በአሥራ ስድስት ሉክ ቆርቆሮ በተሰራ ቤት ውስጥ ሰብሰብ ብለው ተቀምጠዋል፡፡በጭቃ የተሰራችው ባለአንድ ክፍል ቤት በውስጧ የተለያዩ መረጃዎችን ይዛለች፡፡ በክፍሏ ውስጥ ያገኘናቸው ሴቶች በዕድሜ ይለያዩ እንጂ አንድ አይነት ዓላማን አንግበው በጋራ ይወያያሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ በበቀቱ ሎሜ ገበሬ ማህበር ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር አባላት የሆኑት እነዚህ ሴቶች ዋና ዓላማቸው ከሚያገኙት ላይ በመቆጠብ ኑሯቸውን ማሻሻል ነው፡፡ማህበሩ የተመሰረተው በ1996 ዓ.ም ሲሆን በአሁኑ ወቅት 89 አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ ሴቶቹ ቆጥበው ባገኙት ገንዘብ ከብት በማድለብ፣ የጉልት ንግድ በመስራት፣ ቤት በማከራየት እንዲሁም በእርሻና ዶሮ እርባታ በመሰማራት ኖሯቸውን በመምራት ላይ ይገ ኛሉ፡፡ ወይዘሮ ሎሚ ንጋቱ የማህበሩ ገንዘብ ያዥ ሲሆኑ፣ የማህበሩ አባላት የቆጠቡትን ገንዘብ በየወሩ ወደዩኒየኑ ያስገባሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት 91 አባላት መሆናቸውን ጠቅሰው፤እርሳቸውም ማህበሩን የተቀላ ቀሉት በ2008 ዓ.ም እንደሆነ ነግረውናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብድር ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ናቸው።
‹‹ከዚህ በፊትም በግብርና ሥራ ነበር የምተዳ ደረው፡፡ አሁን ላይ ቁጠባ በመጀመሬ ተለውጫለሁ፡ ፡ መሬት በመኮናተር ሽንኩርት ዘርቻለሁ፡፡ ከተማ ውስጥ ለመኖሪያ ቤቴ መሬት ገዝቼ ቤት በመስራት ላይ ነኝ›› ይላሉ። ሌሎችም በተመሳሳይ ሰርተው ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው ይመክራሉ።እነርሱ በቆጠቡት እንጂ ከመንግሥት ይህ ነው የሚባል ድጋፍ አለማግኘታቸውን ጠቁ መው፤ ድጋፍ ለማግኘት ሲባል መቀመጥ ኑሮን እንደማያሻሽል አመልክተዋል፡፡
የዚሁ ማህበር አባል የሆኑት የበቀቱ ሎሜ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ እልፍነሽ ሆርዶፋ በበኩላቸው፤ ‹‹የምንተዳደረው በእርሻ ነው፡፡ ቁጠባውን በምጀም ርበት ጊዜ የሰው ብዛት ወደ 35 ያህል የሚጠጋ ሲሆን፣ በወቅቱም በየወሩ የምንቆጥበው ሁለት ሁለት ብር ነበር፤ በሂደት ግን ቁጠባውን ወደ 5 ብር አሳደግን፡ ፡ እየቆጠብኩ በሄድኩ ቁጥር ጥቅሙ እያደር እያጓጓኝ መሄድ ጀመረ›› ይላሉ፡፡
ወይዘሮዋ፣እስከ አራት ሺ ድረስ ይበደራሉ፡ ፡ ዋናው ነገር ግን ለሚወስዱት ብድር ምን እቅድ ተይዞ ነው የሚለው መታየት ያለበት በመሆኑ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው ቦለቄና ሽንኩርት ያመርታሉ፡፡‹‹ከቤተሰቤ ጋር በተለይ ከትዳር አጋሬ ጋር ተመካክረን ነው የምን ሰራው፤ሰባት ልጆች አሉኝ፡፡ አራቱ አግብተዋል፡፡ ሦስቱ አጠገቤ ናቸው፡፡›› ይላሉ፡፡
‹አሁን ብድር መውሰድ የምፈልገው ከብት ገዝቼ ለማደለብ ነው፡፡›› የሚሉት ወይዘሮ እልፍነሽ፣ ሊያመርቱበት ያቀዱት መሬት ደግሞ ማዳበሪያና ሌሎች ምርጥ ዘር ስለሚፈልግ ለዛም ገንዘቡን እንደሚያውሉት ያስረዳሉ፡፡
ሌላዋ የማህበሩ አባል ወይዘሮ አሰለፈች መሸሻ፣ማህበሩ በ1998 ዓ.ም በተጀመረበት ወቅት የመጀመሪያዋ መስራች ነበሩ። ማህበሩንም ለአምስት ዓመት በሰብሳቢነት መርተዋል፡፡በዚያን ወቅት ደግሞ መሰብሰቢያም መወያያም ትሆናለች በሚል ባለአንድ ክፍል ቢሮ መስራት በመፈለጋቸው ወደ ቀበሌያቸው ለድጋፍ የሚመጡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በመጠየቅ በወቅቱም የነበሩት አባላት የጭቃ ብሎኬቱን ሰርተው በማቅረብ ድጋፍ አድራጊዎቹ ቆርቆሮ፣እንጨት፣በርና መስኮቱን ረድተዋቸው ሰርተዋል፡፡አሁን የውይይት ክፍላቸው ሆኗል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን የማህበሩ አባላት እያንዳንዳቸው እስከ ሥራ ማስኬጃ 55 ብር በመቆጠብ ላይ ናቸው፡፡ ሲበደሩ ግማሹ መሬት የሌለው በመሆኑ መሬቱን ይኮናተርበታል፡፡ በዚያ ላይ ጤፍ፣ ሽንኩርት ምርጥ ዘር ያመርታል፡፡ ከብት ገዝቶ ያደል ባል፡፡ መኖሪያ ቤት ያልሰራም ይሰራል፡፡
