415 ኢትዮጵያዊያን ከፑንትላንድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት በድንበር በኩል በዛሬው እለት ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በህገ ወጥ ደላሎች በመታለል በፑንትላንድ አድርገው በቦሳሶ በኩል ባህር አቋርጠው ወደ የመንና ሳኡዲ አረብያ ለመግባት ሲጓዙ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ከፑንትላድ አስተዳደር ጋር በመተባበር በራሳቸው ፈቃድ ወደ አገር ቤት የመመለስ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው፡፡
ህገ ወጥ ደላሎች ቦሳሶ ካደረሷቸው በኋላ በመንገድ ላይ በትነዋቸው እንደሚሄዱ የሚገልጹት ዜጎች ፑንትላንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ከፑንትላንድ የክልል መስተዳደር ጋር በመተባበር ከእስር ቤት በማስወጣት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል።
በእስካሁኑ እንቅስቃሴም 1ሺህ ዜጎችን ከፑንትላንድ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በማድረስ ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ክትትል እየተደረገ ይገኛል። በህገ ወጥ ደላሎች ከሚደርስባችው እንግልት ማምለጥ በመቻላቸው ደስተኞች መሆናቸውንም አኒሁ ዜጎች ገልጸዋል።
በዛሬው እለት ደግሞ 415 ኢትዮጵያዊያን ፑንትላንድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት በድንበር በኩል ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።
በተመሳሳይ ከዓለም አቀፉ የስደተኞቸ ድርጅት ጋር በመተባበር 517 ዜጎቻችንን ለመመለስ አስፈላጊው የጉዞ ሰነድ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ይጠበቃል።