በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና/ዕድሜ ብዙ የሚባል አይደለም፡፡ ከንጉሱ መውደቅ በኋላ በደርግ ዘመን ከተመሰረቱትና መኢሶንንና ኢህአፓን ጨምሮ፤ በኋላም በራሱ በደርግ ውስጥ ተመስርተውና እርስ በርስ ተባልተው ከጠፉት አራት ድርጅቶች ውጭ ከሩቅ የሚጠቀስ ፓርቲም፤ ታሪክም የለንም፡፡
የ1983ቱን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ሆኑ፡፡ በተለይ በሰኔ1983 ዓ.ም የነበረው የመጀመሪያው የሽግግር መንግሥት ምስረታ ላይ የታደሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በርካቶች ነበሩ፡፡ በእንዲህ አይነት መንገድ የተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምስረታና ህልውና ዛሬ ከ27 ዓመታት በኋላም ቁጥሩ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ በመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ ነው፡፡
ለዚህም እርስ በርስ ይፎካከራሉ፡፡ ሲፎካከሩም በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ ችግሮችን ለመቅረፍ፤ ህብረተሰቡን በተለይም እወክለዋለሁ የሚሉትን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ በመስራት ነው። ለዚህም የፖሊሲ አማራጭ በማቅረብ ለአሸናፊነት ይታገላሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡና እውቅና ያላቸው 24 አገራዊና 42 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አገራዊውን ለውጥ ተከትሎ ከውጭ ወደ አገር የገቡትና በዚህም በውስጥ አዲስ የተመሰረቱትን ጨምሮ ይህ ቁጥር ከአንድ መቶ እንደሚበልጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡ ፡
ይህ ሁሉ ተሰባስቦ ግን መቋጫው አንድ ነገር ነው፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ መፎካከር። የፖለቲካ ስልጣን ግን እንዴት ይያዝ የሚለው ደግሞ የግድ መመለስ አለበት፡፡
ይህ ከላይ የጠቀስነው የአገራችንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ስልጣነ መንግስቱን ከያዘው ኢህአዴግ ጀምሮ አብዛኛዎቹ በብሄር/ዘውግ ላይ በሚያጠነጥን አስተሳሳብ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ በአብዛኛዎቹ ነባርም ይሁኑ አዲስ ተመስራቾች የሚታየው ተመሳሳይ አወቃቀር ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ አወቃቀርና አካሄድ ግን ከስር ተነስቶ ወደ መድረክ ከገባበት ካለፉት 27 ዓመታት ጀምሮ ለህዝቡም ለአገርም ብዙም አልጠቀመም፡፡
የወቅቱ የለውጥ ምክንያትም በዋናነት ይህ የፖለቲካ አካሄድ ያመጣው ችግር ነው፡፡ ሁሌም በብሄር/በዘውግ ሲታሰብ የሚያደላው ለ“እኔ” የሚለው ሀሳብ ነው፡፡ የእኛ የሚለው የሚገኘው ከህብረት ነው፡፡ ይች አገር አሁን የሚያስፈልጋት ደግሞ በህብረት የቆሙ ከ“እኔ” ይልቅ “እኛ”ን የሚያቀነቅኑ መሪ ድርጅቶች እንዲኖሯት ነው፡፡ አገሪቱም ወቅቱም የሚፈልጉት ይህንን ነው፡፡ ይህ እውነት አሁን ላይ በገዥው ፓርቲም ይሁን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል።
ሁሉም ወገኖች ዘርዘር ብለውና በተናጠል ከመቆም ይልቅ መሰባሰብ ጀምረዋል። ቀድሞውንም ፓርቲዎቹ/ድርጅቶቹ የቆምነው ለሕዝብ ነው ካሉ፤ ለምንስ ይለያያሉ? ዓላማቸው እንወከለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ወይም ማህበረሰብ ጥቅምና መብት ለማስከበር ከሆነስ በአንድ ሕዝብ ወይም ማህበረሰብ ስም ለምን በርካቶች ሆነው ቀረቡ? እውነትም ለሕዝብ የሚታሰብ ከሆነ መሰረቱ አንድ ነው ማለት ነው። በአንድ መሰረት ላይ ደግሞ በአንድ ጊዜ የተለያየ ነገር አይቆምምና መጣመሩ ወይም አንድ መሆኑ ይደገፋል። አዎን መሰባሰቡ በርካታ ጥቅሞች ይኖሩታል።
በአንድ በኩል በህዝብ ዘንድ የነበረውን ግርታናብዥታ አጥርቶ “ልንመራህ አስበናል” የሚሉትን ፖርቲዎች ቁጥር ያሳንስለትና በእውቀቱና በክትትሉ ስር ያደርግለታል። የሚፈልገውንም እንዲመርጥ ያስችሉታል። በሌላ በኩል፤ እነርሱም ላንተ ቆመናል የሚሉትን ሕዝብ የምርጫ ድምጽ ከመበጣጠስና ከመነጣጠል ያድኑታል። በዚህም ቀደም ሲል በተመሳሳይ ችግር ተጋርጦበት ከነበረው ባልመረጠው ፓርቲ ወይም ድርጅት ከመተዳደር/ከመገዛት ይታደጉታል።
ይህ ደግሞ ድርብ ውጤት ነውና መለመድ ይገባዋል። በርግጥም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች/ድርጅቶች እንደዓላማቸው ቅርበትና እንደፍላጎታቸው አንድነት መሰባሰባቸው የማይታለፍ ወቅታዊ ጉዳይ ነው። በተለይ መጪውን የ2012 ምርጫ በሁሉም ወገን ተቀባይነት ያለው እንዲሆን የመጀመሪያው ርምጃ እና ተፈላጊ ጉዳይ የፖርቲዎቹ ቁጥር ማነስና ለአስተዳደርም ሆነ ለምርጫ ምቹ መሆን ነው።
እናም በዓላማ አንድ ነን ወይም እንመሳሰላለን፤ የምንወክለው ሕዝብ ወይም ማህበረሰብ ተመሳሳይ ነው፤ እንዲሁም የምንከተለው ወይም የምናራምደው ርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ መስመር ያገናኘናል የሚሉ ሁሉ ሊጣመሩ ወይም ሊዋሀዱ ይገባል። ይህ ደግሞ ዘመናዊነትና ተራማጅ አካሄድ ነው።
ይሁንና ጥምረቱ ወይም ውህደቱ ስስና በቀላሉ ለችግር በሚዳርጉ ጉዳዮች ዙሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ይልቁንም ዘመንና ትውልድ በሚሻገሩ አገርንና ህዝብን ለዘለቄታው አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ዙሪያ፤ አብዛኛውን የሀገሪቱን ሕዝብ ባማከለ መልኩ ቢሆን ተመራጭ ነው እንላለን። እንዲህ ሲሆን ዛሬ የሚታየው ከመቶ የዘለቀው የፖለቲካ ድርጅቶቸ ቁጥር በጣት ወደሚቆጠር መጠን እንደሚወርድ አያጠራጥርም።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ባነሰ ቁጥር ለአስተዳደር ይመቻል። ወጪ ይቆጥባል፤ የሚበታተነውን መራጭ ወደአንድ ያሰባስባል። ለሕዝቡም ምርጫው በ“እከሌነት” ከሚሆን ይልቅ በሀሳብና በፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ይሆንለታል። እናም አማራጭ ፖሊሲ ለማቅረብም ሆነ ከዚህ በፊት በምርጫ እጦት የተንገላታ ሕዝብ መካስ የሚቻለው ፓርቲዎቸ አሁን በጀመሩት ሁኔታ እየተጣመሩ ወይም እየተዋሀዱ በአንድ ዓላማና በአንድ ጥላ ስር ተሰልፈው ሲቀርቡ ነው እንላለን። በዚህ ረገድ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ሆነ ሌሎች ወደ ውህደት ለመምጣት ቁርጠኝነት ያሳዩ ድርጅቶች ጅምራቸው መልካም ነውና መወደስ አለባቸው፡፡
ይህ አገርንና ህዝብን ማዕከል፤ ዓላማንና ዴሞክራሲን መሰረት ያደረገ ውህደት እስከ ዛሬ ያጣነውን የህዝብ በምርጫ አሸናፊነት ያረጋግጣል ብለን እናምናለን፡፡ እንዲህ ያለው የፖለቲካ አካሄድ ሲለመድም ለመንበረ መንግሥት የሚደረገው ፉክክር ለማስተዳደር እንጂ ለመግዛት እንዳይሆን መተማመን ይፈጥራል፡፡ እናም ሁሉም አካላት ህዝብንና አገርን አስበው በኃላፊነት ሰርተው ለፍሬ እንዲበቁ ማገዝ የሁሉም የአገር ፖለቲካ ያገባኛል ባይ ግዴታ ነው እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011