በአገራችን የተጀመረው ለውጥ መሰረታዊ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎችን ባማከለ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በርግጥ ለውጡ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አዲስ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ላለፉት አስራ አንድ ወራት ስለለውጥ ያልሰማንበት ጊዜ አልነበረምና፡፡ ይሁንና የለውጡን ምንነትና ፋይዳ፣ ጥልቀትና ዝርዝር መሰረታዊ ጉዳዮች ከመሰረቱ ለመረዳት ጠለቅ ብሎ መመልከትና ማየትን ይጠይቃል፡፡
በእነዚህ የለውጥ ወቅቶች በጥልቀት ከተዳሰሱ ጉዳዮችም ውስጥ የፖለቲካው አውድ በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአገራችን የተንሰራፉትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጥሰቶች፣ የህግ የበላይነት መሸርሸር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሌብነትና የዴሞክራሲዊ ሥርዓት ግንባታ መጓተት ችግሮችን ለመፍታት የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችና የተካሄዱ የሪፎርም ሥራዎች ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ ዘርፉም ቢሆን የተወሰዱት እርምጃዎችና የተከናወኑት ተግባራት በርካታ ናቸው፡፡
በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ የሰላም እጦትና ያለመረጋጋት ችግሮችን ተከትሎ ተዳክሞ የቆየውን የኢኮኖሚ ዘርፍ ለማረጋጋትና ለማነቃቃት እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት፣ የጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር፣ በብሄራዊ ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የነበረውን ህገወጥነት ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎችና ማሻሻያዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን ለኢንቨስትመንት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ የሚጠበቁትን የሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻፀም በማሻሻል እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ በማፋጠን ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተወሰዱ እርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ትላልቅ የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ባለሀብቱ ለማዞር የተጀመሩት ሥራዎችም የዚሁ አካል ሆነዋል፡፡ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለሥራ ብቁ የሆኑትና ከፊሎቹም ወደ ሥራ የገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአገራችን ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግና ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡
ከዚህ አንጻር በ2025 አጠቃላይ ከ30 በላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባትና ወደ ሥራ በማስገባት የአገራችን ኢኮኖሚ 20 ከመቶ እንዲሁም ከወጪ ምርቶች 50 ከመቶ በኢንዱስትሪ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፤ ይህም ለዘመናት በኋላቀር የግብርና ዘዴ ሲዳክር የነበረውን የአገራችንን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገርና መካከለኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጎን ለጎን እድገቱን ሙሉ ለማድረግና ኢኮኖሚያችንን ወደፊት ለማራመድ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችም በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ከነዚህም ውስጥ በተለይ የወጪ ንግዱን ለማሳለጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው የሚታመንባቸው የባቡር መሰረተ ልማት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ ተጠናቆ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ የአዋሽ-ወልዲያና የመቀሌ-ወልዲያ-ሃራ ገበያ የባቡር መስመሮች ግንባታም በመገባደድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ተከማችተው የቆዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ ለመመለስ በሁሉም ዘርፎች እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ እየተሠራ ይገኛል፡፡
ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ህዝባችን ሰላምን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ርብርብ ሲያደርግ አይታይም፡፡ የተጀመሩት ተስፋ ሰጪ የልማት ቡቃያዎች ፍሬ አፍርተው የድህነት እና የኋላቀርነት ድርቅን አጥፍተው ሰላማችንን እንዲያለመልሙና መጠበቅ እንዲቻል ማድረግ ትልቁ የክፍል ሥራችን ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ምንም ያህል የልማት ሥራ ቢከናወን ሰላም እና መረጋጋት ከሌለ የዜሮ ድምር ውጤት መሆኑ አይቀሬ ነውና፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እዚህም እዚያም እየገነገኑ የመጡት የአክራሪ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎችና ለውጡ ተቀልብሷል በሚል ህዝብን በማደናገር ወዳልተገባ የእርስ በርስ መጠራጠር የሚወስዱ በሮች ከወዲሁ ሊዘጉ ይገባል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ የተነሳውን የባለቤትነት ጥያቄ ሌላ መልክ ለማስያዝ የሚደረጉ ጥረቶችም ሆኑ በአማራና ትግራይ ህዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚፈጠሩ አጀንዳዎች በእንጭጩ ሊቀጩ ይገባል፡፡ ትክክለኛ የህዝብ ጥያቄዎችንም መንግሥት ቆም ብሎ በጥልቀት በመመርመርና ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር ማድረስ አለበት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በድህነት ውስጥ የኖርን ህዝቦች ነን፡፡ ከዚህ በኋላ የሚከሰት ተጨማሪ ድህነት ደግሞ አጥፊያችን መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡
የእርስ በርስ ግጭትም ድህነትን ከማባባስና አገራችንን ከማውደም ሌላ ምንም አይነት ፋይዳ እንደማይኖረው ተረድተን ለሰላም ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ በቅርቡ በአንዳንድ የአፍሪካ እና የአረብ አገራት ከተከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶችም ትምህርት ወስደን ከግጭት መንስኤዎች በብዙ እጥፍ ልንርቅ ይገባል፡፡ ለልማት እንጂ ለጥፋት የምናውለው ጊዜም እንዳይኖረን ጥንቃቄ ልናደርግ ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011