ማይጨው፦ በ1928 ዓ.ም በተደረገው የጣልያን ወረራ ለአገራቸው ሰማዕት የሆኑ ጀግኖች አጽማቸው ተገቢውን ትኩረት እንዳላገኘ ተገለጸ።
የማይጨው የደብረ ሰማዕት ቅዱስ ሚካኤል ደብር አገልጋይ ሊቀ ትጉሃነ ረዳኢ እንደገለጹት፤ መንግሥት ትኩረት ስላልሰጠው የሰማዕታቱን አጽም አሰባስቦ ያስቀመጠው ገዳሙ ነው። አሁን ያለበት ሁኔታ ለእይታ ምቹ አይደለም። በርካታ አጽም በሳጥንና ወለል ላይ ተከምሮ ይገኛል። የሰው ጭንቅላት ጨምሮ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚታዩበት ይህ የአጽም ስብስብ፤ እስከአሁንም ገዳሙ ባዘጋጀለት አነስትኛ ክፍል ውስጥ ይገኛል።
የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ኃለፎም በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሰማዕታቱ አጽም ታሪካዊ ሙዝየም መሆን ሲገባው ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ ቢሆንም አሁን ግን እቅድ ተይዞለታል። የሙዝየም ግንባታ ለመጀመሪም ዲዛይን ወጥቷል፤ የቦታ ርክክብም ተደርጓል።
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ፤ የሙዚየሙ ግንባታ ሲጠናቀቅ የጀግኖች ሰማዕታት አጽም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ታሪካዊ መረጃዎች ሁሉ የሚሰነዱበት ይሆናል። በተለይም በማይጨው አካባቢ የጦርነት ቦታዎች ስለነበሩ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ይሠሩበታል። ጦርነት የተካሄደባቸውና የማይጨው ዙሪያ ተራሮች ራሳቸው የቱሪስት መስህብ ይሆናሉ።
የገዳሙ አገልጋይ ሊቀ ትጉሃን ረዳኢ እንደሚሉት ቤተክ ርስቲያኑም የተሰየመው ለሰማዕታቱ መታሰቢያነት ነው። በቦታው ላይ ግን ፋሽስት ጣልያን ከ40 ሺህ በላይ ጀግኖችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለውን መርዛማ ጋዝ በአውሮፕላን በመርጨት የጨፈጨፈበት በመሆኑ ገዳሙ ደብረ ሰማዕት ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ተብሏል።
በ1928 በተደረገው የጣልያን ወረራ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጦሩን ለመመከት በሦስት አቅጣጫ፤ በሽሬ ተንቤንና እምባአርዓዶም ማጥቃት ጀመረ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ማይጨው ላይ ተጠናክሮ ሲቀጥል ፋሽስት ጣልያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለውን መርዛማ ጋዝ በአውሮፕላን በመርጨት የአካባቢውንም ህዝብ መጨፍጨፉ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
ዋለልኝ አየለ