ሴቶች እንዳለባቸው ድርብርብ የቤተሰብ ኃላፊነትና የስራ ጫና፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ካላቸው ተፈላጊነትና ተቀባይነት… አንፃር የተሰጣቸው ቦታ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ቀደም ሲል በነበሩት ሥርዓቶች ለሴቶች ይሰጥ የነበረው ክብር ዝቅተኛ በመሆኑም መማር የሚችሉበት፣ ሀብት የሚያፈሩበት፣ እኩል የሀብት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ አልነበራቸውም። በየዘመኑ ለሴቶች ይታሰብ የነበረው የትምህርት ዕድል አልነበረም።
በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግም አይደለም። ይልቁኑ በልጅነት መዳር፣ ልጅ ወልዶ ማሳደግ፣ የቤት ውስጥ ስራ እና ቤተሰብ መንከባከብ የመሳሰለው ነው። ለማጀት እንጂ ለአደባባይ የተመረጡ አልነበሩም። ይሄም በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል እንዳይሆን አድርጓል። በኢኮኖሚው ዘርፍም የወንዶች እጅ ተመልካች እንዲሆኑ፣ ሀብት የማፍራትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሆኖባቸው ዘመናትን አስቆጥረዋል። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይብዛም ይነስ መብቶቻቸው ተከብሮላቸው ፣ ጥቅማቸው ተጠብቆላቸው ወደ አደባባይ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። የትምህርት ዕድል መቋደስ ችለዋል፤ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተዋል።
የወንዶች ብቻ የነበሩ የኃላፊነት ደረጃዎችን ሳይቀር ተቀላቅለዋል። እንደአጠቃላይ አሁን ታሪክ እየተቀየረ በመሆኑ ለውጦች አሉ፡፡ በተለይም በአገራችን የተጀመረውን አዲሱን የለውጥ ጉዞ ተከትሎ የሴቶችን እኩልነት፣ ብቃት እና ችሎታን ያገናዘቡ ርምጃዎች ተወስደዋል። ሴቶች አይችሉትም (አይሞክሩትም) በሚባሉባቸው እንደ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስትር እና ሌሎችም ከዛም ከፍ ብሎ የአገራችን ፕሬዚዳንት በመሆን ጭምር ስራቸውን በብቃት በመስራት ሀገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ናቸው።
ይሄ አለምን ያስደመመ፣ ህዝብን ያስደነቀ፣ ሴቶችን ያኮራ የከፍተኛ ስልጣን ሹመቶች ለሴቶች የተሰጡት በችሮታ ሳይሆን፣ ስለሚገባቸው፣ ስለሚሰሩና መሆን ስላለበትም ጭምር ነው። እስከዛሬም ቢሆን ሴቶች ስለማይችሉ ሳይሆን ሴቶች « አይችሉም» በሚል የተሳሳተ የማህበረሰቡ ግንዛቤ ወይም የወንዶች አምባገነንነት ታክሎበት እውቀታቸው፣ ችሎታቸው ፣ ትምህርትና ልምዳቸው ታይቶ ሳይሆን ሴትነታቸው ብቻ በ«አይችሉም» ሚዛን ተመዝኖ ማህበረሰቡ ለሴቶች በሰጣቸው ቦታ ብቻ ተገድበው እንዲኖሩበመደረጋቸው ነው። ዛሬ ዛሬ ግን ሁኔታዎች እየተለወጡ ነው፡፡
ሴቶች «ደግሞ የሴት ፖለቲከኛ» ከሚል አስተሳሰብ ወጥተው ዛሬ በፖለቲካው ያላቸው ተሳትፎና ተሰሚነትም ጨምሯል። የቤት እመቤቶች ሳይቀሩ መብቶቻቸውን ጠያቂና አስከባሪ ሆነዋል። ለሌሎች መብቶች ጭምር ተሟጋችና ተከራካሪ በመሆን በተለያዩ መድረኮች ንቁ ተሳታፊ ሆነዋል። ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ራሳቸውን ለማላቀቅም እንደየችሎታቸውና ዝንባሌያቸው በተለያየ የሙያ ዘርፍ ተሰማርተው ለራሳቸው የገቢ ምንጭ በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማሳደግ ላይ ናቸው።
ይሄ ሁሉ የሚያሳየው ሴቶች ዕድሉን ካገኙ ከማንኛውም ወንድ ባልተናነሰ መልኩ እንደሚሰሩ፣ እንደሚያሰሩ፤ በሁሉም መስክ መምራት እንደሚችሉ ነው። እንዳውም ከወንዶችም በላይ ከትንሿ ጎጆ ጀምሮ በአቅም አመጣጥኖ፣ ሁሉንም እንደየአመሉ ችለውና አቻችለው በጥበብ የመምራት ልምድ አላቸው። አሁንም ዕድሉን ሲያገኙት በተግባር ያየነውና የተረገጋጠውም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በእውቀት፣ በጥበብና ብልሀት መስራትና መምራት እንደሚችሉ ነው።
ይሄው ዛሬ ቀን ቀንን ተክቶ፣ ዘመንም ዘምኖ ሴቶችን ለሹመት፣ ለሥልጣን የሚያይ ዓይን ተገለጠ። የከፍተኛ አመራር ቦታዎች በሴቶችም ተያዙ፤ ተያዙ ብቻ ሳይሆን በሴቶች ተመርተው ውጤትም እያመጡ ናቸው። ሴቶች አንገታቸውን ቀና አድርገው ስለመብቶቻችው መጠየቅና ስለጥቃቶቻቸው መናገር ችለዋል። ይሄ ያስደስታል፤ ጊዜንም፣ ታሪክንም ታሪክ ሰሪውንም በታሪክ ማህደር የታሪክ አሻራውን እንዲያኖር የሚያደርግ ነው። እውነታው ይሄ ቢሆንም ዛሬም ድረስ በህብረተሰቡ ውስጥ ነግሶ የኖረው የ«ሴት አትችልም» አመለካከት ገና ሰንኮፉ ተነቅሎ ስላልወጣ ሴቶችን በአመራርነት ቦታ ላይ ለምን ሆኑ የሚሉ ጉምጉምታዎች አሁንም ገና አልጸዱም። ሴት ስለሆነች የሚለው አመለካከት አሁንም ከስር መሰረቱ አልተመነገለም።
«ይሄ ለሴቶች ያስቸግራል» አይነት «አዛኝ መሳይ …» አስተያየቶች አልተወገዱም። ሴቶች ይችላሉ የሚለው አስተሳሰብ አሁንም ገና ወደ ውስጣችን አልዘለቀም ። በመሆኑም በዚህ ላይ ጠንክሮ መስራትን ይጠይቃል። መስራትም ይገባል። አሁንም ሴቶች መስራት እንደሚችሉ በተሰጣቸው የኃላፊነት ቦታ ላይ በተጨባጭ አሳይተዋል። እንደ እናት አዛኝ፣ እንደ መሪ ብልህና ቆራጥ ሆነው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛሉ። አሁን ታሪክ እየተቀየረ ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011