ውጫሌ፡- ለዓድዋ ጦርነት ምክንያት በሆነውና የውጫሌ ውል በተፈረመበት ታሪካዊ ቦታ ላይ የተሰራው የይስማ ንጉስ የባህል ማዕከል ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ በፊት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፡፡
የይስማ ንጉስ የባህል ማዕከል ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ቴክኒካል ማኔጀር ኢንጂነር ዮሐንስ አሰፋ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም የተጀመረው የባህል ማዕከሉ ግንባታ 62 በመቶ በመጠናቀቁ ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
እንደ ኢንጂነር ዮሐንስ ገለፃ ቀሪው 48 በመቶ ከጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ወዲህ ይጠናቀቃል፡፡ ለዚህ እርግጠኛ መሆን የተቻለው አስቸጋሪ የሚባለው ስራ በመጠናቀቁ ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የይስማ ንጉስ የባህል ማዕከል የቀለም ቅብ ጥቁርና ነጭ ሲሆን፤ አሸናፊውን ጥቁርና ተሸናፊውን ነጭ ለመግለጽ ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ አሸናፊነትን የሚያመለክት የእጅ ምልክትም በማዕከሉ ጣሪያ ላይ ይሰራል፡፡ የውጫሌ ውል አንቀጽን የሚገልጽ የማዕከሉ ዋና መግቢያ በር ላይ የግዕዙ 17 ቁጥር ይኖራል፡፡
የባህል ማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ ሙዚየምና ካፍቴሪያ የሚኖረው ሲሆን፤ ሙዚየሙም ሆነ የባህል ማዕከሉ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያሳዩ መረጃዎችን እንደሚያካትት ኢንጂነር ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡
የማዕከሉ ግንባታ አሰሪ መስሪያ ቤት የአማራ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሲሆን፤ ኮንትራክተሩ የአማራ ህንፃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው፡፡ አማካሪው የደቡብ ወሎ ዞን ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን መምሪያ ነው። ለግንባታው 25 ሚሊዮን 734ሺ 720 ብር ወጭ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት23/2011
በዋለልኝ አየለ