
– በጥቃቱም የጦር አዛዦችና ሳይንቲስቶች ተገድለዋል
እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ሥፍራዎች እና የጦር አዛዦቿ ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሟን የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታወቀ። በዚህ ከባድ በተባለው ጥቃት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ሆሴይን ሳላሚ መገደላቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም መሐመድ ባግሄሪ በዚህ ጥቃት ከተገደሉት መካከል አንዱ ናቸው። ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ በአውሮፓውያኑ 1980 አብዮታዊ ዘቡን የተቀላቀሉ ሲሆን ከሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች አንዱ ናቸው።
የሀገሪቱ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ የነበሩት የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ፍሬይዱን አባሲ ሌላኛው በዚህ ጥቃት የተገደሉ ናቸው። ፍሬይዱን አባሲ ለኢራን የኒውክሌር ማበልጸግ የአንበሳውን ድርሻ እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል። ሳይንቲስቱ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2010 በቴህራን ጎዳና ላይ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው ነበር።
ሌላኛው በዚህ ጥቃት የተገደሉት የኒውክሌር ሳይንቲስት እና በቴህራን የሚገኘው የእስላሚክ አዛድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መህዲ ቴህራንቺ ናቸው። እስራኤል በዚህ ጥቃት የገደለቻቸው ስድስት የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መሆናቸውን ኢራን ገልጻለች።
የኒውክሌር ሳይንቲስቱ እና በሻሂድ ቡህሽቲ ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ኢንጂነሪንግ ኃላፊ የሆኑት አብዶልሃሚድ ሚኖሸር፣ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር የሆኑት አህመድ ረዛ ዞልፋጋሪ እንዲሁም በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲው የኒውክሌር ፕሮፌሰር የሆኑት አሚርሆሴን ፈቂ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የተገደሉ ናቸው።
በተጨማሪም ሞታልቢዛዴህ የተሰኘ የኒውክሌር ሳይንቲስት መገደሉ ተገልጿል። በተጨማሪም የኢራን ጦር ምክትል አዛዥ እና የካህታም አል አንቢያ የተሰኘው ማዕከላዊ ዋና መስሪያ ቤት ኃላፊ ጎላማሊ ራሺድ ተገድለዋል።
የኢራኑ ታላቁ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አማካሪ አሊ ኻምካኒ የከፋ ጉዳት እንደደረሰባቸው የኢራን ዘገባዎች አመልክተዋል።
እስራኤል ኢላማ ያደረግኩት ወታደራዊ ይዞታዎችን ነው ብትልም፤ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው በቴህራን የመኖሪያ ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እና ከተገደሉትም መካከል ሲቪሊያን ይገኙበታል ብለዋል።በኢራን መዲና ቴህራን ከፍተኛ ፍንዳታ እየተሰማ መሆኑም ተገልጿል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀገራቸው በኢራን የፈጸመችው ጥቃት ‘ኦፕሬሽን ራይዚንግ ላየን’ [የሚያንሰራራ አንበሳ ዘመቻ] ሲሉ የጠሩት አካል ነው ብለዋል። በተጨማሪም ኢራን ለእስራኤል የህልውና ስጋት መሆኗን ተናግረዋል።
ኢራን በምላሹ በቅርቡ አጸፋዊ የመልሶ ማጥቃት ልታደርስ እንደምትችል የገለጸችው እስራኤል የአስቸኳይ ጊዜ አውጃለች። የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ዘግቧል።
ሆሴይን ሳላሚ በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው። የሀገሪቱ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ የነበሩት የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ፍሬይዱን አባሲ መገደላቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ፍሬይዱን አባሲ ለኢራን የኒውክሌር ማበልጸግ የአንበሳውን ድርሻ እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል። ሳይንቲስቱ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2010 በቴህራን ጎዳና ላይ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው ነበር።
ሌላኛው በዚህ ጥቃት የተገደሉት የኒውክሌር ሳይንቲስት በቴህራን የሚገኘው የእስላሚክ አዛድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መህዲ ቴህራንቺ ናቸው። ኢራን አሜሪካ የእስራኤልን ጥቃት ደግፋለች ስትል የከሰሰች ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው ሀገራቸው እንዳልተሳተፈች ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ጥቃቶቹ እንደሚፈጸሙ እንደሚያውቁ፤ ነገር ግን ሀገራቸው እንዳልተሳተፈች ለፎክስ ኒውስ ገልጸዋል። ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ድርድር እንደምትቀጥል ተስፋ እንዳላቸው በድጋሚ ተናግረዋል።
“ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ሊኖራት አይገባም እናም ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመመለስ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል። ኢራን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል የፈጸመችባትን ጥቃት እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርባለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱ “የዓለምን ደህንነት ታይቶ ለማያውቅ ስጋት አጋልጦታል” ብሏል። የእስራኤል ዋና አጋር አሜሪካ ለጥቃቱ መዘዝ ተጠያቂ እንደምትሆንም ነው ሚኒስትሩ ያስጠነቀቀው።
ጥቃቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለቱም ወገኖች “ከፍተኛ መቆጠብ” እንዲያሳዩ ሲጠይቅ አውስትራሊያ በበኩሏ በዚህ መልኩ ማገርሸቱ “አስጊ” ነው ብላለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እስራኤል በኢራን ኒውክሌር ይዞታዎች ላይ ያደረሰችውን ጥቃት አውግዘው ሁለቱም ወገኖች ቀጠናው ወደ ከፋ ጦርነት እንዳይገባ እንዲቆጠቡ ጥሪ አድርገዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም