአራቱም አቅጣጫ ዓድዋ የተሰባሰበውና የተመካከረው ጦር የጠላትን ቀንበር በመስበር ድል አድራጊነት ለአፍሪካና ለካሪቢያን ሀገሮች አጎናጸፈ:: ዘንድሮ የሚከበረው 129ኛው ዓመት የዓድዋ ድል ‹‹ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል›› በሚል መሪ ቃል መሆኑም ይህንኑ የሚናገር ነው::
በዓድዋ ሁሉም ዘምቷል ከበርቴው፣ ጭሰኛው፣ ወይዛዝርቱ፣ ወራዙቱ፣ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ፣ ቄሶቹ፣ ሼሆቹ እረኛው ሁሉ አርበኛ ሆኖ ለእናት ሀገሩ የተዋደቀላትና ድልን ያጎናጸፋት ነው:: ዓድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ጠላትን ለመከላከል ሲዘምት እስከ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በእግሩ ሄዶ ነው የተጋደለው::
ታዲያ ሲዘምቱ ወኔ ቀስቃሽ የኪነጥበብ ሰዎች ነበሩ:: እንደ ማሲንቆ መቺዎች ያሉ:: በግጥማቸው ማሲንቆ እየመቱ እያዜሙ በለው በለው ይሉ ነበር:: በአምስቱ ዓመት የፋሽስት ወረራ ወቅት ማሲንቆ መያዝ ታግዶ ነበር:: ይህም የሆነው ፋሽስቶች አይተው ማሲንቆ መቺዎች ፕሮፖጋንዳ እየነዙብን ነው በሚል ስጋት ነበር::
ወደ ግጥም እንመለስና ግጥም የሥነጽሑፍ አንድ ዘርፍ ነው:: በውብና ቁጥብ ቃላት እምቅ መልዕክት የሚተላለፍባት:: ግጥም በቀላሉ ለመያዝ የሚመች በትውፊት በቃል ለትውልድ የሚተላለፍ ነበር:: በዓድዋ ድል ጊዜ ግጥም አንዱ ወኔ መቀስቀሻ ነበር:: ከዓድዋ ድል ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመናችን አያሌ ግጥሞች ዓድዋን ተንተርሶ ተገጥመዋል:: የዓድዋ ግጥሞች በዘመቻው ወቅት፣ በጦርነቱ ጊዜ እና በድሉ ጊዜ እንዲሁም ከዓድዋ ድል በኋላ የተገጠሙ ናቸው:: ዓድዋ በየዓመቱ አዲስ ስለሆነ አዳዲስ ግጥሞች ወደፊትም ይኖራሉ::
ደራሲ ታደለ ገድሌ በጻፉት መጽሐፍ በዓድዋ ጦርነት ገኖ ከሚነገርላቸው ጀግኖች ውስጥ በ1887 ዓ.ም የመንግሥት ልዑካንን ቀኛዝማች ገነሜንና መምህር ገ/እግዚአብሔርን መርተው ሞስኮ ደርሰው የተመለሱት ፊታውራ ዳምጠው አንዱ ነበሩ ይላሉ:: ሩሲያ የሄዱት ለዓድዋ ጦርነት ወታደሮች የሚያክሙ የሐኪሞች ቡድን ለማምጣት ነበር:: ጦሩ ሊዘምት አዲስ አበባ ስለደረሱና ድካም ላይ ስለነበሩ እንዲቀሩና አዲስ አበባ እንዲጠብቁ ተጠየቁ:: እሳቸው ግን እሄዳለሁ ብለው ጦሩን ተቀላቀሉ:: ደራሲ ታደሰ ገድሌ እንደጻፉት በወቅቱ ገጣሚ
‹‹እሪ በሉ ግሽ፣ ስማ ተሁለደሬ፣ ሠፈር ጠብቅ አሉት የጦሩን ገበሬ::››
ፊታውራሪ ዳምጠው ከፊት ለፊት የገጠማቸውን የጠላት ጦር አሸንፈው በማባረር ላይ እንዳሉ በተተኮሰባቸው ጥይት እንደነጎራው ገበየሁ፣ ደጃች ጫጫ፣ እንደነታፈሰ፣ እንደነበሻህ አቦዬ ሕይወታቸው አልፏል:: በእነዚህም ጀግኖች ሞት መላው የዓድዋ ዘማች ሠራዊት ከማዘኑም ባሻገር ኃዘኑን በግጥም ገልጾ ነበር::
