ድሮ ድሮ በተለይም የትምህርት ደረጃ በማይጠይቁና የሥራ ልምድ በማያስፈልጋቸው እንደ ወጥ ቤት፣ የሰው ቤት ሠራተኝነት፣ ጽዳት፣ ጥበቃና ሌሎች መሰል ሥራዎች ፈላጊና ተፈላላጊ የሚገናኘው በዘመድ፣ በጓደኛ ባስ ካለም ሰፈር ውስጥ በሚዘዋወሩና የማገናኘት (የድለላ) ሥራን በሚሰሩ የሚታወቁ ሰዎች ነበር።
ዛሬ ላይ ይህ ሁኔታ ተቀይሮ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ እንዲሁም በመስሪያ ቤቶችም ሆነ በተለያዩ ድርጅቶች እና መሰል ቦታዎች የጥበቃና ጽዳት ሠራተኞች በሚፈለጉበት ወቅት ቀድሞ ወደ ህሊና የሚመጡት የሦስተኛ ወገን አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ናቸው። እነዚህ ኤጀንሲዎች የሚፈልገውን የሰው ሀይል በወቅቱ በማቅረብ በኩል አጋዥ ቢሆኑም፤ ከጀርባቸው የሚነሱባቸው ቅሬታዎች ደግሞ ይህም አለ እንዴ የሚያስብሉ ሆነዋል።
ወጣት እንየው በላይ በኤጀንሲዎች አማካይነት እየተዘዋወረ የጥበቃ ስራን በመስራት ላይ እንደሆነ ይናገራል። ‹‹ኤጀንሲዎች በተለይም ሥራ ፈልገን ለማግኘት ለምንቸገር እንዲሁም የምናቀርበው የትምህርት ማስረጃ ለሌለን ሰዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ቢሆኑም፤ በእኛ ጉልበትና ወዝ ለመነገድ የሚያደርጉት ጥረት ግን ያሳዝናል›› ሲል ብሶቱን ይናገራል።
‹‹ኤጀንሲው እኛን የሚቀጥረንና ከምንሰራበት ተቋም ጋር የሚዋዋለው ገንዘብ ልክ አይገናኝም። ይህ ደግሞ የአደባባይ ምስጢር ነው፤ ምንም ድብቅ ነገርም የለውም፡፡ እኛም አምነንበት ነው የምንገባው፤ አንዳንድ ጊዜ ግን እንደ ሰውና ዜጋ መተሳሰቡ አይከፋም›› ይላል።
እርሱ በጥበቃ ሥራ ላይ አንድ ቀን ውሎ ማደርን እንደሚሰራ ገልጾ፤ ለዚህ የሚከፈለውም ሦስት ሺ ብር መሆኑን ይናገራል። ኤጀንሲው ግን ከእርሱ የሚያገኘውን በውል ባያውቅም ብዙ ተጠቃሚ መሆኑን አይጠራጠርም። ስራን ከፈላጊው ጋር ማገናኘት ጥሩ ቢሆንም፤ አንዱ እየሰራ ሌላው ስላገናኘ ብቻ ከሰራተኛው በላይ ማግኘቱ ግን ጥሩ አለመሆኑን ያብራራል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ቴዎድሮስ አሰፋ በበኩሉ፤ ኤጀንሲዎች ስራን በማገናኘት ቢጠቅሙንም ለምንሰራው ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያን እንድናገኝ ባለማድረግ ደግሞ እየጎዱን ነው›› ይላል። እርሱ ግን ከሁሉም በላይ የሚያበሳጨው ከሚያሰሩት አካላት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት መፍጠር አለመቻሉ ነው። የሚያሰሩትን አካላት በቀጥታ አለማግኘቱ ደግሞ መብቱን ለመጠየቅ ብሎም የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣትና በሚሰራው ሥራ እምነት ለማሳደር እንዳስቸገረው ይናገራል።
‹‹የምንሰራው ሥራ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ ቢሆንም፤ መብቶቻችን ባለመከበራቸው በኑሯችን ላይ ለውጥ ማምጣት አልቻልንም፤ መንግሥት ይህንን በደላችንን ይመልከትልን›› ሲል ያሳስባል።
ወጣት አለምጸሀይ ማሩም በተመሳሳይ ለጥበቃ ሥራ በኤጀንሲ የተቀጠረች ናት፤ እርሷም እንደምትለው በየሰው ቤት ከመንከራተት ይሻላል ብላ የጀመረችው ሥራ የሌሎች መጠቀሚያ ከማድረግ ባለፈ በእርሷ ህይወት ላይ ምንም ለውጥ አለማምጣቱን ትገልጻለች። በመሆኑም ኤጀንሲዎች ለሚያሰሩት ሥራ ተገቢውን ክፍያ እንዲከፍሉ የሚመለከታቸው አካላት ሊፈትሿቸው እንደሚገባም ነው የምትናገረው።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ የወጡ ህጎች በበቂ ሁኔታ ተፈጻሚ ባለመሆናቸው በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዳይኖር አድርጎ ቆይቷል፤ በዚህም ምክንያት ዜጎች በተለይም ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሰረታዊ ፍላጎታቸው አልተሟላም።
በቀጣይም የአሠሪና ሰራተኛ ግንኙነትን የሚያሻሽሉ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና በአገር ውስጥ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የስራ ስምሪት አገልግሎት ስለሚሰጡበት ሁኔታ ለመወሰን የሚያስችል መመሪያም እንደሚዘጋጅ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የዴሞክራሲና የህግ የበላይነትን ከማስጠበቅ አንጻር በተለይም ይፋ የሆነው የአንድ ገጽ ዕቅዱ ውስጥ ተካቶ እየተሰራ መሆኑንና በዚህም የሚዘረጉ ስርዓቶች ይኖራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከህግ ማዕቀፎች የሚጀምር በመሆኑ በግል ኤጀንሲዎች ያሉም ቢሆኑ የራሳቸው ፌዴሬሽን አላቸው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከእነሱ ጋር በቅንጅት በመስራት ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ስርዓት ይዘረጋል። ይህ ከሆነ የዜጎችን ሮሮ መስማት ከመቻሉም በላይ መወሰድ ያለባቸውንም እርምጃዎች በጊዜው ለመውሰድ የሚያስችል ይሆናል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍቃድ አውጥተው የጥበቃ፣ የጽዳትና ሌሎች ባለሙያዎችን ለአሰሪዎች በማቅረብ ላይ የተሰማሩ 290 የሦስተኛ ወገን አሰሪ ኤጀንሲዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከሦስተኛ ወገን አሰሪ ኤጀንሲዎች መካከል የተወሰኑትን በማነጋገር መረጃ ለማካተት ጥረት ቢያደርግም ፈቃደኛ መሆን ስላልቻሉ ይዞ መውጣት ያልቻለ መሆኑ ይታወቃል፡፡