«የተቆለፈበት ቁልፍ» ዛሬ ያወያያል
ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመጻሕፍት ንባብ እና ውይይት ዝግጅት ክፍል ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ዛሬ እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ሰዓት ጀምሮ «የተቆ ለፈበት ቁልፍ» በተሰኘው በዶክተር ምህረት ደበበ መጽሐፍ ላይ የስነ ልቦና ሂስ ይቀርባል፤ ውይይትም ይካሄዳል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ውይይት በሚካሄድበት ወቅት መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት እንግዳወርቅ እንድሪያስ – በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በ «ኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ » የ3ኛ ዲግሪ (PhD) ተማሪ እና በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ እና የፎክሎር መምህር ናቸው። ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ በሚያካሂደው በዚህ ውይይት ላይ እንድትታደሙ በአክብሮት ጋብዟል።
የሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ቀን ነገ ይከበራል
ከተመሠረተ አሥራ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረው ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ነገ መጋቢት 2 ቀን 2011 ብሔራዊ ቴአትር ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት ጀምሮ ቀኔን አከብራለሁ ብሏል።
16ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ በሚካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የመንግሥት ባለስልጣናት ይታደማሉ። የሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ወጣቶችም ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። በዚህም መሰረት ሙዚቃ፣ ባህላዊ ውዝዋዜ፣ ዘመናዊ ዳንስ፣ ቴአትር፣ ግጥምና ወግ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ዝግጅቶች የክዋኔው አካላት ናቸው ተብሏል። ማኅበሩም የጥበብ አፍቃሪያን ሁሉ እንዲታደሙ ጥሪውን አቅርቧል።
«ፍልስፍና -3» መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ያወያያል
በመምህርና ደራሲ ብሩህ ዓለምነህ የተዘ ጋጀው «ፍልስፍና – መጽሐፍ» ላይ የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 2011ዓ.ም በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ያወያያል።
ውይይቱ በመጽሐፉ ሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚከናወን ሲሆን፤ «ቅኔና ፍልስፍና» በሚለው ሃሳብ ላይ መጋቢ ብሉይ አእመረ አሸብር፣« ሃይማኖትና ዘመናዊነት» ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር አቶ ፋሲል መራዊ እንዲሁም «ሰሞነ ህማማትና የኢትዮጵያ ሙዚቃ» በሚል ደግሞ በመሪጌታ ጽጌ መዝገቡ ዳሰሳ ይቀርባል ተብሏል።
መምህርና ደራሲ ብሩህ ዓለምነህ በአሁኑ ወቅት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም «ፍልስፍና -1» «ፍልስፍና -2» እና «የኢትዮጵያ ፍልስፍና» የተባሉ መጻሕፍትን ለአንባብያን ማድረሱ ይታወሳል።
መጻሕፍት በገበያ ላይ
ትናንት የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እናበእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ስድስት መጻሕፍት ተመርቀው የመጻሕፍት ገበያውን ተቀላቅለዋል። የመጻሕፍቶቹ አዘጋጅ ለማ ደገፋ ሲሆኑ፤ ደራሲው ከዚህ ቀደም በቁጥር አስር የሚደርሱ መጻሕፍትን በተለያዩ ቋንቋዎች አዘጋጅተው ለአንባቢ ማደረሳቸው ይታወሳል።
«መጻሕፍት ከታሪካችን ጋር» የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ዛሬ ይጠናቀቃል
ታላቁን የዓድዋ ድል እና ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ «መጻሕፍት ከታሪካችን ጋር» በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ዛሬ እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም አመሻሽ ይጠናቀቃል።
መገናኛ አደባባይ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፊት ለፊት ሲካሄድ በቆየው በዚህ የመጻ ሕፍት ሽያጭና አውደ ርዕይ በርካቶች መታ ደማቸውንም ታዝበናል። በተያያዘ ዜና፤ ወርሃዊ የሕጻናት ምንባብና መዝናኛ ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በአስር የመዝናኛ ፓርክ (ቦሌ ረዋንዳ ኤምባሲ መታጠፊያ) ረፋድ ከ4:00 እስከ 5:00 ሰዓት ይካሄዳል።
በዚህ መሰናዶ የተለያዩ የተሰጥኦ ውድ ድሮች ከሽልማት ጋር ይኖራሉ የተባለ ሲሆን፤ ዶክተር አሉላ ፓንክረሰት፣ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገ/ማርያም፣ መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ደራሲት የዝና ወርቁ፣ አርቲስት ስዩም ተፈራ እና አር ቲስት ማህተመ ኃይሌ ይገኛሉ፤ የልጅነት ትዝታቸውንና ገጠመኞቻቸውን ያወጋሉ ተብሏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011