የመካከለኛው ምሥራቅን ቀውስ የሚያባብሰው ጥቃት

እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማትና ወታደራዊ ጣቢዎች ላይ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች። የእስራኤል አየር ኃይል በአምስት ዙሮች በወሰደው ርምጃ በስምንት ቦታዎች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶችን ፈጽሟል። ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሥፍራዎች መካከል በናታንዝ የሚገኘው ዋናው የዩራኒየም ማብላያ ጣቢያ እና የታብሪዝ የኒውክሌር ምርምር ተቋም እንደሚገኙበት ተገልጿል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጥቃቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጥቃቶቹ የኢራንን የኒውክሌር መሠረተ ልማቶችንና የባሊስቲክ ሚሳኤል ማምረቻ ተቋማትን ለማውደም የተፈጸሙ እንደሆኑ ተናግረዋል። ዘመቻው በእስራኤልና በእስራኤላውያን ሕልውና ላይ የተጋረጠው ስጋት እስከሚወገድ ድረስ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።

የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ኢያል ዛሚር የኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ግንባታ ብዙ ደረጃዎችን ማለፉን ጠቁመው፤እስራኤል ሕልውናዋን ለማስከበር ርምጃ ለመውሰድ የምትጠብቀው ሌላ ጊዜ እንደሌላት ተናግረዋል። “ርምጃችንን ሊያስቆም የሚሞክር ማንኛውም ኃይል ከባድ ዋጋ ይከፍላል” ብለውም አስጠንቅቀዋል።

እስራኤል ኢላማ ያደረገችው ወታደራዊ ይዞታዎችን እንደሆነ ብትገልጽም፤ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ግን በቴህራን የመኖሪያ ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እና ከተገደሉትም መካከል ሰላማዊ ሰዎች እንደሚገኙበት ዘግበዋል።

እስራኤል በፈጸመችው ከባድ ጥቃት የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸውን የኢራንና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል የኢራን አብዮታዊ ዘብ (Islamic Revolutionary Guard Corps) ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሁሴን ሳላሚ እና የሀገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጀኔራል መሐመድ ባግሄሪ እንዲሁም ስድስት የኒውክሌር ሳይንቲስቶች እንደሚገኙበት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከተገደሉት የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መካከል ደግሞ የቀድሞው የኢራን የአቶሚክ ኃይል ድርጅት ኃላፊ ፈሪይዱን አባሲ እና የአዛድ እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ይገኙበታል ተብሏል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጥቃቱ የተለያየ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። ቱርኪዬና በርካታ የአረብ ሀገራት የእስራኤልን ድርጊት በጥብቅ ኮንነዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፤ ሁሉም ወገኖች ተጨማሪ ውድመትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጠይቀዋል። አሜሪካና ኢራን ድርድር ላይ ባሉበት ወቅት እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟ እንዳሳሰባቸው በቃል አቀባያቸው በኩል ገልጸዋል።

ቻይና ድርጊቱ በጣም እንዳሳሰባት እና ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለች መሆኗን ገልጻ፤ ሁሉም ወገኖች ተጨማሪ ግጭት ከሚፈጥሩ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርባለች። የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ ኢራንና እስራኤል ውጥረት እንዲያረግቡ ጠይቋል።

ቼክ ሪፐብሊክ የእስራኤል ጥቃት “ምክንያታዊ ምላሽ” ነው ብለዋለች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ሊፓቭስኪ ኢራን እስራኤልን ለማጥፋት የሚታገሉ ቡድኖችን እንደምትደግፍና ኒውክሌር ለመታጠቅም እየሠራች እንደሆነ ገልጸው፤ ጥቃቱ እስራኤል የተጋረጠባትን የኒውክሌር ቦምብ ስጋት ለመቀልበስ የወሰደችው ምክንያታዊ ርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል።

የእስራኤል ሁነኛ አጋር አሜሪካ በጥቃቱ እጇ እንደሌለበት ገልጻለች። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከ“ፎክስ ኒውስ” (Fox News) ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሜሪካ በጥቃቱ እንዳልተሳተፈች ተናግረዋል። “ኢራን ፈጽሞ ኒውክሌር ልትታጠቅ አትችልም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ወደ ድርድር እንደምትመለስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ኢራን ለእስራኤል የአፀፋ ምላሽ ከሰጠች ግን አሜሪካ እስራኤልን እንደምታግዝም ተናግረዋል። ኢራን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ካልደረሰች የከፋ ቅጣት እንደሚጠብቃት ሲያስጠነቅቁ የነበሩት ትራምፕ፤ ኢራን ከእዚህም የባሰ ክፉ ነገር ከመፈጠሩ በፊት የድርድር እድሏን እንድትጠቀምበት አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው፤ “አሜሪካ በእዚህ ጥቃት ምንም ተሳትፎ የላትም። የእኛ ቀዳሚ አጀንዳ በቀጣናው ያሉ አሜሪካውያንን ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ኢራን አሜሪካውያንንና የአሜሪካን ጥቅም ኢላማ እንዳታደርግ በግልጽ መናገር እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ስጋት ላይ ከጣሉት ጉዳዮች መካከል አንዱ በኒውክሌር መሠረተ ልማቶች ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች ፍንዳታዎችና ብክለትን ሊፈጥሩ እንዲሁም የሬዲዮአክቲቭ ጨረሮች ማፈትለክንም ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ አደገኛ ቀውሶችን ሊፈጥር ይችላል ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን የተሰማ መጥፎ ዜና እንደሌለ አስታውቋል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ኤጀንሲው ከኢራን ባለሥልጣናትና በሀገሪቱ ካሉ ባለሙያዎቹ ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የናታንዝ የኒውክሌር ጣቢያ ጥቃት እንደተፈጸመበት አረጋግጠው፤ ኤጀንሲው ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለው እንደሚገኝ ተናግረዋል። በኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት አደገኛ ውጤቶችን እንደሚያስከትል ጠቁመው፤ ሁሉም ወገኖች ከመሰል ድርጊቶች እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

