
አዲስ አበባ፡– ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ችግር ፈቺ ድጋፍ እንደሚያደረግ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ “በአክሪዲቴሽን የአነስተኛ እና የመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅም ይጎለብታል” የሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ የአክሪዲቴሽን ቀን ትናንት ሲከበር እንደገለጹት፤ አክሪዲቴሽን የሰው ልጅ የሕልውና ጉዳይ እና የዓለም የዘላቂ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ከሚገኝባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ ተቋማት የተሻለ የአሠራር ሥርዓትን እንዲከተሉ እና ሂደታቸውን ያለማቋረጥ እንዲገመግሙ፣ በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ እና በከፍተኛ የገበያ ፉክክር ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቆዩ፣ እንዲሁም ትውልድን የሚያሻግሩ ጠንካራ ተቋማት እንዲገነቡም ያስችላል ብለዋል ፡፡
በዓለም የአክሪዲቴሽን ቀን በየዓመቱ እንደሚከበር የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በሀገራችን በዓሉ ሲከበር ኢንተርፕራይዞች አዳዲስ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ለአካባቢያዊ ምጣኔ ሀብት ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ በመገንዘብ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የአክሪዲቴሽን ቀን በየዓመቱ የሚከበርበት ዋና ዓላማም ደህንነትን የሚያረጋግጡ የዓለም አቀፍ ገበያዎች ተደራሽነትን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ለማስገንዘብ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሀገር ዕድገት መሠረት በመሆናቸው እንደ ጥራት መሠረተ ልማት ተቋም የተቀናጀ እና ችግር ፈቺ ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞችም እንደ ከእዚህ በፊቱ የተሰጣቸውን ብቻ የሚቀበሉ ከሆነ የገበያ ዕድል እየተዘጋ የሚሄድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትና ከሌሎች አማራጮች ጋር ተያይዞ የሚመጡ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ፉክክር ብቁ ተዋናይ ሆነው ለመቆየትና ዕድሉን በሚገባ ለመጠቀም ገበያው ምን ዓይነት ምርት በምን ዓይነት የጥራት ደረጃ ይፈለጋል? የሚለውን ታሳቢ በማድረግ ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በእዚህ ወቅት በገበያ ውስጥ በዘላቂነት የመቆየት ትልቅ ፈተና ይስተዋላል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ጥራትም ትልቁ የዓለም መወዳደሪያ መሣሪያ በመሆኑ የአክሪዲቴሽን ዕውቅና ማግኘት ቁልፍ ነገር ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡
አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ካላቸው የሀብት ውስንነትና ከሚገጥማቸው ጠንካራ የገበያ ፉክክር ጋር ተያይዞ ብዙ ፈተና እንደሚገጥማቸው ጠቅሰው፤ እነዚህን ኢንተርፕራይዞች አክሪዲትድ በሆነ ተስማሚነት ምዘና በኩል ምርቶቻቸውን በማስፈተሽ ዓለምአቀፍ የጥራት ደረጃ አሟልተው እንዲያመርቱ እገዛ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም