«አልቦ ዘመድ »የሚለው መጽሐፍ በአምባ ሳደር ብርሃኑ ድንቄ በዐሥራ ዐራት ምዕራፎች፤ በሰባ ስድስት ገጾች ተዘጋጅቶ ለንባብ የበቃ ምሥጢር ጠለቅና ታሪካዊ የፈጠራ ሥራ ነው፡፡ በየምዕራፎቹ ዘመን የማይሽራቸውና የሰውን ልጅ የአኗኗር ስልትና ሥነ ልቡናዊ ሕይወት፤ የዓለምን ሁኔታ በፍልስፍና አስተሳሰብ የሚቃኙ ዘጠኝ ቅኔዎች ተተንትነው ቀርበዋል፡፡ ከቅኔዎቹ ውስጥ የምዕራፍ አንድ መግቢያ የሆነው የመምህር ኤርምያስ የመወድስ ርእስ «አልቦ ዘመድ» የሚለው አንደኛው ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚዳስሰው የመጽሐፉን አጠቃላይ መልእክት ሳይሆን አልቦ ዘመድ የሚለውን የመወድስ ቅኔ መነሻና ይዘት ይሆናል፡፡
አባቶቻችን ስለ ጊዜና ስለ ባለጊዜ ድርጊት ከሚናገሯቸው አባባሎች ውስጥ «ጊዜ ያነሣል ጊዜ ይጥላል፤ ሁሉም ያልፋል፤ እስኪያልፍ ግን ያለፋል፤ የቀን ጀግና እንጂ የሰው ጀግና የለውም፤ አትዋል ይዋሉብህ አትምከር ይምከሩ፤ በቆፈሩት ጉድጓድ ሳይገቡም አይቀሩ፤ ጊዜ የሰጠው ቅል ደንጋይ ይሠብራል፤»የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለጠቢቡ ሰሎሞንም «ለሁሉም ጊዜ አለው » የምትል አባባል አለችው፡፡
የሰው ልጅ በዘመኑ ኅሊናው በፈቀደለት መጠን ለሀገርም ለወገንም የሚጠቅም መልካም ነገር አድርጎ ቢያልፍ በትውልድ ዘንድ ለዘለዓለም በአርአያነቱ ሲወደስና ሲጠቀስ፤ ወገኑም በሥራው ሲኮራ ይኖራል፡፡ ትላንት የማይደፈሩና ሥልጣናቸውም የማይገሠሥ ይመስሉ የነበሩ ክፉ አድራጊዎች በሕይወት እያሉና ከገጸ ምድር ሲጠፉም በእኩይ ድርጊታቸው ሲወቀሱና ሀገርንም ሲያሳፍሩ ይኖራሉ፡፡ ይህንን የምለው ዘመን ለትልቁም ለትንሹም የራስዋን ፍርድ ለመስጠት እንደማትቦዝን በጥቂቱ ለማሳየት ነው፡ ፡ የሰው ልጅ በሠራው ግፍ ከሚዛን ላይ ወጥቶ ዋጋ ይከፍልበታል፡፡ ባልሠራው ነገርም በግፍ ሰንሰለት ተይዞ በደል ቢፈጸምበት የበቀል አምላክ መልሱን ሳይውልና ሳያድር ይሰጠዋል፡፡
እናም ከክብር ውርደት በገጠማቸው ጊዜ « አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ—( የሰው ልጅ በተዋረደ ጊዜ ዘመድ የለውም ) ብለው በራሳቸው ላይ የዛሬ ሦስት መቶ ዓመት ገደማ መወድስ ቅኔ የተቀኙት ዘመን አንሦቶ የጣላቸው የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ መምህር ኤርምያስ የተባሉት ናቸው፡፡ «አልቦ ዘመድ» በተሰኘውና በዚህ የመወድስ ቅኔ ርእስ መጽሐፋቸውን የሰየሙት አቶ ብርሃኑ ድንቄ እንደጠቀሱት እኒህ ሊቅ በጎንደር ዘመነ መንግሥት ዘፋኙ ዳዊት እየተባሉ ይጠሩ በነበሩት በዓፄ ዳዊት ጊዜ ፍትሐ ነገሥት አውጭና ተርጓሚ፤ የቤተ መንግሥቱም ባለሟል ነበሩ፡፡ ሊቁ በንጉሡ የዙፋን ችሎት ለፍርድ በቀረቡ እሥረኞች ፊት ትልቁን የሕግ መጽሐፍ በወርቅና በብር በተጌጠ አትሮንስ ላይ ዘርግተው ጥዑም በሆነ አንደበታቸው በግእዝ ሲያስኬዱ ከቆዩ በኋላ እንደገና ወደ አማርኛ በመተርጎም«አንተ በሠራኸው ሥራ እድሜ ልክህን ትታሠራለህ፤ አንተ ደግሞ ይሙት በቃ ተፈርዶብሃል (ይመውት ይልሃል)—እያሉ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ የመጨረሻውን የቅጣት ፍርድ የሚወስኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን ስለነበሩ እርሳቸውን የማይፈራና የማያከብር፤ ሲያያቸውም የማይርበደበድ ሰው አልነበረም፡፡
አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ
ሊቁ ለዜጎቹ የተጣመመ ፍርድ ይስጡ አይስጡ ባይታወቅም ከዕለታት በአንዱ ከዓፄ ዳዊት ጋር ይጣላሉ፡፡ የጠቡ መነሻም በዘመኑ በአቡነ ኤዎስጣቴዎስና በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳማት መምህራን መካከል በሃይማኖት አስተምህሮ (ዶክትሪን)የተነሣ የከረረ ጠብ ተጣልተው ይጨቃጨቁ ስለነበር ነው፡፡ በመሆኑም ስለ ምሥጢረ ሥጋዌና ስለ ትስብእተ መንፈስ ቅዱስ የተነሣውን ጠብ ለማብረድ ጉዳዩ ለችሎት ሲቀርብ ዓፄ ዳዊት የኤዎስጣቴዎሳውያን እምነት የተሻለ ስለመሰላቸው ( ለሥዕል፤ ለመስቀል መስገድ አይገባም የሚሉ) እነርሱን ደገፉ፡፡ የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ መምህር ኤርምያስ ግን ከንጉሡ ሐሳብ በመለየት የኤዎስጣቴዎሳውያን እምነት ከእምነታቸው ጋር የማይሔድ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረው ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት እምነትና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም መምህራን ጋር ተሰለፉ፡፡ በዚህም ተወግዘውና የንጉሡ ቁጣ ደርሶባቸው እሥር ቤት እንዲገቡ ተደረገ፡፡ በዚያ ዘመን በእምነትና በአስተሳሰብ ከመሪው የተለየ ሰው ታሥሮ መከራውን ይበላ ነበር ማለት ነው፡፡ ዓፄ ዳዊትም ሊቁን እሥር ቤት አስገብተው እንዲማቅቁ ያደረጓቸው የሃይማኖቱ ዶክትሪን አሳስቧቸው ሳይሆን በፖለቲካውና በአገዛዛቸው ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ተጽእኖ በመፍራት መሆኑን ደራሲው አምባሳደር ብርሃኑ አስምረውበታል፡፡
መምህር ኤርምያስ የዓፄ ዳዊት ባለሟል በነበሩበት ጊዜ አያሌ ዘመዶችና ወዳጆች ያጅቧቸውና ያከብሯቸው ነበር፡፡ እሥር ቤት በገቡበት ወቅት ግን እንደ ኢትዮጵያውያን ልማድ «እግዚአብሔር ያስፈታዎ» ብሎ የሚጠ ይቃቸው ከመጥፋቱ ባሻገር እንዲያውም ያልሠሩትን ወንጀል እየጨመረ፤ እየፈጠረና እያሳበቀ የሚከስሳቸው ሰው ስለበዛ የዚያኑ ያህል የንጉሡ ቁጣ ተባባሰና ጨከኑባቸው፡፡ ንጉሡን በመፍራትም የሚጠይቃቸው ሰው ጠፋ፡፡ ይህም ሁኔታ ከተከሰሱበት ክስ በላይ የመምህር ኤርምያስን ስሜት በእጅጉ ጎድቶት ነበር ይባላል፡፡ ሊቁ በቅኔያቸው ያንጸባረቁትም ይህንኑ ነው፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሡ ዓፄ ዳዊት በድንገት ይሞታሉ፡፡ የሞቱትም መርዝ በልተው ነው፡፡
ይህንን ያደረጉባቸውም የደብረ ሊባኖስ ደብተሮች ናቸው ተብሎ ተወራ፡፡ ከዓፄ ዳዊት ቀጥሎ ዓፄ በካፋ ሲነግሡ የዘውዳቸውን ክብረ በዓል ምክንያት አድርገው አሥረኞች ሁሉ እንዲፈቱ የምሕረት አዋጅ ሲያሳውጁ በአጋጣሚው ተጠቅመው መምህር ኤርምያስም ከእሥር ቤት ወጡ፡ ፡ ያልተጠበቀ ድንገተኛ እድል ነበር፡፡ የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ መምህር ኤርምያስ የተፈቱበት ዕለት እሑድ፤ ቀኑ መስከረም ዐራት፤ በዓሉ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ነበር፡ ፡ካህናቱ ጎንደር በዓታ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማኅሌት ቆመው የተለመደውን ቃለ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ከእስር ቤት የወጡት ሊቅ ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ ወደ በዓታ ገብተው ከካህናቱ ጋር እንደተቀላቀሉ በክብር የመወድስ ቅኔ አደራረስ ሰዓት ደረሰና ቅኔውን ለእርሳቸው ሰጡዋቸው፡፡
መወድስ
አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ ወይከውን ባዕደ ጊዜ ተዋርዶ ዘመድ፡፡
እመሰ ይትሌዓል በንብረተ ሥጋ ማዕድ፤ ጥቀ ዘመዱ ወጥቀ ነገድ፡፡
ባዕድ ይዛመድ፡፡
እምኀበ አልቦ ነገድ ወእምኀበ አልቦ ትውልድ፡፡
ሶበሂ ተሰአልዎ ለሓዋርያ አይሁድ፡፡ ኀደገ ፈጣሪሁ ወቆመ ምስለ ባዕድ፡፡
ዘመድሰ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ፡፡
ኢተፈልጠ ምስለ እሙ እስከነ መቃብር ይወርድ፡፡
የመወድሱ ትርጉም ፡-የሰው ልጅ በተዋረደ ጊዜ ዘመድ አይኖረውም፡፡ ሰው በተዋረደ ጊዜ ምንም እንኳ ኃላፊና ጠፊ በሆነው የሥጋ ሀብቱና ማዕዱም ከፍ ያለ ቢሆን ዘመድ ሳይቀር( በችግር ጊዜ) ባዕድ ይሆናል፡፡ ዘመድም ነገድም ቢሆን ዘመድ፤ ትውልድ ሳይል ከባዕድ ጋር ይዛመዳል፡፡ አይሁድ ሐዋርያውን (ጴጥሮስን) በለመኑት( ባስጨነቁት ጊዜ) ፈጣሪውን ትቶ ከባዕድ ጋር ተሰልፏል፡፡ ይልቅስ እውነተኛ ዘመድ የሚባለው ወልደ ነጎድጓድ ዮሐንስ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ መቃብር እስከሚወርድበት ጊዜ ከእናቱ ( ከቅድስት ድንግል ማርያም ) አልተለየምና ነው፡፡
የመወድሱ ምሥጢር፡-ሰው ሲዋረድና በመከራ ላይ ሲወድቅ ዘመድ አዝማድ ሁሉ እንደሚርቀውና ወዳጅ ሁሉ እንደሚክደው ያመለክታል፡፡ሊቁ መምህር ኤርምያስ በታሠሩበት ዘመን ከደረሰባቸው ታሪክ በመነሣትና በመጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 ቁጥር 75 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ጴጥሮስን «ዛሬ ገና ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ» ያለውን በመጥቀስ የተቀኙት ሰው ሁሉ ስለካዳቸው ነው፡፡
ባለቅኔው በዚህ መወድስ «ዘመድ»የሚለውን ቃል ለአምስት፤ «ባዕድ» የሚለውን ደግሞ ለሦስት ጊዜ ተጠቅመውበታል፡፡ ምክንያቱም በተዋረዱበትና በታሠሩበት ወቅት የዘመድን አለኝታነትና ረዳትነት ስለአላገኙ ነው፡፡ እውነተኛ ዘመድ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ በመስቀሉ ሥር ቆሞ ሲያለቅስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ ነው ብለው ሊቁ አመሥጥረዋል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ«እነኋት እናትህ »ብሎ የሰጠውን አደራ በመቀበል እስከሞት ድረስ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያም ታማኝ ሆኖ በመኖሩ ነው፡፡
እናም አምባሳደር ብርሃኑ እንደሚሉትና ከቅኔውም ምጣኔ ለመረዳት እንደሚቻለው በበዓታ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይበል ማለፊያ ነው ተብሎ የተደነቀው መወድስ ስለሰው ልጅ ተፈጥሮና ጠባይ የሚያሳይና የሚያስተምር ፤ ጥልቅ የፍልስፍና ስልትን የያዘ ከመሆኑ ባሻገር ደራሲው በራሳቸው ሕይወት ላይ የደረሰውን ድርጊት መነሻ አድርገው ስለተቀኙት ሁሉንም አድማጭ አሳዝኖትና አስደንቆት ነበር፡፡ በጎንደር በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅኔ ማኅሌት ውስጥ የተሰማው ቅኔም እዚያው በዚያው ብቻ ተደንቆ አልቀረም፡፡ ይልቁንም ቃላዊ በሆነ አውሎ ነፋስ በፍጥነት እስከ ጎጃም፤ ወሎ፤ ሸዋና ትግሬ እየተዛመተ ለመላው የኢትዮጵያ ቅኔ ሊቃውንት ተዳርሶና በየልባቸው ጽላት ተቀርጾ ሲነገር ኖሯል፡ ፡አሁን ደግሞ በጽሑፍ መልክ ተሰንዶ እየተሰራጨ ለዚህ ትውልድ ደርሷል፡፡
ደራሲ ብርሃኑ ድንቄ እንደሚያስታውሱት ጠለቅ ያለ የሳይኮሎጂና የፍልስፍናን ትምህርት የያዘው ይህ መወድስ(አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ) በብዙ ቅኔ ቤቶች የሚማሩ ጀማሪ ተማሪዎች ከዜማው ጋር በቃላቸው እንዲይዙት ይደረጉ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት የኢትዮጵያ ቅኔ በውበቱ፤በድምጸቱ፤ በምጣኔው፤ በረቀቀ ምሥጢሩ ፤ በዜማ ልኩ፤ በሰምና ወርቅ መንገዱ— የምዕራባውያን ሥልጣኔ ምንጭ ከሆኑት ከጥንታውያኑ ከግሪኮችና ከሮማውያን ቅኔና ፍልስፍና ይልቅ የመጠቀ፤ እነርሱም ተመራምረውና አጥንተው ገና ያልደረሱበት ጥበብ መሆኑን አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡ በአልቦ ዘመድ ውስጥ ሌሎች ቅኔዎች የያዙት ምሥጢር እንዲሁ ስለዓለምና ስለየሰው ልጅ ጠባይ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ለአብነትም የትግሬውን መስፍን የራስ ወልደ ገብርኤልን ሥላሴ ቅኔ(አልቦ ዘመድ ገጽ 6) እንደሚከተለው አቅርቤ አሳርጋለሁ፡፡
ሥላሴ
ዓለም እስከ ጊዜሃ በሐብለ ዝንጋዔ ትስኅበነ፤ወታወርደነ ታኅተ ኀበ ዘቀዳሚ መርገም፡፡
ለዘተወለድነ በሥጋ ወደም፡፡ ወለአእመራሰ ጠቢብ ለባዊ ለኅልፈተ ዛቲ ዓለም፡፡
ፍዳ ወይን ይሥተይ ማየ ዝናም፡፡ወህየንተ ልብስ ይትከደን ቆጽለ አእዋም፡፡
እስመ ዛቲ ጽላሎት ወሕልም፡፡
ትርጉም፡-ዓለም እስከጊዜው ድረስ በዝንጋታ ገመድ ትስበናለች፡፡ ሰው ሆይ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ እንደተባለው በእርግማናችን መሠረት ዓለም በሥጋና በደም የተወለድነውን ሁሉ ወደ መቃብር ታወርደናለች፡፡ የዚህችን ዓለም ከንቱነት የሚያውቅ አስተዋይና ጥበበኛ ሰው እንደ ዝናም የመከራና የፍዳ ወይንን ይጠጣ፡፡ በልብስ ፋንታም የዛፍ ቅጠልን ይልበስ፡፡ዓለም እንደ ጥላ ታልፋለችና፡፡
ምሥጢር፡- ይህች ዓለም ኃላፊና ጠፊ ስለሆነች እየተዘናጋን ክፉ ሥራ አንሥራ፡፡ ቋሚና ዘለዓለማዊ አይደለንምና፤ ለልብሳችን፤ ለምግባችን አንጨነቅ፡፡ መጋቤ ፍጥረታት የሆነው ፈጣሪ ለእኛ ያስባልና የሚል ነው፡፡
ይህ ቅኔ አገራችን አሁን ለአለችበት ነባራዊ ሁኔታም የሚያስተላልፈው መልእክት ከፍተኛ ነው፡፡ በስግብግብነት የስሜት ገመድ ተተብትቦ፤ በአልበቃኝም ባይነት ተወራጭቶ፤ ሕዝብን በእብሪት ለጥፋት አነሣሥቶ፤ በዘር፤ በሥልጣን፤ በመንደር፤ በክልል፤ በፖለቲካ እምነት፤ በጥቅም ሳቢያ ከፋፍሎ እርስ በርሱ ለሚያፋጀው፤ የገዛ ወንድሙን ሥጋ ይበላውና ደሙንም ይጠጣው ይመስል አካሉን፤ ወንድሙን እንደ ቃኤል ለመግደል፤ ለማሳደድ፤ ለማሠቃየት፤ ሌት ተቀን በመባዘን ላይ ለሚገኘው አንዳንድ ኢትዮጵያዊ የጥፋት ኃይል በአስተማሪነቱ በምሳሌነት የሚቀርብ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ባለቅኔው ራስ ወልደ ገብርኤል እምነት ይህች ዓለም ኃላፊና ጠፊ ስለሆነች የጥፋት ኃይል ሁሉ ከፈጣሪ ትእዛዝ እየወጣና በሰይጣን ፈረስ እየጋለበ፤ ሕዝብን በቋንቋና በዘር እየከፋፈለ፤ እግዚአብሔር ፍጥረቱ ሁሉ እንዲኖርባት የሠራትን መሬት ልክ ራሱ ጠፍጥፎ እንደሠራት ሁሉ የኔናት እያለ ድንበር እየከለለና እየገፋ፤ ክፉ ሥራ ለመሥራትና ደም ለማፍሰስ የሚሽቀዳደም የዓለምን ከንቱነት ቢረዳ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ነቢዩ ዳዊት «ወይፈድዮ ለኵሉ በከመ ምግባሩ »እንዳለው ለሁሉም እንደሥራው የሚፈርድ የሰማዩ ንጉሥ መኖሩን ክፉ አድራጊዎች፤ የእርኵስ መንፈስ ማደሪያዎች፤ ዘረኞችና የፖለቲካ ቁማርተኞች ሁሉ ቢረዱት መልካም ነው፡፡
በነገራችን ላይ የተምቤን ተወላጅ የሆኑትና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፓርላማ አባል የነበሩት ፊታውራሪ አበበ ሥዩም እንዳጫወቱኝ ባለቅኔው ራስ ወልደ ገብርኤል አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳልፉ የነበሩት የሀገሪቱ ዋና ከተማ በነበረቺው ጎንደር ውስጥ ነው፡፡ እና ከዕለታት ባንዱ አንድ ባህታዊ «መደብ ላይ ትሞታለህና ተጠንቀቅ» ይላቸዋል፡፡ ብልጡ ባለቅኔም መደብ ላይ ተኝተው ላለመሞት በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ የሚተኙበትን የጠፍር አልጋ (በጎንደር ዘመነ መንግሥት የብረት አልጋ ላይኖር ይችላል) በአሽከሮቻቸው እያሸከሙ ሄደው በአልጋቸው ላይ ይተኛሉ፡፡
በዚህ ዓይነት መደብ ወደተባለ ቦታ ወይም ግዛታቸው የሚተኙበትን አልጋ አሸክመው እንደሄዱ በመንገድ ላይ ማለፊያ የበግ ሙክት ያያሉ፡፡ ከበቅሎ ላይ ወርደውም በጉን አገላብጠው ካዩት በኋላ ገዝተው ወደ ማረፊያ ቦታቸው በመውሰድ ያሳርዱታል፡፡ በጉ ተጠባብሶ ራት ተበልቶ አልጋቸው ላይ እንደተኙ ጣታቸውን የሚያቃጥልና የሚለበልብ ነገር ይሰማቸዋል፡፡ ቀስ እያለም እያበጠ ሰውነታቸውን ይወራቸዋል፡፡ ለካ በጉን በእጃቸው እያገላበጡ ላቱን፤ ሽንጡን ሲያዩ ልብ ያላሉትና በበጉ ጸጉር ውስጥ የመሸገ መርዘኛ እሾህ ጣታቸውን ወግቷቸዋል ኖሯል፡፡ በዚህም ሰበብ ባህታዊው እንደነገራቸው መደብ በተባለው ቦታ ይሞታሉ፡፡ እናም ዓለም ከንቱ ስለሆነችና ሞትም የማይቀር በመሆኑ ሕዝብ የሚወድደውንና ለትውልድ የሚጠቅመውን መልካም ነገር ብቻ በአንድነት፤ በፍቅርና በሰላም እየሠራን ለመኖር እንሽቀዳደም፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)