‹‹በመቆጠቤ ብዙ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ከብት የለኝም ነበር፡፡ በተበደርኩት 2 ሺ 500 ብር ጊደር ገዛሁ፡፡ ያቺ ጊደር በጊዜ ሂደት የሦስት ወይፈንና የሁለት ጊደር ባለቤት አደረገችኝ፡፡ በመሆኑም በአይቡ፣ በቅቤው፣ በእርጎው ሁሉ ተጠቃሚ መሆን ችያለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ በመንግሥት በኩል የተለየ የሚባል የስልጠና ድጋፍ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
‹‹ሁለት ሴትና አራት ወንድ ልጆች አሉኝ፤ እነሱን አሳድጌ ለወግ ማዕረግ አብቅቻለሁ፡፡ በመቆጠቤ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ከእኛ በማየት የአካባቢው ሴት ወጣቶች እንዲጠቀሙ እመክራለሁ፡፡ ወደፊት የተሻለ መኖሪያ መስራት እቅድ ያለኝ ሲሆን፣ እሱንም ጀምሬያለሁ፡፡ መቆጠብ ይለውጣል፡፡›› ሲሉም ነው የተና ገሩት፡፡
የአንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ፀሐይ ኃይሉ ማህበሩ በ1998 ዓ.ም ሲጀመር ጀምሮ እንዳሉበት ይናገራሉ፡፡ በመቆጠባቸውም መሬት በመከራየት የተለያየ ምርት ማምረት እንደቻሉ ያመለክታሉ፡፡ እህል ከማምረት ጎን ለጎንም ንግድ በመነገድ ህይወታቸውን የሰመረ እንዲሆን በማድረግ ላይ እንዳሉም ያስረዳሉ፡፡
‹‹ጤፍ፣ ቦለቄ ሽንኩርት አመርታለሁ፡፡ ከማህበሩ እንደ ቁጠባዬ መጠን እበደራለሁ፡፡ 7ሺ660 ብር አምና ተበድሬ ጤፍና ቦለቄ ዘርቼያለሁ፡፡ ካገኘሁት ትርፍ ደግሞ ብድሬን በወቅቱ መልሻለሁ፡፡ ወደፊት ደግሞ ለመበደር አቅጃለሁ፡፡ በምበደረው ገንዘብ የወተት ላም ለመግዛት ነው እቅዴ፡፡›› ብለዋል፡፡
የምስራቅ ሸዋ ቦሰት ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ የሴቶች አደረጃጀት ወይዘሮ ዛሊካ አደም ቢሮው ትልቁ ዓላማው ግንዛቤ መስጠት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሴቶቹን በመጀመሪያ ማነቃቃት ከዚያም ማደራጀት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ ‹‹ጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ማህበራት ማደራጃ የሚባል አማራጭ አለና ከሁለቱ የትኛው ላይ መደራጀት ቢችሉ ይጠቅማቸዋል የሚለውን ከግንዛቤ አስገብተን ነው የምናደራጃቸው፡፡›› ሲሉ ጠቅሰዋል፡ ፡ በወረዳው 47 ማህበራት አሉ፡፡ ከ47ቱም ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ደህና ነው የሚባል ቢሆንም 50 በመቶ ላይ ግን አልደረሰም፡፡ በወረዳው ያለው ቀበሌ 42 ነው፡፡ከእነዚህ ውስጥ 33 የገጠር ቀበሌዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ገጠር ቀበሌዎች ላይ ቢሮው በበለጠ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በእነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈለገውን ያህል ባይሆንም ሴቷ ተደራጅታና የቁጠባን ባህል አዳብራ ህይወቷን በመለወጥ ላይ ትገኛለች፡፡ በየቀበሌው ቢያንስ እስከ 50 ሴት በቁጠባና ብድር ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንዳሉ ወይዘሮ ዛሊካ አብራርተዋል፡፡ ‹‹በወረዳው ከ25 እስከ 35 ሺ የሚሆኑ ሴቶች ይኖራሉ ተብሎ ይገመ ታል፡፡ እነዚህ ሴቶች ግን ተደራጅተዋል፣ በቅተዋል፤ ሰልጥነዋል፤ ቢባል የሚቀር ነገር አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሴቷ ከትዳር አጋሯ ጥገኝነት በመላቀቅ ላይ ናት፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷንም በማረጋገጥ ላይ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም ቁርስ በልቶ ራት መድገም የማይችል በአሁኑ ወቅት በቀን ሶስቴ መብላት ጀምሯል፡፡›› ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ በበቀቱ ሎሜ ገበሬ ማህበር ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር የተመሰረተው በ1996 ዓ.ም ነው፡፡ ቁጠባቸው በጣም በማደግ ላይ ሲሆን አንድ ሚሊዮን 23 ሺ በብር ለመበደር ዝግጁ ናቸው፡፡ ከመደራጀታቸው በፊት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ነበሩ፡፡አሁን ከቤት እመቤትነት ወጥተው የራሳቸውን ኢኮኖሚ ማመንጨት ላይ ደርሰ ዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
አስቴር ኤልያስ