አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥራት ያለው የፍትህ አሰጣጥ እንዲኖር የሚያስችል ሥራ በማከናወን የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ማህበረሰቡ ባህላዊ የህግ አፈታት ሥርዓቶችን በመጠቀም ማህበራዊ እሴቱን ሊያጎለብት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደሳ ቡልቻ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የተከሰቱት አለመረጋጋቶች በፍትህ ሥርዓቱ መንግሥት ተዳክሟል እስከማለት ተደርሷል፡፡ አንድ ጉዳይ ውሳኔ እስካላገኘ ድረስ የህግ የበላይነት ተከብሯል ለማለት አያስደፍርም፡፡
በመሆኑም የኦሮሚያ ፍርድ ቤት ብዛት ላይ ሳይሆን ጥራት ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ደሳ ማብራሪያ ዳኞች ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ፣ ህግና ህግን ብቻ መሰረት አድርገው በቀረበላቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲወስኑ፣ የዳኝነት ነፃነቱ እንዲከበር፣ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር በክልሉ ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር የለውጥ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ በሥነ ምግባር የታነጹ ዳኞችን ማፍራትና ክህሎታቸውን በስልጠና ማጎልበትም የለውጡ አካል ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡም ለዞንና ለወረዳ ዳኞች ስልጠና ለመስጠት እና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋርም በፍትህ ዙሪያ መድረክ ለማመቻቸት ታቅዷል፡፡ እንቅስቃሴዎቹም ለተጀመረው ለውጥ እንደሚያግዝ ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል፡፡ የዳኞች ጥቅማ ጥቅምና የደህንነት ጥያቄም ከተጀመረው ለውጥ ጋር ተካትቶ ምላሽ የሚያገኝ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ‹‹የዳኝነትና የደህ ንነት ጉዳይ ከሀገሪቷ ደህንነት ጋር ይያያዛል፡ ፡ የህግ የበላይነት ሲከበር የሀገር ሰላምም አብሮ እየጎለበተ ይመጣል›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ወደ ፍርድ ቤት መምጣት የሌለባቸው ጉዳዮች በፍርድ ቤት ሥራ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ የጉዳዮች መብዛት በፍርድ ቤቶች በጀትና የሰው ኃይል ላይ ጫና ከማሳደራቸው በተጨማሪ በወቅቱ ውሳኔ ለመስጠትና ጉዳዮችን ለመፈጸም ተግዳ ሮት እንደሚያጋጥም አመልክተዋል፡፡ ሌሎች አማራጮች ካልጠፉ በስተቀር ፍርድ ቤት መም ጣት በገንዘብና በጊዜ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በባህላዊ ሥርዓት ችግሮች ሲፈቱ አብሮ የመኖር ማህበራዊ እሴቶችን የማስተሳሰር ሥራ አብሮ እንደሚከናወንና ጠቀሜታውም ሰፊ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ በዚህ ረገድ በኦሮሚያ በገዳ ሥርዓት አባ ገዳዎች ችግሮችን የመፍቻ ሥርዓታቸው ጠንካራ መሆኑን አስታ ውሰዋል፡፡ ማህበረሰቡም አባገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌ ዎችን በመጠቀም ልችግሮቻቸው መፍትሄ ማግኘት ቢችሉ ከተደራራቢ ችግር እንደሚድኑ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ላይም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ሊያግዙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በለምለም መንግሥቱ