ዲጂታል ኢትዮጵያ ለሥራ ፈጣሪዎች ምቹ የሥራ እድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፦ የመንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያ የትኩረት አቅጣጫ ለሥራ ፈጣሪዎች ሰፊ የሥራ እድል ይዞ የመጣ መሆኑን የቲና ማርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወጣት ኢዘዲን ካሚል ገለጸ።

ወጣት ኢዘዲን ካሚል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው የስለኢትዮጵያ የፓናል ውይይት መድረክ ላይ “ሥራ ፈጠራ በኢትዮጵያ” በሚል ባቀረበው የመነሻ ጽሑፍ፤ የመንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያን የትኩረት አቅጣጫ፣ የዜጎች ቀላል እና ዘመናዊ የሆነ የአኗኗር ሁኔታዎች ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ለሥራ ፈጣሪዎችም ሰፊ የሥራ እድልን ይዞ የመጣ ነው ብሏል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን የሞባይል መኒ፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማት እድገት፣ የዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን(ስማርትፎን) ተጠቃሚዎች ቁጥር እያሳደገ መምጣቱን የገለጸው ወጣት ኢዘዲን፤ ሶፍትዌር ማበልጸግ እና ኢ-ኮሜርስ በቀጣዩ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ሰፊ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ገልጿል።

የዲጂታል ዘርፉ የሚፈጥረውን የሥራ እድል ወጣቱ አሟጦ ሊጠቀም እንደሚገባና የፋይናንስ ተቋማት ስታርት አፖችን በመመደብ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ መሥራት እንዳለባቸው ገልጾ፤ ሃሳብ ላይ ኢንቨስት ማድረግን ከአሁኑ መለማመድ እንደሚገባ ተናግሯል።

ወጣቶች ሥራ የለም ከሚል እሳቤ በመውጣት ሥራ ፈጣሪ ሊሆኑ እንደሚገባ የገለጸው ወጣት ኢዘዲን፤ በኢትዮጵያ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የኢንኩቬሽን ማዕከላትን እና መሰል ተቋማትን በርካታ ወጣቶች እንዲያውቁት ሊደረግ እንደሚገባ አመላክቷል።

በኢትዮጵያ ብዙ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ቢኖሩም ወደ ገበያው ለመግባት ትልቁ ማነቆ ፋይናንስ መሆኑን አንስቶ፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋት ሃሳብ ላይ ኢንቨስት ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጿል። በዘርፉ ልምድና ተሞክሮ ካላቸው ሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ቢወሰድ መልካም መሆኑን ጨምሮ ተናግሯል።

ሥራ ፈጣሪ ችግርን ወደ ቢዝነስ መቀየር የሚችል ነው። ሀገራችን እንደምናውቀው ብዙ ያልተፈቱ ችግሮች አሏት። ችግር እድል መሆኑን ማመን ይገባል ያለው ወጣት ኢዘዲን፤ ቅጥርን ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ከማሰብ ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል።

እንደ ብሩህ ኢትዮጵያ ያሉ የሥራ ፈጠራ መድረኮች እና ለስታርት አፕ የተመቸ የመንግሥት ሥርዓት ሥራንና ሀብትን ለመፍጠር እንደሚያስችሉ ገልጾ፤ የሥራ ፈጠራ ክህሎት መድረኮች ቢበራከቱ እና ሥራ ፈጣሪዎች ለብቻቸው ቢዝነስን ከመጀመር ይልቅ በቡድን መሥራትን ቢለማመዱ በቀላሉ ችግሮችን ወደ እድል መቀየር እንደሚቻል ጠቁሟል።

እንደ ወጣት ኢዘዲን ገለጻ፤ ኤክስ ሃብ አዲስ፣ ሶልቭ ዒት፣ ቪዛ ስቴም ፓወር እና የስታርታፕ ቡት ካምፕ ያሉ መድረኮች ለሃሳብ እንዴት ቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት እንደሚቻል፣ ቡድን እንዴት እንደሚገነባ እና በአጠቃላይ ቢዝነስ ላይ እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በቂ ግንዛቤ ይሰጣሉ።

እነዚህ የኢንኩቤሽን ማእከላት መኖራቸውን የማያውቁ በርካታ ወጣቶች መኖራቸውን የገለጸው ወጣት ኢዘዲን፤ የኢንኩቤሽን መድረኮች አለመበራከት እና በቀላሉ ተደራሽ ያለመደረግ ችግር የሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን ያደረገ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You