የኦለንጪቲ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ማሜ ነጋሽ ለበርካታ ዓመታት በሌሊት ተነስተው ከጅብና ከሌሎች የዱር አራዊቶች ጋር በመጋፋት ስድስት ሰዓት የሚሸፍን የእግር መንገድ ተጉዘው ውሃ ሲቀዱ ቆይተዋል፡፡ ምንም እንኳን ውሃውን ለመቅዳት ሌሊት ጉዟቸውን ቢጀምሩም ረጅም ርቀት መሄዳቸው ስለማይቀር ለቀኑ የጸሐይ ሀሩር መጋለጣቸውም ግዴታ ነበር፡፡ ይህ የሆነው በከተማዋ ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር በመኖሩ ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለውን ድካም ለዘመናት ሲያስተናግዱ ቢቆዩም፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ይገባልን ይሆናል የሚል ተስፋ ነበራቸው፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት በ2008ዓ.ም በአካባቢያቸው የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲጀመር፤ ተስፋቸው ለመለመ፡፡
አሁን ላይ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሥራ መጀመሩ ውሃን በማንኛውም ጊዜ ከበራፋቸው ላይ ቀድተው ለመጠቀም እንዳስቻላቸው የሚገልጹት ወይዘሮ ማሜ፤ ፕሮጀክቱ የውሃ ጥምን ለማርካት ብቻ ሳይሆን ለከተማዋ እድገት መሰረት በመሆኑም ድርብ ደስታን እንዳጎናጸፋቸው ይናገራሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ ማሜ ሁሉ ከንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት የተነሣ ረጅም መንገድ በመጓዝ ለጤና ተስማሚ ያልሆነ ውሃ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን የሚገልጹት ሌላው ነዋሪ አቶ በላይ ገዛኸኝ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው በነበረው የውሃ እጦት እንስሳት የሚጠጡትን ውሃ ፍለጋ ከረዥም ርቀት ውሃ ለማምጣት ስለሚከብዳቸው እንስሳቱም በውሃ ጥም ይሰቃዩ እንደነበር እና ከእንስሳቱም ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ባለመቻላቸው በኑሯቸው ላይ የውሃ ችግሩ አሉታዊ ጫና አሳድሮ መሰንበቱን ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በየቤታቸው የቧንቧ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናቸው፤ የከብት ማጠጫና የልብስ ማጠቢያ ገንዳ በመስራት ያገኙትን ውሃ ያለምንም ብክነት እየተገለገሉበት እንደሆነ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳት ሳይቀሩ ውሃ ጥማቸው እየተቆረጠ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡
የሰው ልጅ ሕይወቱን ለማቆየት ከእስትንፋሱ ጋር የተቆራኙና አማራጭ ከማይገኝላቸው መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል ውሃ አንዱ ነው ያሉት አቶ በላይ፤ አብስሎ ለመብላት፣ ጠጥቶ ለመርካት እና ታጥቦ ለመጽዳት አገልግሎት የጀመረው የውሃ ፕሮጀክት ፋይዳው ቀላል እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡
በኦለንጪቲ ዳንጉሬ ጢዮ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ የውብዳርተግን ሀይሌ በበኩላቸው፤ ቦታው ሞቃታማ በመሆኑ በአካባቢያቸው የውሃ አማራጭ አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ረዥም ርቀት ተጉዘው ውሃ ለመቅዳት ጊዜና ጉልበታቸውን ሲያፈሱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ረጅም ርቀት በመጓዝ የሚቀዱበት ቦታ ሲደርሱ ረጅም ሰልፍ ይጠብቃቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ መንግስትና፣ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተሳትፎ በተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግራቸው ተቃሎ እንስሳት ጭምር ያለ ችግር ውሃ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የውሃና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰይፈዲን መሃዲ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በተባበሩት መንግስታት የህፃናት ነፍስ አድን ድርጅት ‹‹ዩኒሴፍ›› እና በ‹‹ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ›› በብሪታኒያ መንግስት የዓለም ዓቀፍ ልማት እና እርዳታ ክፍል ድጋፍ በኦለንጪቲ ከተማና አካባቢዋ በ120 ሚሊዮን ብር የተሰራ ነው፡፡ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረጉም ባሻገር ሌሎች አካባቢዎች ላይ ተመሳሳይ ስራዎችን ለማከናወን እንደተሞክሮ ይወሰዳል፡፡ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ሥራ ለማጠናቀቅ ሶስት ዓመታትን ፈጅቷል፡፡ አገልግሎቱ ኦለንጪቲ ከተማና አካባቢዋ ላሉት ሶስት የገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ ይሆናል፡፡ አካባቢዋ ከዚህ ቀደም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያላገኘች በመሆኑ የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ችግሩን በማቃለል 48ሺ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
የዩኒሴፍ ተወካይ በኢትዮጵያ ሚስ ጊላን ሚልሶፕ በበኩላቸው፤ የኦለንጪቲ መጠጥ ውሃ አስተዳደር ፕሮጀክት እና ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች መኖራቸው በኢትዮጵያ ሴቶችና ልጃገረዶች ውሃ ለመቅዳት ረጅም ርቀት በመጓዝ ያጠፉት የነበረውን ጊዜና ያባክኑ የነበረውን ጉልበት ይቆጥባል፡፡ በመሆኑም ልጃገረዶቹ ትምህርት ቤት ለመሄድና ለመማር፤ እናቶችም ከልጆቻቸው ጋር ጊዜያቸውን ለማሳለፍና ሌላ ጠቃሚ ተግባር ለመከወን ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ ለህብረተሰቡም ንጽህናው የተጠበቀ አካባቢ እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው፤ ለምርቃት የበቃው የውሃ ፕሮጀክት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ 22 ሺህ ሕጻናትን ጨምሮ ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ይሰጣል በማለት፤ ፕሮጀክቱ የከተማውን የውሃ ሽፋን 100 በመቶ እንደሚያደርስና በተጨማሪም በኦለንጪቲ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ሦስት የአርሶ አደር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቂና አስተማማኝ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ በማድረግ ለኢኮኖሚ እድገቱ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ጤናማና ምርታማ ዜጋ ለመፍጠር ዋነኛው ዓላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኦለንጪቲ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት የደረቅ ቆሻሻ ማጣሪያ፣ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት፣ በትምህርት ቤቶችና በገበያ ቦታ መጸዳጃ እና መታጠቢያ ቤቶች የተካተቱበት ሞዴል ፕሮጀክት ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በታቀደው መሠረት በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ተጀምሮ በያዝነው ዓመት ተጠናቋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት22/2011
በአዲሱ ገረመው