አዲስ አበባ፡- የሴቶች ጥቃትን በጥልቀት የሚመረምር በፌዴራል ደረጃ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሚመራው ፎረም መቋቋሙን የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ ገለፁ። በየክልሎቹም ተመሳሳይ ፎረም እየተቋቋመ መሆኑን ጠቁመዋል። ሚኒስትሯ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በሴቶች ጥቃት ላይ ሦስት ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዷል።
ከሥራዎቹ ውስጥ አንዱ የሆነው የፎረሙ መቋቋም ሲሆን፤ ችግሮቹን እንዴት ነው ማቃለል የሚቻለው? የትኛውስ አካል ምን ስላልሠራ ነውችግሮቹ እየተፈጠሩ ያሉት? በቀጣይስ እንዴት ነው መፍታት የሚቻለው? በሚል ጉዳዩን በጥልቀት ይመረምራል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የፎረሙ አባል መሆናቸውን ነው የገለጹት። ወይዘሮ ያለም፤ ከዚህ ቀደም ሴቶች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ግለሰቦች ላይ የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎች ተመጣጣኝ አይደሉም በሚል ይተች እንደነበር አስታውሰው፤ ለዚህም የፍትሕ ፎረሙን የማጠናከር ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል።
ቀጣይም በትኩረት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አስፈላጊ፣ ተመጣጣኝና አስተማሪ እርምጃ የሚወሰድባቸው ሁኔታዎች እንደሚመቻቹና በዚህም የሕግ መላላት ላይ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። የፎረሙ አንዱ ሥራ በሕግ ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ለይቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ማቃለል እንደሆነ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
በተለይ ጥቃት አድራሹ ላይ አስተማሪ ቅጣት የማይጣልበት ሁኔታ ፍትሐዊም አስተማሪም ባለመሆኑ ይህንን ጉዳይ ሁሉም በጋራ ሊቃወመው እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል። ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከልና ተፈጥረው ሲገኙም አስተማሪ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት ሌላው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ቀድሞ የመከላከል ሥራ እን ደሆነ የጠቆሙት ወ/ሮ ያለም ሴቶች ጥቃት እንዲ ደርስባቸው ማንም መፍቀድ የለበትም ብለዋል።
በዚህም መላው ሕብረተሰብ ሊከላከልና ድርጊቱን በጋራ ሊያወግዘው እንደሚገባ አሳስበዋል። ሚኒስትሯ እንደገለፁት ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ተጎጂ ሴቶች አንዳንዴም ከወንጀሉ አስከፊነት የተነሳ ተስፋ እስከመቁረጥ ይደርሳሉ። ከጥቃቱ ደረጃ የተነሳ ሕይወታቸው እስከማለፍም ሊደርሱ ይችላሉ።
ምንም እንኳ ድርጊቱ ከመነሻው መከሰት ባይገባውም ጥቃት ደርሶ ሲገኝ ለተጠቂዊ የሥነልቦና ድጋፍ ማድረግ ደግሞ በዕቅድ ከተያዙት ተግባራት ውስጥ ሌላው ተጠቃሽ ሥራ ነው። በመሆኑም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የማገገሚያ አገልግሎት እንዲሰጣቸው ማድረግ ይገባል። በስልጠናውም ወደ ሥራ እንዲገቡ የመደገፍና ከችግራቸው ወጥተው ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲገቡ የማድረግ ሥራም ይከናወናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በፍዮሪ ተወልደ