አዲስ አበባ፤ በአገሪቱ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በሚፈለገው ልክ ማደግ ባለመቻላቸው በርካታ የኬሚካል የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ከውጭ ለማስገባት እየተገደደ መሆኑን የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ከያስካይና ቤተሰቦቹ ስታርችና አድሄሲቭ አምራች ኢንዱስትሪ ጋር በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ትላንት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ እንዳሉት፣ኢትዮጵያ ለብዙ ምርቶች ምቹ የሆነችና መሰረታዊ ግብዓቶችም በበቂ ሁኔታ ያሏት ቢሆንም መሰረታዊ የግብርና ምርቶችን ሳይቀር ከውጭ እያስገባች ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ኢንዱስትሪዎቻችን በሚፈለገው ልክ ማደግ ባለመቻላቸው ነው።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ ህብረተሰቡ ለእለት ተዕለት ኑሮው የሚጠቀምባቸው፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ እንዲሁም ለተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችና ግብዓቶች በሙሉ ከውጭ አገር እየገቡ ሲሆኑ፣እነዚህን ደግሞ በአገር ውስጥ ባለ ሀብት መተካት ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሔ ግብርናውን ማዘመን፣ ማዕድናት የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ላይ ያሉ አሰራሮችን ዘመናዊ ማድረግና ምርቶቹንም እሴት ጨምሮ ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም ተወዳዳሪ ማድረግ ያስፈልጋል።
«ኢንዱስትሪያችን ባለማደጉ ብዙ ምርቶችን ከውጭ እንድናመጣ አስገድዶናል » ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ይህም ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ የተለያዩ ኢንዱስተሪዎች ባለቻቸው አቅም የሚያመርቱትንም በቅጡ ከመጠቀም ይልቅ ከውጭ ወደ ማስመጣቱ ማምራታቸውን፤ ይህ ደግሞ የማይደገፍ ከመሆኑም በላይ ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ፍጥነት እንዳያድግ ብሎም በአገር የውጭ ምንዛሪ ላይም ከፍተኛ ጫናን የሚያሳድር መሆኑን አብራርተዋል።
ኢንስቲትዩቱም የተማሩ ሰዎች እውቀታቸውን ወደ ክህሎት ቀይረው በአገር ውስጥ ያሉ ግብዓቶችን በጥሩ ሁኔታ ለአገልግሎት ማብቃት እንዲችሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደስታ ላምቤቦ በበኩላቸው ኢንዱስትሪያላይዜሽን በአገሪቱ ገና አላደገም፤ ይህ ደግሞ በአገር ውስጥ አምርተን ልንጠቀምና ለሌሎች ግብዓት አድርገን ልናቀርባቸው የምንችላቸውን ምርቶች ሁሉ ከውጭ እንድናመጣ አስገድዷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግስት በአገር ውስጥ የማይመረቱ ግብዓቶች እንዲመረቱ፣ የተመረቱትም ምርቶች ወደ ውጭ ተልከው ምንዛሪን እንዲያስገኙ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፤ በመሆኑም ይህ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት፣ምርታቸውንም በአግባቡ መጠቀምና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በአገር ውስጥ ያሉት ጥቂት ኢንዱስትሪዎችም በመደጋገፍና አንዱ የአንዱን ምርት መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የሚፈለገው ውጤት ካለመምጣቱም በላይ በሌለን የውጭ ምንዛሪ ግብዓቶች ከውጭ ስናስገባ እንኖራለን ብለዋል።
«ያስካይና ቤተሰቦቹ ስታርችና አድሄሲቭ አምራች ኢንዱስትሪ » ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ይትባረክ እንዳሉትም በአገሪቱ ያሉ ጥቂት ኢንዱስትሪዎች የሚታይባቸው ትልቁ ችግር ተሳስሮ ያለመስራት ነው ።
የእርሳቸውን ፋብሪካ ማሳያ አደርገው ሲናገሩም ፋብሪካው በስታርች ምርት ብቻ የአገሪቱን 70 በመቶ ፍላጎት የመሸፈን አቅም አለው፡፡ ሆኖም የተጠቃሚዎች ፍላጎትና እምነት ውስን በመሆኑ የአቅሙን ያህል በማምረት ለዚህ ተብሎ ወደ ውጭ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን አለመቻሉን ይናገራሉ።
ይህም ቢሆን ግን በ40 በመቶ አቅሙ እያመረተ ላለፉት 20 ዓመታት በወር እስከ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እያዳነ እንደሚገኝ አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።
መንግስት በአገር ውስጥ ሊመረቱ ለሚችሉ ምርቶች ድጋፍ ማድረግ ያለበት ሲሆን፤ የገበያ ማስተዋወቅ ስራዎችንና የትስስር መንገዶችንም ማመቻቸት አለበት ብለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት22/2011
በእፀገነት አክሊሉ