ቀደም ባሉት ሥርዓቶች በአገራችን የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ጥቂት መሆናቸው ይታወሳል፡፡ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደዚያ የሚዘልቁትም ውስን ዜጎች ነበሩ፡፡
ይሁንና በጎ ገጽታቸው በተለያየ መንገድ ይነሳል፡፡ በተለይ የ1960 ዎቹ ትውልድ በትምህርት ቆይታቸውም ሆነ ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም ከገቡ በኋላ ሀገርን የሚለውጥ ሃሳብ የሚያፈልቁ፣ ለህዝብ ሰላምና ብልጽግና የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ወደ ኋላ የማይሉ፣ ብሄራዊ ማንነት እንደተከበረ አንድነት የሚጠነክርበትን መንገድ የሚሹ የበሳል አዕምሮ ባለቤቶች እንደነበሩ በታሪክ ይነሳል፣ በተግባራቸውም አሳይተዋል፡፡
‹‹ያ ትውልድ›› ለእኔነት ሳይሆን ለእኛነት በቁርጠኝነት ሲታገል እንደነበርም በብዙዎች ምስክርነት የሚሰጠው ነው፡፡ ቁርጠኛ በሆኑ ተማሪዎችም አማካይነት አገራችንን አላንቀሳቅስ ብሎ የኋልዮሽ ይጎትታት የነበረው ማርሽ ስለመቀየሩ በህያው ተግባራቸው ይታወሳሉ፡፡
ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ምሩቃን የአንድን አገር ገጽታ ከመቀየር አኳያ ሚናቸው ጉልህ ነው፡፡ ምክንያት ቢባል የተማረ የሰው ኃይል ያለው አገር የሚታቀዱ እቅዶችን በማስፈጸሙ በኩልም ይሁን አዳዲስ ሃሳቦችን በማመንጨትና በመተግበሩ በኩል አዎንታዊ ድርሻ ስለሚኖረው ነው፡፡ የ ‹‹ያ ትውልድ›› መገለጫም ይኸው ነበር፡፡ አሁን በአገራችን ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ቢያሻቅብም፤ የዚያኑ ያህልም ተማሪውም ከዓመት ዓመት ከፍ ቢልም ከቀድሞው ትውልድ ሲነጻጸር አንዳንድ የማይጠበቁ ክፍተቶች መኖራቸው መፍትሄ እንደሚያስፈልገው አመላካች ነው፡፡
መንግሥትም በተቻለው ሁሉ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለሚማሩ ተማሪዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ደፋ ቀና ሲል ይታያል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውስን ተማሪዎች ዘንድ እየታየ ያለው አዝማሚያ ከምንም በላይ የአቅሙን ብቻ ሳይሆን ባይኖረውም ተበድሮ እያስተማረ ላለው ወላጅ ፈተና እየሆነበት ይገኛል፡፡ለሀገር ሰላምም ጠንቅ ነው፡፡
በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ የፖለቲካ ፍጆታ ለማግኘት በሚንቀሳቀሱ አካላት በሚለኮሰ ፀብ አጫሪነት ምክንያት የተማሪዎች የእርስ በርስ መገፋፋትና መናቆር ትምህርትን በሚፈለገው ልክ ለመከታተልና ብሎም ለቁም ነገር ለመብቃት ዋና መሰናክል በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ድርጊት የራሱ የተማሪውንም የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚያጨልም ነው፡፡ ውድቀቱና ስጋቱ የተማሪ አሊያም የወላጅ ብቻ አይደለም፡፡
