አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወጥቶ የነበረው ‹‹የፀረ- ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001›› የተደረጉ ማሻሻያዎች ጎን ለጎን የፈፃሚውን አካል ክህሎት ማሳደግ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር የሥራ ቡድን አስታወቀ፡፡
በቡድኑ ውስጥ በአማካሪነት የሚሰሩት ጠበቃና የሕግ አማካሪ እንዲሁም የሕግ መምህር አዲ ደቀቦ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ረቂቁ ተግባር ላይ ሲውል ይገጥሙታል ተብለው እንደ ስጋት የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የሽብር ጉዳዮችን ማቀድ ወንጀል ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ ይህም ከድርጊትና ከዝግጅት በመለስ ያለ በመሆኑ የሚያስጠይቁት ምን ዓይነት ድርጊቶች ናቸው? የሚለው አነጋጋሪ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕጎቹና ተቋማቶቹ ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ እንዲህ እናድርግ ብለው ነበር በሚል ሰዎችን ሊከስሱ ይችላል፡፡ በመሆኑም አዋጁ ሲለወጥ የፈፃሚውን አካል፣ ፍርድ ቤቶችና ዐቃቤ ሕግ ራሱን ከፍ ባለ መልኩ ሊያሳድግ ይገባዋል፡፡ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገና ጤነኛ የሆነ ሕግ ጤነኛ በሆነ መልኩ ካልተተረጎመ ስጋት ላይ መጣሉ አይቀሬ ነው፡፡
በአገሪቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወጥቶ የነበረው የቀድሞ አዋጅ እያንዳንዱ ድንጋጌ ላይ በተወሰነ ደረጃ ለውጥ ተደርጓል፡፡ በተለይ ደግሞ የቀድሞው ሕግ ይወቀስበት የነበረው የሰብዓዊ መብት እንደነበር አስታውሰው፤ ሰው ከታሰረ በኋላ ምን ይደረጋል? የፍርድ ቤት ሚናስ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ዋስትና ይከለከላል? ከሚሉ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ወቀሳ ይደርስበት እንደነበር አማካሪው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከትርጉሙ ከአንቀጽ ሁለት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድንጋጌ ድረስ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ ረቂቅ ስለሆነ በየጊዜው መቀያየር ቢኖርም እስካሁን ግን 53 አንቀጾች መሻሻላቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡
ስድስት ክፍሎች የያዘው ረቂቁ ሽብር ወንጀል ምንድን ነው? ምን ሲደረግስ ሰው ለቅጣት ይዳረጋል? ድርጅትን በአሸባሪነት ስለመሰየም፣ ልዩ የምርመራ ዘዴ ስለመጠቀምና የተጠርጣሪ አያያዝ፣ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል ተቋማት ያላቸው ስልጣንን በሚደነግግ መልኩ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት የወጣው ረቂቅ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እንዲቀሩ በማድረግ በስልክ ልውውጥ የተገኙ ማስረጃዎች ካሉ በቀጥታ በተገኙበት መልኩ የድምጽ ማስረጃው ለፍርድ ቤት ካልቀረበ በስተቀር ቅቡል እንዳይሆን ተደርጓል፡፡ በልዩ ምርመራ በጠለፋ የሚገኙ ማስረጃዎችን ለማግኘትም የፍርድ ቤት ፍቃድ ወሳኝ ነው፡፡ የምርመራ ዘዴውን መጠቀም የሚቻለውም በመደበኛ የምርመራ ዘዴ ማጣራት ሳይቻል የቀረ እንደሆነና ይህንንም ጥያቄ ለፍርድ ቤት አስፈቅዶ ተቀባይነት ካገኘ ብቻ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ሰዎች ከተያዙ በኋላም የተያዙበት አግባብ ሕጋዊነት ፍርድ ቤት እንዲመረምር ተደርጎ ሕጋዊ ካልሆነ መልቀቅ እንደሚያስችል አመላክተዋል፡፡
በአዋጁ የደህንነት ጉዳይም ከግምት ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡ ይህ ግን የሰብዓዊ መብትን በሚጥስ መልኩ ሳይሆን በማቻቻል እንዲረቅቅ ነው የተደረገው፡፡ ሕጉ ልዩ የምርመራ ዘዴ ቢፈቅድም ተግባር ላይ ሲውል ግን አላግባብ እንዳይተረጎም የጥንቃቄ ድንጋጌዎችን ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ አንፃርም ክፍተት የለበትም ብለዋል፡፡
በአዋጁ ላይ ለውጥ ተደርጎ ጽፈኝነትን የተመለከቱ ወደ ሽብር ተግባር ሊያመሩ የሚችሉ ተግባራትን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ከወዲሁ ሕክምና ክትትል እንዲያገኙ፣ ለጥንቃቄ እርምጃ እንዲገለሉ፣ በተለይም በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መንግስት ኃላፊነት እንዲኖረው ተመላክቷል፡፡ በዚህም ግለሰቡ አመለካከቱን ይዞ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ከመጠበቅ ይልቅ አስቀድሞ ቁጥጥር እንዲያደርግ በረቂቁ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ተፈፃሚነቱ ላይ ሰዎቹ እንዴት ይለያሉ? የሚለው በአሰራር ሂደት የሚዳብር ነው፡፡ ችግሮቹን ለማቃለልም ረቂቁ ሰብዓዊ መብትን በጠበቀና የተከሳሽ መብት በማይጋፋ መልኩ መፈፀምን የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ የመተርጎምና የማስፈፀም ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ራሳቸውን ለውጠው የማስፈፀም ሥራ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
በአገሪቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተሻሽሎ በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ በትናንትናው ዕለት የተፎካካሪ የፓርቲ አመራሮች፣ የሕግ ምሁራንና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት22/2011
በፍዮሪ ተወልደ