የንግዱ ማኅበረሰብ የራሱን ታሪክ በደመቀ ቀለም መጻፍ እንዲችል!

 

ንግድ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። በተለይም ባለንበት ዘመን የሸቀጦች ልውውጥ እና ፍላጎት በአይነትም በብዛትም እየጨመረ በሄደበት፤ የሀገራት ኢኮኖሚ እድገት በአብዛኛው አምርተው ወደ ገበያ በሚያቀርቧቸው ሸቀጦች እና ሰርቪሶች ተወዳዳሪነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ፤ ሀገራት ለንግድ እና ለንግድ ሥርዓታቸው ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ እየተገደዱ ነው።

በተለይም እንደኛ ባሉ ንግዳቸውም ሆነ የንግድ ሥርዓታቸው ከእዚያም ባለፈ ለንግድ ያላቸው አስተሳሰብ ዝቅተኛ በሆኑባቸው ሀገራት እና ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚጠበቅ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የንግዱን ዘርፍ በሁለንተናዊ መንገድ ማሳደግ፣ ለእዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ ግንባታ ማካሄድ ወሳኝ ነው። ዘርፉ በሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ያለውን አቅም አሟጥጦ መጠቀም የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠርም ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አይደለም።

በእርግጥ ንግድ በእኛ ሀገር እንደ ሀገረ መንግሥት ግንባታው የረጅም ዘመናት ታሪክ ያለው ነው፤ በእዚህ የረጅም ዘመናት ጉዞው ለሀገር አሁናዊ እድገት የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህም ሆኖ ግን አሁን ላይ ዘመኑ የሚጠይቀውን እሳቤ ተላብሶ እና ዘምኖ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጠበቀውን ያህል እያበረከተ አይደለም። በተለይም የንግዱ ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ፈተናዎችን ማሻገር የሚያስችል ተሻጋሪ አስተሳሰብ ሆነ ሥርዓት ተፈጥሯል ማለት አይቻልም።

ንግዱ እንደ አንድ ትልቅ የኢኮኖሚ ዘርፍ በግለሰብ ደረጃ ሊፈጥር ከሚችለው ተጠቃሚነት ባለፈ እንደ ሀገር የኢኮኖሚ አቅም አድርጎ ማሰብ እና ለእዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ ልዕልና መፍጠር አልተቻለም። በንግዱ ዘርፍ የሚታይ ሕገ ወጥነት፣ እስካሁን ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ጠንካራ ፉክክር ማሸነፍ የሚያስችል ሀገራዊ አቅም መገንባትም አላስቻለም።

አሁን ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ለራሱ፣ ለሀገሩ እና ለመጪው ትውልድ የሚሆን ተስፋ ሰንቆ የሚንቀሳቀስበት የአስተሳሰብ መሠረት ያስፈልገዋል። በኃላፊነት የተገራ ማንነት፣ የተጠቃሚነት ፍላጎቱን በመርህ ፣ ሕግ እና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ መወጣት የሚያስችለው ስብዕና መገንባት የሚያስችል የአስተሳሰብ ልእልና ሊላበስ እና ፍላጎቶቹ ለመጪ ትውልዶች የተሻለ ሀገር በመገንባት ራእይ የተጋራ ሊሆን ይገባል።

በተለይም አሁን ላይ ትናንቶችን በመግራት ነገን የተሻለ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ፣ በንግዱ ዘርፍ ያሉ የትናንት እጸጾችን ነቅሶ በማውጣት፣ ማረም የሚያስችል የአስተሳሰብ ግንባታ ማካሄድ ያስፈልጋል። ዘርፉ ነግዶ ከማትረፍ ባለፈ ሀገርን እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚጠይቅ መሆኑን በተሻለ መልኩ ማጤን ያስፈልጋል።

አሁናዊ ዓለም አቀፍ የንግድ እሳቤ ነግዶ በማትረፍ ግለሰባዊ ፍላጎትን አሸንፎ መገኘት ፣ ነግዶ በሚገኝ ትርፍ ለራስ እና ለራስ ለሆኑ በቅቶ መገኘት አይደለም። የሀገር አቅም ሆኖ መገለጥ ነው፤ ለሀገር እና ለሕዝብ ተስፋ የመሆን ጥልቅ ተልእኮ ነው። ይህንን ተልእኮ ዘመኑን በሚመጥን አስተሳሰብ መግራት ካልተቻለ በግል ተጠቃሚነት ላይ ብቻ ተመስርቶ ረጅም ርቀት መጓዝ አይቻልም።

የንግድ ዘርፉ አሁን ላይ ሀገር እንደ ሀገር ለጀመረችው የለውጥ ጉዞ ስኬት የሚኖረው አበርክቶ ከፍ ያለ ነው። በሁለንተናዊ መንገድ ከፍተኛ ተወዳዳሪነት በሚጠይቀው የዓለም የንግድ ሥርዓት ውስጥ ገብቶ ሀገር እና ራስን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሁሉም በላይ ትናንት ይዘናቸው ከመጣናቸው የተዛነፉ የንግድ እሳቤዎች ሆነ በተጨባጭ ከመጣንባቸው ያልተገቡ መንገዶች መውጣት ይጠይቃል።

የንግዱ ማኅበረሰብ በዓለም አቀፍ መድረክ እንደ ሀገር ዘላቂ ተወዳዳሪ በሚያደርጉን የንግድ ሥራዎች እና የአሠራር ሥርዓቶች ራስን ማስገዛት፤ ለእዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ ግንባታን ማፍጠን ይኖርበታል። በሀገር ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግለሰባዊ ተጠቃሚነት ዘላቂነት ያለው፣ በሕግ እና በሥርዓት የሚመራ አንገት ቀና አድርጎ ለመሄድ ጉልበት የሚሆን ነው።

በተለይም አሁን ላይ የንግዱን ዘርፍ ሊብራላይዝ በማድረግ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን አቅም አሟጠን ለመጠቀም ለጀመርነው ሀገራዊ ጥረት ስኬት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ የእዚህ ራዕይ ተጋሪ መሆን ይጠበቅበታል። ዘርፉን ከግል ተጠቃሚነት በላይ ለሀገር የሚኖረውን ፋይዳ ተረድቶ መንቀሳቀስ ከሙያ፣ ከሕግ፣ ከሞራል እና ከታሪክ ተጠያቂነትን የሚታደግ ጭምር ነው።

ከእዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ሰሞኑን ያደረጉት ውይይት፤ የንግዱ ማኅበረሰብ በንግዱ ዙሪያ ያለውን እሳቤ በማስፋትም ሆነ እንደ ዜጋ ያለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ተገንዝቦ እንዲወጣ፤ በለውጡ የታሪክ ትርክት ውስጥ የራሱን ምዕራፍ በደመቀ ቀለም መጻፍ የሚያስችለውን ዕድል የሚፈጥር ነው !

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You