አገርም እንደ አገር መቀጠል የሚችለው የተማረና መልካም ሥነ ምግባር ያለው ዜጋ ሲኖረው ነውና በተማሪዎች አካባቢ የሚታየው እንቅስቃሴ መንግሥትንም ህዝብንም የማያስተኛ ነውና በፍጥነት ሊገታ ይገባል፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ ተገቢ ያልሆነው፤ ተማሪውን እርስ በርሱ ዱላ የሚያማዝዘው ርዕሰ ጉዳይ የፖለቲካ ትርፍ ፈላጊዎች አጀንዳ መሆኑና ውሃ የማይቋጥርም ምክንያት መጠቀሱ ነው፡፡ በብዙዎቹ ተማሪዎች ዘንድ ላለመግባባቶች ምክንያት የሚሆነው ተራ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬ መሆኑም ያሳስባል፡፡ በእዚህም እንቁ የሆነው የትምህርት ጊዜ ላይመለስ እብስ ሲልባቸው ይስተዋላል፡፡ ስለሆነም ትውልዱ ዱላ ከመማዘዝ ይልቅ በሀሳብ ልዕልና መታገል የተሻለ መሆኑን መገንዘብ አለበት፡፡ ከ‹‹ያ ትውልድ›› መልካሙን ነገር መማርም አለበት፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ማዕከላት ጭምር በመሆናቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚፈልቁባቸው ናቸውና ተማሪዎቻችን የእርስ በርሱን መናቆር ወዲያ ጥለው ጊዜያቸውን ለመጡበት ዓላማ ማዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሁለትና ሦስት ተማሪዎች መካከል የሚነሳው አተካራ ለግጭት በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሚጠበቅ አካሄድ ባለመሆኑም ሊታረም ይገባል፡፡ የጎንደር፣ የመቱ እና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህንኑ ጉዳይ በመቃወም ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ የሚበረታታና የሚደገፍ ነው፡፡ ከግጭት ሞትና ጉዳት እንጂ መልካም ነገር አይገኝምና፡፡
ያለአንዳች አሳማኝ ምክንያት እኔነትን ብቻ በማስቀደም ለግጭት የሚደረግ ሩጫ ቅቡልነት የሌለው በመሆኑ ሊወገዝ ግድ ነው፡፡
አገሪቱ እየተከተለች ያለው የለውጥ ጅማሬ እኔነትን የሚሰብክ ሳይሆን አብሮነትን የሚያጎላ ነው፡፡ በመደመር እኛነትን ማጉላት ብልህነትም አዋጭም አካሄድ ነውና፤ ተማሪዎች ይህንን አመለካከት የአደባባይ ሰልፍ ሲኖር ብቻ ሳይሆን በሚማሩበትም ቅጥር ግቢ ውስጥም ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ጥበብንና ማስተዋልን ለማግኘት መትጋት የግድ ነው፡፡ እንደ ውቂያኖስ ጥልቅ የሆነውን ጥበብ በመምህሩ ከሚሰጠው ትምህርት ብቻ እየጨለፉ ከመረዳት ይልቅ ጠልቆ በመዋኘት ጊዜን ለተሰለፉበት አላማ ማዋል ይገባል፡፡ ዓላማን መሳት የተነሱበትን ጉዞ ከማሰናከሉም ባሻገር ህይወትንም ሊያስቀጥፍ እንደሚችል መረዳት ብልህነት ነው፡፡
ከምንም በላይ ግን በየዩኒቨርሲቲው ችግሮች ሲከሰቱ የመጀመሪያዎቹ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ተማሪዎች ቢሆኑም፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ስነ ምግባር መበላሸት የመጀመሪያው መስመር ላይ የሚመጡ ናቸውና ልጆችን በኃላፊነት ስሜት ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲሁም በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራንም ለተማሪዎች ሥነ ምግባር የጎላ ሚና ይኖራቸዋልና ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ትውልድን ከመቅረጽ አኳያ መልካም አርዓያ በመሆን መልካም ስነ ምግባርን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከፍ ሲልም ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲያስተምሩ የሚጠበቅባቸው የቀለም ትምህርትን ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ተማሪውን ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ የመቅረጽ አኃላፊነትም አለባቸውና ለዚህም የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