
አዲስ አበባ፦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመመከት ፈጠራና እውቀትን ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሳይበር ደህንነት ማህበር አስገነዘበ።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ብርሃኑ በየነ (ዶ/ር) 3ኛው የሳይበር ደህንነትና ዲጂታል ሽግግር ኮንፈረንስ ትናንት ሲከፈት እንደገለጹት፤ የሳይበር ጥቃትን መከላከል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። በተለይ በግለሰብ ደረጃ በግንዛቤ ጉድለት የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ፈጠራንና እውቀትን በየጊዜው ማሳደግ ይገባል።
የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች በቴሌኮም መሠረተ ልማት እድገት እያመጡ ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን የገለጹት ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ኢትዮጵያ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብና የሳይበር ደህንነት እውቀትን በማሳደግ ጥቃቱን ለመከላከል ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የማህበረሰቡን ንቃተ ሕሊና ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ ማህበሩ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኮንፈረንሱ ከሳይበር ደህንነት አንጻር ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት እንደሚዳስስ ገልጸው፤ በእዚህም የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ ትብብር ወሳኝ መሆኑን የባለድርሻ አካላት እንዲረዱ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
የሰው ኃይላችንን በማሳደግ ረገድ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብርና በሳይበር ደህንነት ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠናዎችን ማህበሩ ለመስጠት ማቀዱን ገልጸው፤ ከዓለም ሀገራት ጋር ትብብርና ቅንጅትን በማሳደግ፣ መረጃን ቀድሞ በማግኘት እና ለሌሎች በማጋራት እድሎችን ማስፋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢኖቬሺንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፎዚያ አሚን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥታት ለመተባበር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከግሉ ሴክተር መሪዎች፣ ከአካዳሚዎች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል መሠረተ ልማት ለፋይናንስ፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለኢነርጂ እና ለሁሉም ዘርፎች ተግባራት ስኬታማነት ወሳኝ ነው ያሉት ፎዚያ አሚን (ዶ/ር)፤የሳይበር ደህንነት በባሕሪው በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ትብብር ይጠይቃል። የኮንፈረንሱ ዓላማም ትብብርን ማጠናከር ነው ብለዋል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሲደረግ በሳይበር ደህንነት አስፈላጊነት ላይ በቂ ግንዛቤ ሊኖር እንደሚገባ ገልጸው፤ ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር በአንድ ሚኒስቴር፣ ኤጀንሲ እና ሀገር እውን መሆን ስለማይችል ሁሉም ሀገራት በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትብብር ለመሥራት ምቹ ሁኔታዎች መፍጠሩን የገለጹት ፎዚያ (ዶ/ር)፤የሳይበር ጥቃት ለመመከት ፈጠራና የሀገር በቀል እውቀት ማሳደግ ይገባል። ኮንፈረንሱም ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ትብብርን ለማጠናከር፣ ልምድ ለመለዋወጥና በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም