የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ፍኖተ ሰላም የሚገኘው ኃይሉ ዓለሙ ኮሌጅ የእውቅና ፈቃድ ባልተሰጠበት በፋይናንስና አካውንቲንግ የትምህርት መስክ በዲግሪ መርሃ ግብር መዝግቦ ሲያስተምር በመገኘቱ ተማሪዎቹን እንዲያሰናብት ውሳኔ ማስተላለፉን ገለጸ።
ኮሌጁ ፍኖተ ሰላም ኮሌጅ በሚል ስያሜ ሲጠራ በነበረበት ወቅት በ2007 ዓ.ም በማኔጅመንት፣ በአካውንቲንግና ፋይናንስ እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የትምህርት መስኮች በመደበኛ መርሃ ግብር በፍኖተ ሰላም ካምፓስ ትምህርት ለመስጠት የእውቅና ፈቃድ ጥያቄ አቅርቦ በመመሪያው መሰረት በመጀመሪያው ግምገማ አስፈላጊውን መስፈርት ለማሟላቱ እና እንደገና በተሰጠው የ3 ወር ጊዜ ውስጥ በተካሄደውም ግምገማ መስፈርቱን አሟልቶ ባለመገኘቱ የእውቅና ፈቃድ ጥያቄውን ከአንድ ዓመት በኋላ እንዲያቀርብ ተገልጾለት ነበር።
ነገር ግን በካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት መስክ የእውቅና ፈቃድ ተከልክሎ ሳለ ተማሪዎችን መዝግቦ ሲያስተምር መቆየቱን ከተማሪዎቹና ከህብረተሰቡ በደረሰው መረጃ እንዲሁም ከብዙ ምልልስ በኋላ ከራሱ ከተቋሙ በተጻፈ ደብዳቤ ስለተረጋገጠ ለፈጸመው የመመሪያ ጥሰት የእርምት ውሳኔዎችን መተላለፉን ኤጀንሲው አሳውቋል፡፡
ኤጀንሲው ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች፦
1. በአካውንቲንግና ፋይናንስ የትምህርት መስክ በ2009 ዓ.ም ያለዕውቅና ፈቃድ መዝግቦ የሚያስተምቸቸው ተማሪዎች በኤጀንሲው ዕውቅና የማይሰጣቸው ስለሆኑ በአስቸኳይ አሰናብቶ አፈጻጸሙን ሪፖርት እንዲያደርግ፤
2. ለፈጸመው ጥፋት ከ2012 የትምህርት ዘመን በፊት በአካውንቲንግና ፋይናንስ የትምህርት መስክ የእውቅና ፈቃድ ጥያቄ እንዳያቀርብ ዕገዳ የተጣለበት ከመሆኑም በተጨማሪ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣችሁ መሆኑንና፤
3. ከዚህ በላይ በተራ ቁጥር 1 እና 2 ላይ በተጠቀሰው መሠረት ተገቢውን ማስተካከያ በወቅቱ የማያደርግና ከተፈጸመው ጥፋት ትምህርት ወስዶ ወደ ህጋዊ አሠራር የማይመለስ ከሆነ ጥብቅ ህጋዊና አስተዳዳራዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡
ምንጭ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