በቻይና አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ላይ መሰማራት በእድሜ ልክ ወይም በሞት ቅጣት ያስቀጣል፡፡
47 ኢትዮጵያውያን በአደንዛዥ ዕፅና ጫት ዝውውር ወንጀል በቻይና በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ዛሬ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያውያኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት በህገወጥ ደላሎች አማካኝነት የነፃ ትምህርት እድል አግኝታችኋል በሚል ተታለው ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ወደ ቻይና ካቀኑ በኋላ በደላሎች የተነገራቸው ነፃ የትምህርት እድል ሀሰት መሆኑ ሲነገራቸው በሀገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ተሳትፈው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ወደ ቻይና በሚጓዙበት ወቅት መልዕክት አድርሱልን በሚል ምንነቱን የማያውቁትን እሽግ በመያዝ ወደ ሀገሪቱ ሲገቡ በሚደረግ ፍተሻ አደንዛዥ ዕፅ ወይም ጫት ይዘው በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል አቶ ነብያት፡፡
የኢትዮጵያውያኑ ጉዳይ በቻይና በሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲና ቆንፅላዎች በኩል ክትትል እየተደረገበት ነው የተባለ ሲሆን ህገወጥ ደላሎች በሁለቱም ሀገራት እንደሚገኙና ጥብቅ ክትትል በማድረግ መሰል ወንጀለኞችን ለመከላከል ኢትዮጵያና ቻይና በጋራ እየሰሩ ስለመሆኑም በመግለጫው ተነግሯል፡፡
አሁን በቁጥጥር ስር ከዋሉት ኢትዮጵያውያን ውስጥ የተወሰኑት የፍርድ ቅጣት ያገኙ ሲሆን ሌሎችም የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በአጭበርባሪዎች በመታለል ለአላስፈላጊ እንግልት ከመዳረግ በፊት የሚገኙ ነፃ የትምህርት እድሎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥና ጉዞ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በተጨማሪም ህገ ወጥ ስደት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን የተናገሩ ሲሆን በሁለት ሳምንታት ብቻ 747 ኢትዮጵያውያን በህገወጥ መንገድ ወደ የመን ለመግባት ሲሞክሩ መያዛቸውን እና ወደ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሳምንትም 1 ሺህ 40 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ እንዲሁም 1 ሺህ 415 ደግሞ ከፑንትላንድ ወደሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን 500 ዜጎችን ከሳዑዲ እና 517 ደግሞ ከፑንትላንድ ወደሀደገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
አቶ ነብያት በመግለጫቸው የኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል ያሉ ሲሆን በቆይታቸውም ከጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
ከፕሬዚዳንቱ ጋር 100 የሚሆኑ የኬኒያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አብረው መጥተዋል የተባለ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር የሚግዝው የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው ተብሏል፡፡
በድልነሳ ምንውየለት