አዲስ አበባ፡- ወጪ ቁጠባ እና የተቋማትን ባህሪ ያላገናዘበ ለሁሉም ተቋማት የሚወጣ መመሪያ
የምርምር ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ጠቆመ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ አብተው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ተመራማሪዎች በጊዜ ሳይገደቡ የያዙትን ሃሳብ ለማውጣት እና አዲስ ሃሳብ ለማመንጨት ራሳቸውን ለስራው መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ብዙ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡
ነፃ ሆነው እንዲሰሩ፣እንዲያነቡ እና ሙሉ ሰዓታቸውን ሥራቸው ላይ እንዲያውሉ ደግሞ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ገንዘብ ማውጣት የግድ ነው፡፡ ሆኖም ወጪ ቁጠባው እና የሚወጡ መመሪያዎች የተቋማቸው ስራ ለማሳካት አግዷቸዋል፡፡
‹‹ወጪ ቁጠባ በሚል ዋናው ስራ ከተጎዳ ዋጋ የለውም ›› የሚሉት አቶ አህመድ፤ በምርምር ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥቅማ ጥቅምን ከማሟላት ባሻገር ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ እስከ አሁን ያንን ማድረግ ባለመቻሉ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ተመራማሪዎች እየረኩ አይደለም፡፡ ስራው እንደ ሙሉ ሰዓት ሳይሆን እንደ ቢሮ ስራ እንዲታይ እንዲሁም ተመራማሪዎቹ ወጣ ገባ እያሉ እንዲሰሩ በማስገደዱ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን አመላክተዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ አርባ ተመራማሪዎች ይገኛሉ ፡፡ 31ዱ ቋሚ ሆነው በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩ ናቸው፡፡ (ከአቶ አህመድ አብተው ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ በገጽ 11 ይመልከቱ)
አዲስ ዘመን የካቲት22/2011
በምህረት ሞገስ