ኢራን እስራኤል ለፈጸመችባት ጥቃት “በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የአፀፋ ምላሽ እሰጣለሁ” ብላ ዝታለች። የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያላህ አሊኻሜኒ እስራኤል የምትጸጸትበት ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃት ተናግረዋል። የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀኔራል ኤፊ ደፍሪን ኢራን ከ100 በላይ ድሮኖችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን እና ጦሩ ድሮኖቹን እያከሸፈ እንደሆነ ተናግረዋል።

አሜሪካ ጥቃቱ እስራኤል በተናጠል የወሰደችው ርምጃ እንደሆነና በጥቃቱ ተሳትፎ እንደሌላት ብትገልጽም፤ ኢራን ግን እስራኤል ያለአሜሪካ ፈቃድና ይሁንታ ይህን ጥቃት እንዳልፈጸመችው ታምናለች። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ቴህራን ለተፈጸመባት ጥቃት ምላሽ የመስጠት ሕጋዊና ተገቢ መብት እንዳላት አስታውቋል። “እስራኤል ካለአሜሪካ ትብብርና ፈቃድ ይህን ጥቃት አልፈጸመችውም። ኢራን በጥቃቱ የተሳተፉትን ሁሉንም አካላት ኢላማ ያደረገ ምላሽ ትሰጣለች” ብሏል።

አሜሪካ ከቀናት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶቿንና ቤተሰቦቻቸውን ከሀገራቱ ልታስወጣ እንደሆነ መግለጿ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም መረጃ እንደነበራት አመላካች ነው ተብሏል። አሜሪካ በኢራቅ ኤምባሲዋ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን በከፊል ለማስወጣት እየተዘጋጀች እንደሆነና በባህሬን፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና በኩዌት የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ቤተሰቦች ደግሞ በፈቃዳቸው ከሀገራቱ እንዲወጡ ለማድረግ እንዳቀደች ከጥቂት ቀናት በፊት ተገልጾ ነበር።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በድጋሚ ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ ወዲህ አሜሪካና ኢራን በኦማን አደራዳሪነት አምስት ዙር ውይይቶችን አካሂደዋል። ውይይቶቹ እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት አላስገኙም። የአሜሪካ ዩራኒየም የማበልጸግ ሂደቱን የማቋረጥ ጥያቄና የኢራን ያለማቋረጥ አቋም የሁለቱ አካላት የክርክር ነጥብ ሆኖ ዘልቋል።

የኢራንን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት የሕልውናዋ ዋና አደጋ አድርጋ የምትመለከተው እስራኤል ግን በኢራን የኑክሌር ድርድር ላይ በሚደረጉ ድርድሮች እምነት የላትም። የእስራኤል ባለሥልጣናት በቀጣናው እስራኤልን የሚወጉ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች ብለው የሚከሷትን ኢራንን እንደ ዋና አደጋ ይመለከቷታል። ኢራን የኑክሌር ቦምብ ልትታጠቅ ጫፍ ላይ እንደደረሰች ደጋግማ በመግለጽ ወታደራዊ ርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት መቆየቷ ይታወሳል።

ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ የመድረስ ተስፋ የነበራቸውና “ስምምነት ላይ ልንደርስ ነው” ብለው እርግጠኛ ሆነው ሲናገሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ግን በሀገራቸውና በኢራን መካከል የሚደረገው ውይይት ውጤት ያመጣል የሚለው ተስፋቸው እንደተመናመነ ተናግረው ነበር።

“ሲኤንኤን” (CNN) ከሦስት ሳምንታት በፊት ባሰራጨው ዘገባ፤ እስራኤል በኢራን የኑክሌር መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀች እንደነበር ገልጿል። ጣቢያው ስማቸው ካልተገለጸ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት፤ እስራኤል በመካሄድ ላይ ያለውን የአሜሪካንና የኢራንን ድርድር ወደ ጎን በማለት በራሷ እቅድና ፍላጎት ኢራንን ለማጥቃት እየተዘጋጀች ነው ብሎ ዘግቧል።

ኢራን በእስራኤል ጥቃት ከባድ ጉዳት እንዳስተናገደች እየተገለጸ ነው። ኢራንም ከደረሰባት ጉዳት አንጻር በእስራኤል ላይ የምትወስደው የአጸፋ ርምጃ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን የአፀፋ ርምጃ ከወሰደች አሜሪካ እስራኤልን እንደምትደግፍ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ የግጭቱን ተዋንያን በማብዛት ወትሮም ቢሆን ሰላም ለራቀው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ተጨማሪ የደህንነት አደጋ እንዳይፈጥር ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል ሲሉ ምሁራን ያስጠነቅቃሉ።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You