‹‹ያጐራው ገበየሁ ምን አሉ ምን አሉ፣
እነ ደጃች ጫጫ እነ ደጃች ባሻህ ምን አሉ ምን አሉ::
ተማምለው ነበር ከጦሩ ሲገቡ፣
የኢትዮጵያን ነፃነት በደም ሊገነቡ::
ያበሻህ አቦዬ ያጐራው ገበየሁ ሁለቱም ያበዱ፣
እንቅር አይልም ወይ አንዱ ሲሄድ አንዱ::
አበዛው ገበየሁ ነጩን ሲጋግር፣
ታፈሰ እያረደ ሥጋውን ሲመትር፣
መትረው ጋግረው ሄዱ ሳያዩ ግብር:: ››
የ25 ዓመት ወጣት የነበሩት ቀኛዝማች ታፈሰ በዓድዋ ጦር ሜዳ ጀብዱ ሠርተው የሞቱ ጀግና ናቸው:: የተቀበሩት በዓድዋ ሥላሴ ነው:: በወቅቱ እንዲህ ተገጥሞላቸው ነበር::
እንደሄደ ቀረ እንደገሠገሠ፣
የንጉሥ ባለሟል ቀኛዝማች ታፈሰ::
እንደዋርካ ቅጠል እንደ ትላልቁ፣
የታፈሰ አሽከሮች ረግፈው አለቁ::
የዓድዋን ሥላሴን ማን ዳኛ አድርጎኃል ፣
አባትና ልጁ ይፈጠሙብሃል::
ፊታውራሪ ዳምጠው በዓድዋ ጦርነት በጀግንነት ተዋግተው መውደቃቸውን ዘመዶቻቸው ተረድተው ውሎ ተደርጎ ተለቀሰላቸው በዚህ ጊዜ አልቃሽ
‹‹እንዝርቱ ቢጠፋ ቢታጣ ደጋኑ፣
ጌታዬ አሽከሮችህ ዳምጠው ተበተኑ::
በዓድዋ ጦርነት ሊቀ መኳስ አባተ በያዙት መድፍ አነጥጥረው የጠላትን መድፍ ባፉ አግብተው ሰባብረውት ነበር:: ስለሳቸው በጅሮንድ ባልቻ እንዲህ ገጠሙ ሲሉ ተክለጻዲቅ መኩሪያ ጽፈዋል::
አባ አባ ይትረፍ ነገረኛ አዋሻኪ ሰው፣ ይህን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው::
አበሻ ጉድ አለ ጣሊያን ወተወተ ፣ ዐይነጥሩ ተኳሸ ቧ ያለው አባተ::
በዓድዋ ጦርነት ወቅት የጀግንነት ሥራ ከሠሩት እና ከተሰዉት አንዱ ፊታውራ ገበየሁ ነበሩ:: ከሞታቸው በፊት
የዓድዋን ሥላሴ ጠላት አረከሰው፣
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው::
ተብሎ ተገጥሞላቸው ነበር::
ገበየሁ ሲሞቱም ገጣሚ
‹‹ገበየሁ ሞተ ተተካ ባልቻ፣
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ::
ተብሎላቸዋል::
የ25 ዓመት ወጣት የነበሩት ቀኛዝማች ታፈሰ በዓድዋ ጦር ሜዳ ጀብዱ ሠርተው የሞቱ ጀግና ናቸው:: የተቀበሩት በዓድዋ ሥላሴ ነው::
አንድ የተጉለት ሰው በዘመቻው አንድ ልጁን ስላጣ ሀገሩ ሲገባ እንዲህ ብሎ ተለቀሰ ይባላል::
ይለቀስለታል ሁሉም በየቤቱ፣ እንኳን ደህና ገባህ ዳኘው ባለቤቱ::
በጦርነቱ ወንድሟን ያጣች እህትም
‹‹ ከአሞራም አሞራ ነጭ አሞራ አልወድም ፣ በልቶብኛልና ፈረስና ወንድም::››
ሁለት ታላቅና ታናሽ ልጆችዋን ያጣች እናትም በእንጉርጉሮ
‹‹ሥጋ ይዞ አለፈ አሞራ በደጄ፣
የታላቁ ይሁን የታናሹ ልጄ::››
ጦሩ ከዓድዋ ድል በኋላ በ12 ቀኑ ነው ወደ ሸዋ የተመለሰው:: አዲስ አበባ ሲደርሱ ሕዝቡ በደስታና በእልልታ ተቀበላቸው:: በወቅቱ ግዳይ ሲጣልና ሲፎከር ከተገጠሙት ግጥሞች መካከል
‹‹… በሠራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ፣ ተፈጠመ ጣልያን ሀበሻ እንዳይደርስ:: … መድፉን መትረየሱን ዓድዋ መሬት ዘርቶ ፣ እንክርዳዱን ነቅሎ ስንዴውን ለይቶ
የተዘራውን ውል አጭዶና ወቅቶ ፣
ላንቶሊኒ አሳየው ፍሬውን አምርቶ::
የዓድዋ ድል እንደ ጠጅ እየቆየ በሄደ ቁጥር የሚቆነጅ (የሚጣፍጥ) እንጂ የሚጎመዝዝ፣ የሚፈዝና የሚደበዝዝ አይደለም:: እየደመቀና እያደመቀን የሄደ የድል ቀንዲል ነው::
በዓድዋ ድል ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ ዕውቅና ሰጥተው ዲፕሎማሲያው ግንኙነት የከፈቱበት ነው:: ኢትዮጵያ ከጣሊያን፣ ከፈረንሣይ፣ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከሩሲያና ከጀርመን (ከስድስት ሀገራት) ጋር አንድ መቶ ሩብ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አዳብራ እና አፅንታ የቆየች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር ነች:: በሊግ ኦፍ ኔሽን አባልም የሆነችው በዓድዋ ድል ያመጣው ቀንዲልና እውቅና ነው:: ተመድ ሲመሠረትም ከመሥራች ሀገሮች አንዷ ነበረች::
በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ ያደረገው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ አዳራሽንና ጽሕፈት ቤቱን በኢትዮጵያ ወጪ በመሥራታቸውና በዲፕሎማሲው በማሳመናቸው ነው:: የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት አዲስ አበባ የሆነው እና የቻይና መንግሥትም የአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤትንና ስብሰባ አዳራሽን በአዲስ አበባ የሠራው የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ቀንዲል መሆኑ ቅቡልነት እና ተቀባይነቱ አሁንም እየጎላ በመሄዱ ነው:: የዓድዋ የድል ጮራ ኢትዮጵያን ወደ ዲፕሎማሲ ጎራ የቀላቀለ አዲስ አበባንም ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ከተማ እንድትሆን በር የከፈተ ነው::
ስለ ዓድዋ ከተጻፉ ግጥሞች በስፋት ዕውቅናና አድናቆት የሚቸረው የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ‹‹እሳት ወይ አበባ›› ግጥም መድብል ውስጥ የሚገኘው ‹‹ዓድዋ›› የተሰኘው ግጥም ነው። አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁም በትምህርት መጽሐፋችን ታትሞ ትዝታ ሆኖብኝ ነበረ:: ሎሬት በግጥማቸው ዓድዋን መልክዓ ምድራዊ ገጽታዋን በሕሊናችን ስለውታል:: ሃሳባዊ ወሰኗን አድማስ ተሻጋሪ፣ ሰማይ ታካኪ አድርገው ገልጸውታል:: ታሪካዊ ስፍራዋ የአጽም ርስትና የደም ትቢያ የተሸበለለባት መቀነት ብለውታል። በዓድዋ ታሪካዊ ስፍራ በተከፈለው መስዋዕትነት ከባርነት መንጭቆ ነጻነትን ሲያጎናጽፍ፣ የኩራት ቅርስ መሆኗንም ሰፊውን ታሪክ በስንኞች እንዲህ ቋጥሯታል ሲል አየለ ያረጋል የዓድዋ ስንኞች በሚል በጻፈው ጽሑፍ እንዲህ ከትቦታል።
