የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፔድሮ ሳንቼስ ባሳለፍነው ሰኞ ለጋዜጠኞች አፍሪካ እና አውሮፓን ለአንድ አላማ በጋራ ያስተሳስራል ያሉትን እቅድ ይፋ አድርገዋል። በዚህም ከሁለቱ አህጉራት ሶስት አገራት ይሳተፉበታል ያሉትን የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ጥያቄ ለዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር «ፊፋ» ለማቅረብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል። ማህበሩ ማመልከቻቸውን ይቀበለዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 የሚዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ ሁለቱ አህጉራት በጋራ እንዲያዘጋጁ አቅደዋል። የዓለም ዋንጫ ውድድሩንም ሞሮኮ፣ ስፔን እና ፖርቹጋል ማሰናዳት እንዲችሉ ለፊፋ ማመልከቻ ለማስገባት ነው ያሰቡት።
«ሃሳቡን ከሞሮኮው ንጉስ ሞሃመድ ስድስተኛ ጋር ተወያይተንበታል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን እቅዱን ለሞሮኮ መንግስት አሳውቄያለሁ» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እቅዱ እውን የሚሆን ከሆነ ሁለቱ አህጉራት በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያዘጋጁት ውድድር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መሰናዶውን ተከትሎ ከሞሮኮ መንግስት እና ንጉሳውያን ቤተሰቦች ጋር ከመወያየታቸው በፊት የሞሮኮ ፌዴሬሽን የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ፊፋ ይፋ በሚያደርገው የዝግጅት ጥያቄ ማመልከቻ ላይ እንዲሳተፍ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
መቀመጫውን ፈረንሳይ ውስጥ ያደረገው ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ሁኔታውን ለማጣራት የሞሮኮ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ኢዲን ኢል ኦትማኒ ጋር ግንኙነት አድርጎ ለማጣራት ሙከራ ቢያደርግም ሁለቱ አህጉሮች ለማዘጋጀት እቅድ መያዝ አለመያዛቸውን ከማረጋገጥ ተቆጥበዋል። ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት አምስት ጊዜ ለፊፋ ማመልከቻ ብታቀርብም ውድቅ ሆኖባታል።
በ2022 የሚዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ ኳታር የምታሰናዳው ሲሆን፤ በ2026 የሚዘጋጀውን ደግሞ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በጋራ የሚያዘጋጁት ይሆናል። በ2030 ፊፋ ለሚያዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ተመራጭ ለመሆን ከወዲሁ በርካታ አገራት ይፎካከራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ የደቡብ አሜሪካ እና ብቻቸውን ማዘጋጀት የሚፈልጉ የአውሮፓ አገራት በጨረታው ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኡራጓይ፣ አርጀንቲና እንዲሁም ፓራጓይ ከደቡብ አሜሪካ ማመልከቻውን የሚያስገቡ ሲሆን፤ ግሪክ፣ ቡልጋሪያ፣ ሰርቢያ እንዲሁም ሮማኒያ በጋራ ዝግጅቱን ለማሰናዳት ጥያቄ ያቀርባሉ ተብሎ ይታሰባል። አየርላንድ እና እንግሊዝም ፉክክሩ ውስጥ አሉበት። የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር በ2020 ጨረታውን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በ2030 ገና በርካታ ዓመት የሚቀሩት ቢሆንም ፉክክሩ ግን ከወዲሁ ጀምሯል። አሁን እንደታቀደው አገራት በጋራ የሚያዘጋጁ ከሆነ ከሁለት በላይ አገራት የሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ የመሆን እድሉ የሰፋ ነው።
ዳግም ከበደ