‹‹አድዋ ሩቅዋ የዓለት ምሰሶ የአድማስ ጥግዋ፣
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ…
ዓድዋ የዘር አፅመ ርስትዋ- የደም ትቢያ መቀነትዋ
ከሞት ከባርነት ሥርየት- በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ እ’ ለት
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ- የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ…››
ነፍስ ሔር ደራሲ ነብይ መኮንን በ‘ስውር ስፌት’ የግጥም መድብሉ የዓድዋን ድል ሲያመሰጥረው ዓድዋን ‘በደም ግብርነት’ ይገልጸዋል።
“ዓድዋ የደም ግብር ነው፤ አበው የለኮሱት ቀንዲል፣
ዓድዋ የአፍሪካ ዱካ ነው፤ አበሽ የከተበው ፊደል፣
ላጥፋህ ቢሉት መች ይጠፋል፤ ጠላት በልቶ ያፈራ ተክል::
ደራሲ አበረ አዳሙም ‹‹ፍርድ እርድ›› በሚል የግጥም መድብላቸው ዓድዋ ቀበሌ፣ ሠፈር፣ መንደር አይደለም ዓለም ነው ይሉናል:: ዓለም በኦሮምኛ አዱኛ የሚል ፍቺ አለው በአማርኛ ደግሞ አዱኛ ማለት አዶናይ ማለት ጌታ ሀብት፣ ዓለም ማለት ነው:: ዓድዋ ዓለም ሀብት ነው ማለት ነው::
ዓድዋ ሰፈር አይደለም-ዓድዋ መንደር አይደለም
ሀገር ነው ከነታሪኩ-አሕጉር ነው፣ ሰ……ፊ ዓለም።
እነምኒልክ ጦር ይዘው-ከመድፍ የተዋደቁ ጎራዴ መዘው የሮጡ-በጠብ-መንጃ አፍ ያለቁ ለጓጉለት ነፃነት-ደማቸውን ያፈሰሱ
ለሰፈር ብቻ አይደለም-ያሕጉር ድል አታንኳሱ።
ዓለም ናት ዓድዋ ቤቱ – ሀገር ናት የድል ትራሱ
ለጠበበ የዘር ቅኔ – የደም ድል አታሳንሱ!
ስለ ዓድዋ ሲነሳ በዘፈኖቻችን እምብዛም ቦታ የተሰጠው አይመስልም:: እጅጋየሁ ሽባባው የዘፈነችው ዘፈን አንድ ለእናቱ እስኪመስል ስለዓድዋ ሲነሳ ሲወሳ በሬዲዮ በቲቪ የሚደመጠው የሚመስጠው ዘፈንዋ ብዙ የሚናገረው ነገር አለ:: ዓድዋ የጥቁሮች ድል መሆኑን ይናገራል:: ምናልባት በዓድዋ ዘፈን ዙሪያ የግጥምና የዜማ ደራሲያን ስለዓድዋ ብዙ ይጠበቅባቸዋል ብለን በእጅጋየሁ ሽባባው ዓድዋ ዘፈን ግጥም እንሰናበታለን::
‹‹…የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት ፣
ስንተ ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር፣
ትናገር ዓድዋ ትናገር ትመስክር::
ትናገር ዓድዋ ትናገር ሀገሬ ፣
እንዴት እንደቆምኩኝ በክብራችሁ ዛሬ::…
የጥቁር ድል አምባ ዓድዋ፣
አፍሪካ እምዬ ኢትዮጵያ
ተናገሪ ተናገሪ
የድል ታሪክሽን አውሪ:: ››
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም